ዘፀአት 8:1-32

  • ሁለተኛው መቅሰፍት፦ እንቁራሪቶች (1-15)

  • ሦስተኛው መቅሰፍት፦ ትንኝ (16-19)

  • አራተኛው መቅሰፍት፦ ተናካሽ ዝንብ (20-32)

    • መቅሰፍቱ ጎሸንን አልነካም (22, 23)

8  ከዚያም ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ “ወደ ፈርዖን ገብተህ እንዲህ በለው፦ ‘ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “እንዲያገለግለኝ ሕዝቤን ልቀቅ።+  እነሱን ለመልቀቅ አሁንም ፈቃደኛ የማትሆን ከሆነ ምድርህን በሙሉ በእንቁራሪት መቅሰፍት እመታለሁ።+  የአባይም ወንዝ በእንቁራሪቶች ይሞላል፤ እነሱም ወጥተው ወደ ቤትህ፣ ወደ መኝታ ክፍልህ ይገባሉ፤ አልጋህም ላይ ይወጣሉ፤ እንዲሁም ወደ አገልጋዮችህ ቤቶች ይገባሉ፤ ሕዝብህም ላይ ይወጣሉ፤ መጋገሪያ ምድጃዎችህና ቡሃቃዎችህም ውስጥ ይገባሉ።+  እንቁራሪቶቹ በአንተ፣ በሕዝብህና በአገልጋዮችህ ሁሉ ላይ ይወጡባችኋል።”’”  በኋላም ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ “አሮንን እንዲህ በለው፦ ‘እጅህን ሰንዝረህ ወንዞቹን፣ የአባይ ወንዝ የመስኖ ቦዮቹንና ረግረጋማ ቦታዎቹን በበትርህ በመምታት እንቁራሪቶቹ በግብፅ ምድር ላይ እንዲወጡ አድርግ።’”  ስለዚህ አሮን በግብፅ ውኃዎች ላይ እጁን ሰነዘረ፤ እንቁራሪቶቹም እየወጡ የግብፅን ምድር መውረር ጀመሩ።  ይሁን እንጂ አስማተኞቹ ካህናትም በሚስጥራዊ ጥበባቸው ተመሳሳይ ነገር ፈጸሙ፤ እነሱም እንቁራሪቶች በግብፅ ምድር ላይ እንዲወጡ አደረጉ።+  ከዚያም ፈርዖን ሙሴንና አሮንን ጠርቶ “ሕዝቡ ለይሖዋ መሥዋዕት እንዲያቀርብ መልቀቅ ስለምፈልግ እንቁራሪቶቹን ከእኔም ሆነ ከሕዝቤ ላይ እንዲያስወግድ ይሖዋን ለምኑልኝ”+ አላቸው።  ከዚያም ሙሴ ፈርዖንን እንዲህ አለው፦ “እንቁራሪቶቹ ከአንተ፣ ከአገልጋዮችህ፣ ከሕዝብህና ከቤቶችህ ይወገዱ ዘንድ አምላክን እንድለምንልህ የምትፈልገው መቼ እንደሆነ የመወሰኑን ጉዳይ ለአንተ ትቼዋለሁ። እንቁራሪቶቹ በአባይ ወንዝ ውስጥ ብቻ ተወስነው ይቀራሉ።” 10  እሱም “ነገ ይሁን” አለው። በመሆኑም ሙሴ እንዲህ አለው፦ “እንደ አምላካችን እንደ ይሖዋ ያለ ማንም እንደሌለ+ እንድታውቅ ልክ እንዳልከው ይሆናል። 11  እንቁራሪቶቹ ከአንተ፣ ከቤቶችህ፣ ከአገልጋዮችህና ከሕዝቦችህ ይወገዳሉ። በአባይ ወንዝ ውስጥ ብቻ ተወስነው ይቀራሉ።”+ 12  ሙሴና አሮንም ከፈርዖን ፊት ወጥተው ሄዱ፤ ሙሴም ይሖዋ በፈርዖን ላይ ያመጣቸውን እንቁራሪቶች አስመልክቶ ወደ እሱ ጮኸ።+ 13  ይሖዋም ሙሴ እንደጠየቀው አደረገ፤ እንቁራሪቶቹም በየቤቱ፣ በየግቢውና በየሜዳው መሞት ጀመሩ። 14  እነሱም እንቁራሪቶቹን በየቦታው ከመሯቸው፤ ምድሪቱም መግማት ጀመረች። 15  ፈርዖንም ችግሩ ጋብ ማለቱን ባየ ጊዜ ልቡን አደነደነ፤ ልክ ይሖዋ እንደተናገረውም እነሱን ለመስማት ፈቃደኛ አልሆነም።+ 16  በዚህ ጊዜ ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ “አሮንን እንዲህ በለው፦ ‘በትርህን ሰንዝረህ የምድርን አቧራ ምታ፤ አቧራውም በመላው የግብፅ ምድር ላይ ትንኝ ይሆናል።’” 