ዘፍጥረት 11:1-32

  • የባቤል ግንብ (1-4)

  • ይሖዋ ቋንቋቸውን ዘበራረቀ (5-9)

  • ከሴም እስከ አብራም (10-32)

    • የታራ ቤተሰብ (27)

    • አብራም ዑርን ለቆ ወጣ (31)

11  በዚህ ጊዜ፣ ምድር ሁሉ አንድ ቋንቋና ተመሳሳይ ቃላት ትጠቀም ነበር።  ወደ ምሥራቅ ሲጓዙም በሰናኦር+ ምድር ወደሚገኝ አንድ ሸለቋማ ሜዳ ደረሱ፤ በዚያም መኖር ጀመሩ።  እርስ በርሳቸውም “ኑ! ጡብ እንሥራ፤ በእሳትም እንተኩሰው” ይባባሉ ጀመር። በመሆኑም በድንጋይ ፋንታ ጡብ፣ ለማያያዣም ቅጥራን ተጠቀሙ።  ከዚያም “ኑ! በመላው ምድር ላይ እንዳንበተን+ ከተማና ጫፉ ሰማይ የሚደርስ ግንብ ለራሳችን እንገንባ፤ ስማችንንም እናስጠራ” ተባባሉ።  ከዚያም ይሖዋ ሰዎች የሠሩትን ከተማና ግንብ ለማየት ወረደ።  ይሖዋም እንዲህ አለ፦ “እነዚህ ሰዎች አንድ ቋንቋ የሚናገሩ አንድ ሕዝብ ናቸው፤+ ይኸው አሁን ደግሞ ይህን መሥራት ጀምረዋል። በዚህ ከቀጠሉ ያሰቡትን* ሁሉ ከማከናወን የሚያግዳቸው ምንም ነገር አይኖርም።  ና! እንውረድና*+ በቋንቋ እርስ በርስ እንዳይግባቡ ቋንቋቸውን እናዘበራርቅ።”  በመሆኑም ይሖዋ ከዚያ ቦታ ተነስተው በመላው ምድር ላይ እንዲበተኑ አደረገ፤+ እነሱም ቀስ በቀስ ከተማዋን መገንባታቸውን አቆሙ።  የከተማዋ ስም ባቤል*+ የተባለውም በዚህ የተነሳ ነው፤ ምክንያቱም ይሖዋ በዚያ የምድርን ሁሉ ቋንቋ አዘበራርቋል፤ እንዲሁም ይሖዋ ሰዎቹ ከዚያ ቦታ ተነስተው በመላው ምድር ላይ እንዲበተኑ አድርጓል። 10  የሴም+ ታሪክ ይህ ነው። ሴም የጥፋት ውኃ ከተከሰተ ከሁለት ዓመት በኋላ አርፋክስድን+ ሲወልድ የ100 ዓመት ሰው ነበር። 11  ሴም አርፋክስድን ከወለደ በኋላ 500 ዓመት ኖረ። ወንዶችና ሴቶች ልጆችንም ወለደ።+ 12  አርፋክስድ 35 ዓመት ኖረ፤ ከዚያም ሴሎምን+ ወለደ። 13  አርፋክስድ ሴሎምን ከወለደ በኋላ 403 ዓመት ኖረ። ወንዶችና ሴቶች ልጆችንም ወለደ። 14  ሴሎም 30 ዓመት ኖረ፤ ከዚያም ኤቤርን+ ወለደ። 15  ሴሎም ኤቤርን ከወለደ በኋላ 403 ዓመት ኖረ። ወንዶችና ሴቶች ልጆችንም ወለደ። 16  ኤቤር 34 ዓመት ኖረ፤ ከዚያም ፋሌቅን+ ወለደ። 17  ኤቤርም ፋሌቅን ከወለደ በኋላ 430 ዓመት ኖረ። ወንዶችና ሴቶች ልጆችንም ወለደ። 18  ፋሌቅ 30 ዓመት ኖረ፤ ከዚያም ረኡን+ ወለደ። 19  ፋሌቅ ረኡን ከወለደ በኋላ 209 ዓመት ኖረ። ወንዶችና ሴቶች ልጆችንም ወለደ። 20  ረኡ 32 ዓመት ኖረ፤ ከዚያም ሴሮህን ወለደ። 21  ረኡ ሴሮህን ከወለደ በኋላ 207 ዓመት ኖረ። ወንዶችና ሴቶች ልጆችንም ወለደ። 22  ሴሮህ 30 ዓመት ኖረ፤ ከዚያም ናኮርን ወለደ። 23  ሴሮህ ናኮርን ከወለደ በኋላ 200 ዓመት ኖረ። ወንዶችና ሴቶች ልጆችንም ወለደ። 24  ናኮር 29 ዓመት ኖረ፤ ከዚያም ታራን+ ወለደ። 25  ናኮር ታራን ከወለደ በኋላ 119 ዓመት ኖረ። ወንዶችና ሴቶች ልጆችንም ወለደ። 26  ታራ 70 ዓመት ከኖረ በኋላ አብራምን፣+ ናኮርን+ እና ካራንን ወለደ። 27  የታራ ታሪክ ይህ ነው። ታራ አብራምን፣ ናኮርን እና ካራንን ወለደ፤ ካራን ደግሞ ሎጥን+ ወለደ። 28  ካራንም አባቱ ታራ ገና በሕይወት እያለ፣ በተወለደበት አገር በከለዳውያን+ ዑር+ ሞተ። 29  አብራምና ናኮር ሚስት አገቡ። የአብራም ሚስት ስሟ ሦራ+ ሲሆን የናኮር ሚስት ደግሞ ስሟ ሚልካ+ ነበር፤ እሷም የሚልካ እና የዪስካ አባት የሆነው የካራን ልጅ ናት። 30  በዚህ ጊዜ ሦራ መሃን ነበረች፤+ ልጅም አልነበራትም። 31  ከዚያም ታራ ልጁን አብራምንና የልጁ ልጅ የሆነውን የካራንን ልጅ ሎጥን+ እንዲሁም የልጁ የአብራም ሚስት የሆነችውን ምራቱን ሦራን ይዞ ወደ ከነአን ምድር+ ለመሄድ ከከለዳውያን ዑር ተነሳ። ከጊዜ በኋላም ወደ ካራን+ መጡ፤ በዚያም መኖር ጀመሩ። 32  ታራም 205 ዓመት ኖረ። ከዚያም በካራን ሞተ።

የግርጌ ማስታወሻ

ወይም “የወጠኑትን።”
የዕብራይስጡ ቃል ሁለት ወይም ከዚያ በላይ የሆኑ አካላትን ሊያመለክት ይችላል።
“ዝብርቅ” የሚል ትርጉም አለው።