ዘፍጥረት 20:1-18

  • አቢሜሌክ ሣራን ለአብርሃም መለሰለት (1-18)

20  አብርሃም ድንኳኑን+ ከዚያ ነቅሎ ወደ ኔጌብ ምድር ሄደ፤ በቃዴስና+ በሹር+ መካከልም መኖር ጀመረ። በጌራራ+ እየኖረ* ሳለ  በድጋሚ ሚስቱን ሣራን “እህቴ ናት” አለ።+ በመሆኑም የጌራራ ንጉሥ አቢሜሌክ ሰዎችን ልኮ ሣራን አስመጣት፤ ከዚያም ወሰዳት።+  ከዚያም አምላክ ለአቢሜሌክ ሌሊት በሕልም ተገልጦለት “በወሰድካት ሴት የተነሳ ትሞታለህ፤+ ምክንያቱም እሷ ያገባችና ባለቤት ያላት ሴት ናት”+ አለው።  ሆኖም አቢሜሌክ ወደ እሷ አልቀረበም ነበር።* በመሆኑም እንዲህ አለ፦ “ይሖዋ፣ ምንም በደል ያልፈጸመን* ብሔር ታጠፋለህ?  እሱ ‘እህቴ ናት’ አላለኝም? እሷስ ብትሆን ‘ወንድሜ ነው’ አላለችም? ይህን ያደረግኩት በቅን ልቦናና በንጹሕ እጅ ነው።”  ከዚያም እውነተኛው አምላክ በሕልም ተገልጦለት እንዲህ አለው፦ “ይህን ያደረግከው በቅን ልቦና ተነሳስተህ እንደሆነ አውቃለሁ፤ በእኔም ላይ ኃጢአት እንዳትሠራ ጠብቄሃለሁ። እንድትነካት ያልፈቀድኩልህም ለዚህ ነው።  በል አሁን የሰውየውን ሚስት መልስ፤ እሱ ነቢይ ነውና፤+ ስለ አንተም ልመና ያቀርባል፤+ አንተም በሕይወት ትኖራለህ። እሷን ባትመልስ ግን በእርግጥ እንደምትሞት እወቅ፤ አንተም ሆንክ የአንተ የሆነው ሁሉ ትሞታላችሁ።”  አቢሜሌክ በማለዳ ተነሳ፤ አገልጋዮቹንም በሙሉ ጠርቶ የሆነውን ሁሉ ነገራቸው፤ እነሱም በጣም ፈሩ።  ከዚያም አቢሜሌክ አብርሃምን ጠርቶ እንዲህ አለው፦ “ይህ ያደረግክብን ነገር ምንድን ነው? በእኔም ሆነ በግዛቴ ላይ እንዲህ ያለውን ታላቅ ኃጢአት ያመጣህብን ለመሆኑ ምን በድዬህ ነው? ያደረግክብኝ ነገር ትክክል አይደለም።” 10  በመቀጠልም አቢሜሌክ አብርሃምን “ለመሆኑ ይህን ያደረግከው ምን አስበህ ነው?” አለው።+ 11  አብርሃምም እንዲህ አለው፦ “ይህን ያደረግኩት ‘በዚህ ስፍራ እንደሆነ ፈሪሃ አምላክ የሚባል ነገር የለም፤ ሰዎቹ ለሚስቴ ሲሉ ሊገድሉኝ ይችላሉ’ ብዬ ስለሰጋሁ ነው።+ 12  ደግሞም እኮ በእርግጥ እህቴ ናት፤ የእናቴ ልጅ ባትሆንም የአባቴ ልጅ ናት፤ እሷም ሚስቴ ሆነች።+ 13  በመሆኑም አምላክ ከአባቴ ቤት ወጥቼ ከአገር አገር እየዞርኩ እንድኖር በነገረኝ ጊዜ+ ‘በምንሄድበት ስፍራ ሁሉ “ወንድሜ ነው” ብለሽ በመናገር ታማኝ ፍቅር አሳዪኝ’ ብያት ነበር።”+ 14  ከዚያም አቢሜሌክ በጎችን፣ ከብቶችን እንዲሁም ወንድና ሴት አገልጋዮችን ለአብርሃም ሰጠው፤ ሚስቱን ሣራንም መለሰለት። 15  በተጨማሪም አቢሜሌክ “አገሬ አገርህ ናት፤ ደስ ባለህ ቦታ መኖር ትችላለህ” አለው። 16  ሣራንም እንዲህ አላት፦ “ይኸው ለወንድምሽ+ 1,000 የብር ሰቅል እሰጠዋለሁ። ይህም አንቺ ንጹሕ ሰው መሆንሽን ከአንቺ ጋር ባሉት ሰዎች ሁሉ ፊትም ሆነ በሌሎች ሰዎች ፊት የሚያሳውቅ ምልክት ነው፤* አንቺም ከማንኛውም ነቀፋ ነፃ ነሽ።” 17  አብርሃምም ወደ እውነተኛው አምላክ ልመና አቀረበ፤ አምላክም አቢሜሌክን፣ ሚስቱንና ሴት ባሪያዎቹን ፈወሳቸው፤ እነሱም ልጆች መውለድ ጀመሩ፤ 18  ምክንያቱም ይሖዋ በአብርሃም ሚስት በሣራ የተነሳ በአቢሜሌክ ቤት ያሉትን ሴቶች ሁሉ መሃን አድርጎ ነበር።*+

የግርጌ ማስታወሻ

ወይም “እንደ ባዕድ አገር ሰው ሆኖ።”
ወይም “ጻድቅ የሆነን።”
ከእሷ ጋር የፆታ ግንኙነት አለመፈጸሙን ያመለክታል።
ቃል በቃል “እነሆ፣ ይህ ለአንቺ የዓይን መሸፈኛ ነው።”
ወይም “በአቢሜሌክ ቤት ያለውን ማህፀን ሁሉ ፈጽሞ ዘግቶ ነበር።”