ዘፍጥረት 21:1-34

  • ይስሐቅ ተወለደ (1-7)

  • እስማኤል በይስሐቅ ላይ አፌዘበት (8, 9)

  • አጋርና እስማኤል ተባረሩ (10-21)

  • አብርሃም ከአቢሜሌክ ጋር የገባው ቃል ኪዳን (22-34)

21  ይሖዋ ልክ በተናገረው መሠረት ሣራን አሰባት፤ ይሖዋም ለሣራ ቃል የገባላትን አደረገላት።+  በመሆኑም ሣራ ፀነሰች፤+ ለአብርሃምም አምላክ ቃል በገባለት በተወሰነው ጊዜ ላይ በስተርጅናው ወንድ ልጅ ወለደችለት።+  አብርሃም ሣራ የወለደችለትን ልጅ ይስሐቅ ብሎ ጠራው።+  አብርሃምም ልክ አምላክ ባዘዘው መሠረት ልጁ ይስሐቅ ስምንት ቀን ሲሆነው ገረዘው።+  አብርሃም ልጁ ይስሐቅ ሲወለድ ዕድሜው 100 ዓመት ነበር።  ከዚያም ሣራ “አምላክ በደስታ እንድስቅ አድርጎኛል፤ ይህን የሰማም ሁሉ ከእኔ ጋር አብሮ ይስቃል”* አለች።  አክላም “ለመሆኑ ለአብርሃም ‘ሣራ ልጆች ታጠባለች’ ማን ብሎት ያውቃል? እኔ ግን ይኸው በስተርጅናው ወንድ ልጅ ወለድኩለት” አለች።  ልጁም አደገ፤ ጡትም ጣለ፤ አብርሃምም ይስሐቅ ጡት በጣለበት ቀን ትልቅ ግብዣ አደረገ።  ሣራም ግብፃዊቷ አጋር ለአብርሃም የወለደችለት ልጅ+ በይስሐቅ ላይ እንደሚያፌዝበት+ በተደጋጋሚ አስተዋለች። 10  ስለዚህ አብርሃምን “ይህችን ባሪያና ልጇን ከዚህ አባር፤ ምክንያቱም የዚህች ባሪያ ልጅ ከልጄ ከይስሐቅ ጋር ወራሽ አይሆንም!”+ አለችው። 11  አብርሃም ግን ሣራ ስለ ልጁ የተናገረችው ነገር በጣም ቅር አሰኘው።+ 12  ከዚያም አምላክ አብርሃምን እንዲህ አለው፦ “ሣራ ስለ ልጁና ስለ ባሪያህ እየነገረችህ ያለው ነገር ምንም ቅር አያሰኝህ። ዘርህ የሚጠራልህ በይስሐቅ በኩል ስለሆነ የምትልህን* ስማ።+ 13  የባሪያይቱም ልጅ+ ቢሆን ልጅህ ስለሆነ ከእሱ አንድ ብሔር እንዲገኝ አደርጋለሁ።”+ 14  ስለዚህ አብርሃም በማለዳ ተነሳ፤ ለአጋርም ምግብና የውኃ አቁማዳ ሰጣት። እነዚህንም በትከሻዋ አሸከማት፤ ከዚያም ከልጁ ጋር አሰናበታት።+ እሷም ሄደች፤ በቤርሳቤህ+ ምድረ በዳም ትንከራተት ጀመር። 15  በመጨረሻም በአቁማዳው ውስጥ የነበረው ውኃ አለቀ፤ እሷም ልጁን አንዱ ቁጥቋጦ ሥር ጣለችው። 16  ከዚያም “ልጁ ሲሞት ማየት አልፈልግም” ብላ የቀስት ውርወራ ያህል ርቃ ተቀመጠች። እሷም ትጮኽና ታለቅስ ጀመር። 17  በዚህ ጊዜ አምላክ የልጁን ድምፅ ሰማ፤+ የአምላክም መልአክ ከሰማይ አጋርን ጠርቶ እንዲህ አላት፦+ “አጋር፣ ምን ሆነሻል? ልጁ ካለበት ቦታ ሆኖ ሲያለቅስ አምላክ ስለሰማ አይዞሽ አትፍሪ። 