17  እነሱም እንዲሁ አደረጉ። አሮን በእጁ የያዘውን በትር ሰንዝሮ የምድርን አቧራ መታ፤ ትንኞቹም ሰዉንም እንስሳውንም ወረሩ። በምድሪቱ ያለው አቧራ ሁሉ በመላው የግብፅ ምድር ላይ ትንኝ ሆነ።+ 18  አስማተኞቹ ካህናትም ተመሳሳይ ነገር ለመፈጸምና በሚስጥራዊ ጥበባቸው ትንኞች እንዲፈሉ ለማድረግ ሞከሩ፤+ ሆኖም አልቻሉም። ትንኞቹ ሰዉንም እንስሳውንም ወርረው ነበር። 19  በመሆኑም አስማተኞቹ ካህናት ፈርዖንን “ይህ የአምላክ ጣት ነው!”+ አሉት። የፈርዖን ልብ ግን ደነደነ፤ ልክ ይሖዋ እንዳለውም እነሱን አልሰማቸውም። 20  ከዚያም ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ “በማለዳ ተነስተህ ፈርዖን ፊት ቁም። እሱም ወደ ውኃው ይወርዳል! አንተም እንዲህ በለው፦ ‘ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “እንዲያገለግለኝ ሕዝቤን ልቀቅ። 21  ሕዝቤን የማትለቅ ከሆነ ግን በአንተ፣ በአገልጋዮችህና በሕዝብህ ላይ እንዲሁም በቤቶችህ ውስጥ ተናካሽ ዝንብ እለቃለሁ፤ ዝንቦቹም በግብፅ ያሉትን ቤቶች ይሞላሉ፤ አልፎ ተርፎም የቆሙበትን* መሬት ይሸፍናሉ። 22  በዚያ ቀን ሕዝቤ የሚኖርበትን የጎሸንን ምድር እለያለሁ። በዚያ ምንም ተናካሽ ዝንብ አይኖርም፤+ ይህን በማድረጌም እኔ ይሖዋ በምድሪቱ መካከል እንዳለሁ ታውቃለህ።+ 23  እኔም በሕዝቤና በሕዝብህ መካከል ልዩነት እንዲኖር አደርጋለሁ። ይህ ምልክት ነገ ይፈጸማል።”’” 24  ይሖዋም እንዳለው አደረገ፤ የተናካሽ ዝንብ መንጋም የፈርዖንን ቤትና የአገልጋዮቹን ቤቶች እንዲሁም መላውን የግብፅ ምድር መውረር ጀመረ።+ በተናካሽ ዝንቦቹም የተነሳ ምድሪቱ ክፉኛ ተበላሸች።+ 25  በመጨረሻም ፈርዖን ሙሴንና አሮንን ጠርቶ “ሂዱ፤ በምድሪቱም ለአምላካችሁ መሥዋዕት ሠዉ” አላቸው። 26  ሙሴ ግን እንዲህ አለው፦ “ይሄማ ተገቢ አይደለም፤ ምክንያቱም እኛ ለአምላካችን ለይሖዋ መሥዋዕት የምናደርገው ነገር ለግብፃውያን አስጸያፊ ነው።+ ታዲያ ግብፃውያን የሚጸየፉትን መሥዋዕት እዚያው እነሱ እያዩን ብናቀርብ አይወግሩንም? 27  ስለዚህ ወደ ምድረ በዳው የሦስት ቀን መንገድ እንጓዛለን፤ በዚያም አምላካችን ይሖዋ ባለን መሠረት ለእሱ መሥዋዕት እናቀርባለን።”+ 28  በዚህ ጊዜ ፈርዖን እንዲህ አለ፦ “በምድረ በዳ ለአምላካችሁ ለይሖዋ መሥዋዕት እንድታቀርቡ እለቃችኋለሁ። ብቻ ብዙ ርቃችሁ መሄድ የለባችሁም። ስለ እኔም ለምኑልኝ።”+ 29  ከዚያም ሙሴ እንዲህ አለው፦ “እንግዲህ አሁን ከአንተ ተለይቼ እወጣለሁ፤ ይሖዋንም እለምናለሁ፤ ተናካሽ ዝንቦቹም በነገው ዕለት ከፈርዖን፣ ከአገልጋዮቹና ከሕዝቡ ይወገዳሉ። ሆኖም ፈርዖን፣ ሕዝቡ ለይሖዋ መሥዋዕት ለማቅረብ እንዳይሄድ በመከልከል ሊያታልለን* መሞከሩን ይተው።”+ 30  ከዚያም ሙሴ ከፈርዖን ፊት ወጥቶ በመሄድ ይሖዋን ለመነ።+ 31  ይሖዋም ሙሴ እንዳለው አደረገ፤ ተናካሽ ዝንቦቹም ከፈርዖን፣ ከአገልጋዮቹና ከሕዝቡ ተወገዱ። አንድም ዝንብ አልቀረም። 32  ሆኖም ፈርዖን እንደገና ልቡን አደነደነ፤ ሕዝቡንም ለመልቀቅ ፈቃደኛ አልሆነም።

የግርጌ ማስታወሻ

ግብፃውያንን ያመለክታል።
ወይም “ሊጫወትብን።”