18  ተነሽ፣ ልጁንም አንስተሽ በእጅሽ ያዢው፤ ምክንያቱም እኔ ታላቅ ብሔር አደርገዋለሁ።”+ 19  ከዚያም አምላክ ዓይኖቿን ከፈተላት፤ የውኃ ጉድጓድም ተመለከተች። ወደዚያም ሄዳ በአቁማዳው ውኃ ሞላች፤ ልጁንም አጠጣችው። 20  ልጁም እያደገ ሄደ፤ አምላክም ከልጁ+ ጋር ነበር። እሱም የሚኖረው በምድረ በዳ ነበር፤ ቀስተኛም ሆነ። 21  እሱም በፋራን ምድረ በዳ+ ኖረ፤ እናቱም ከግብፅ ምድር ሚስት አመጣችለት። 22  በዚያን ጊዜ አቢሜሌክ ከሠራዊቱ አዛዥ ከፊኮል ጋር ሆኖ አብርሃምን እንዲህ አለው፦ “በምታደርገው ነገር ሁሉ አምላክ ከአንተ ጋር ነው።+ 23  ስለዚህ እኔንም ሆነ ልጆቼንና ዘሮቼን እንደማትክድ እንዲሁም ለእኔም ሆነ ለምትኖርባት ምድር እኔ ያሳየሁህ ዓይነት ታማኝ ፍቅር እንደምታሳይ በአምላክ ስም ማልልኝ።”+ 24  አብርሃምም “እሺ፣ እምላለሁ” አለ። 25  ሆኖም አብርሃም የአቢሜሌክ አገልጋዮች በጉልበት ስለወሰዱት የውኃ ጉድጓድ ለአቢሜሌክ ቅሬታውን ገለጸለት።+ 26  አቢሜሌክም መልሶ “ይህን ያደረገው ማን እንደሆነ አላውቅም፤ አንተም ብትሆን ስለዚህ ጉዳይ አልነገርከኝም፤ ስለዚህ ነገር ያለዛሬ አልሰማሁም” አለው። 27  በዚህ ጊዜ አብርሃም በጎችንና ከብቶችን ወስዶ ለአቢሜሌክ ሰጠው፤ ሁለቱም ቃል ኪዳን ገቡ። 28  አብርሃም ሰባት እንስት በጎችን ከመንጋው ለይቶ ለብቻቸው እንዲሆኑ ባደረገ ጊዜ 29  አቢሜሌክ አብርሃምን “እነዚህን ሰባት እንስት በጎች ለብቻቸው የለየኸው ለምንድን ነው?” አለው። 30  እሱም “ይህን ጉድጓድ የቆፈርኩት እኔ ለመሆኔ ምሥክር እንዲሆን እነዚህን ሰባት እንስት በጎች ከእጄ ውሰድ” አለው። 31  የቦታውን ስም ቤርሳቤህ*+ ብሎ የጠራው በዚህ የተነሳ ነው፤ ምክንያቱም በዚያ ሁለቱ ተማምለዋል። 32  ስለዚህ በቤርሳቤህ ቃል ኪዳን ገቡ፤+ ከዚያም አቢሜሌክ ከሠራዊቱ አዛዥ ከፊኮል ጋር ሆኖ ወደ ፍልስጤማውያን+ ምድር ተመለሰ። 33  ከዚያም በኋላ አብርሃም በቤርሳቤህ የታማሪስክ ዛፍ ተከለ፤ በዚያም የዘላለማዊውን አምላክ+ የይሖዋን ስም ጠራ።+ 34  አብርሃምም በፍልስጤማውያን ምድር ረዘም ላለ ጊዜ* ኖረ።*+

የግርጌ ማስታወሻ

“ይስቅብኛል” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ቃል በቃል “ድምፅዋን።”
“የመሐላው የውኃ ጉድጓድ” ወይም “የሰባት የውኃ ጉድጓድ” ማለት ሳይሆን አይቀርም።
ቃል በቃል “ለብዙ ቀናት።”
ወይም “እንደ ባዕድ አገር ሰው ሆኖ ኖረ።”