ዘፍጥረት 3:1-24

  • ሰው ኃጢአት ውስጥ የወደቀበት ሁኔታ (1-13)

    • የመጀመሪያው ውሸት (4, 5)

  • ይሖዋ በዓመፀኞቹ ላይ ያስተላለፈው ፍርድ (14-24)

    • ስለ ሴቲቱ ዘር የተነገረ ትንቢት (15)

    • ከኤደን ገነት ተባረሩ (23, 24)

3  እባብም+ ይሖዋ አምላክ ከሠራቸው የዱር እንስሳት ሁሉ እጅግ ጠንቃቃ* ነበር። በመሆኑም ሴቲቱን “በእርግጥ አምላክ ‘በአትክልቱ ስፍራ ካለው ከማንኛውም ዛፍ አትብሉ’ ብሏችኋል?”+ ሲል ጠየቃት።  በዚህ ጊዜ ሴቲቱ እባቡን እንዲህ አለችው፦ “በአትክልቱ ስፍራ ካሉት ዛፎች ፍሬ መብላት እንችላለን።+  ይሁንና በአትክልቱ ስፍራ መካከል የሚገኘውን ዛፍ+ ፍሬ በተመለከተ አምላክ ‘ከእሱ አትብሉ፤ ፈጽሞም አትንኩት፤ አለዚያ ትሞታላችሁ’ ብሏል።”  በዚህ ጊዜ እባቡ ሴቲቱን እንዲህ አላት፦ “መሞት እንኳ ፈጽሞ አትሞቱም።+  አምላክ ከዛፉ በበላችሁ ቀን ዓይኖቻችሁ እንደሚገለጡና መልካምና ክፉን በማወቅ ረገድ እንደ አምላክ እንደምትሆኑ+ ስለሚያውቅ ነው።”  በዚህም የተነሳ ሴቲቱ ዛፉ ለመብል መልካም፣ ሲያዩትም የሚያጓጓ እንደሆነ ተመለከተች፤ ዛፉ ለዓይን የሚማርክ ነበር። ስለሆነም ከዛፉ ፍሬ ወስዳ በላች።+ ባሏም አብሯት ሲሆን ለእሱም ሰጠችው፤ እሱም በላ።+  ከዚያም የሁለቱም ዓይኖች ተገለጡ፤ ራቁታቸውን መሆናቸውንም አስተዋሉ። በመሆኑም የበለስ ቅጠል በመስፋት የሚያሸርጡት ነገር ለራሳቸው ሠሩ።+  በኋላም ሰውየውና ሚስቱ ቀኑ ነፋሻማ በሆነበት ጊዜ ላይ ይሖዋ አምላክ በአትክልቱ ስፍራ ውስጥ ሲሄድ ድምፁን ሰሙ፤ እነሱም በአትክልቱ ስፍራ ባሉት ዛፎች መካከል በመግባት ከይሖዋ አምላክ ፊት ተደበቁ።  ይሖዋ አምላክም ሰውየውን በተደጋጋሚ በመጣራት “የት ነህ?” አለው። 10  በመጨረሻም ሰውየው “በአትክልቱ ስፍራ ድምፅህን ሰማሁ፤ ሆኖም ራቁቴን ስለነበርኩ ፈራሁ፤ ስለሆነም ተደበቅኩ” አለ። 11  እሱም “ራቁትህን+ እንደሆንክ ማን ነገረህ? እንዳትበላ ብዬ ካዘዝኩህ ዛፍ+ በላህ?” አለው። 12  ሰውየውም “ከእኔ ጋር እንድትሆን የሰጠኸኝ ይህች ሴት ከዛፉ ፍሬ ሰጠችኝና በላሁ” አለ። 13  ከዚያም ይሖዋ አምላክ ሴቲቱን “ለመሆኑ ይህ ያደረግሽው ነገር ምንድን ነው?” አላት። ሴቲቱም “እባቡ አታለለኝና በላሁ”+ ስትል መለሰች። 14  ከዚያም ይሖዋ አምላክ እባቡን+ እንዲህ አለው፦ “ይህን ስላደረግክ ከቤት እንስሳት ሁሉ እንዲሁም ከዱር እንስሳት ሁሉ የተረገምክ ትሆናለህ። በሕይወትህ ዘመን ሁሉ በሆድህ እየተሳብክ ትሄዳለህ፤ እንዲሁም አፈር ትበላለህ። 15  በአንተና+ በሴቲቱ+ መካከል እንዲሁም በዘርህና+ በዘሯ+ መካከል ጠላትነት+ እንዲኖር አደርጋለሁ፤ እሱ ራስህን ይጨፈልቃል፤*+ አንተም ተረከዙን ታቆስላለህ።”*+ 16  ሴቲቱንም እንዲህ አላት፦ “በእርግዝናሽ ወቅት የሚሰማሽን ሕመም በእጅጉ አበዛለሁ፤ ልጆች የምትወልጂውም በሥቃይ ይሆናል፤ ምኞትሽ ሁሉ ባልሽ ይሆናል፤ እሱ ደግሞ ይገዛሻል።” 17  አዳምንም* እንዲህ አለው፦ “የሚስትህን ቃል ስለሰማህና ‘ከእሱ አትብላ’ ብዬ ካዘዝኩህ ዛፍ+ ወስደህ ስለበላህ በአንተ የተነሳ ምድር የተረገመች ትሁን።+ በሕይወትህ ዘመን ሁሉ የምድርን ፍሬ በሥቃይ ትበላለህ።+ 18  ምድርም እሾህና አሜኬላ ታበቅልብሃለች፤ አንተም በሜዳ ላይ የሚበቅለውን ተክል ትበላለህ። 19  ከመሬት ስለተገኘህ+ ወደ መሬት እስክትመለስ ድረስ ላብህን እያንጠፈጠፍክ ምግብ ትበላለህ። አፈር ስለሆንክ ወደ አፈር ትመለሳለህ።”+ 20  ከዚህ በኋላ አዳም ሚስቱን ሔዋን* ብሎ ጠራት፤ ምክንያቱም እሷ የሕያዋን ሁሉ እናት ትሆናለች።+ 21  ይሖዋ አምላክም ረጅም ልብስ ከቆዳ ሠርቶ አዳምንና ሚስቱን አለበሳቸው።+ 22  ከዚያም ይሖዋ አምላክ እንዲህ አለ፦ “እንግዲህ ሰውየው መልካምና ክፉን በማወቅ ረገድ ከእኛ እንደ አንዱ ሆኗል።+ አሁን ደግሞ እጁን በመዘርጋት ከሕይወት ዛፍ+ ፍሬ ወስዶ እንዳይበላና ለዘላለም እንዳይኖር . . .” 23  ይህን ካለ በኋላም የተገኘበትን መሬት እንዲያርስ፣+ ይሖዋ አምላክ አዳምን ከኤደን የአትክልት ስፍራ+ አባረረው። 24  ሰውየውንም አስወጣው፤ ወደ ሕይወት ዛፍ የሚወስደውንም መንገድ ለመጠበቅ በኤደን የአትክልት ስፍራ በስተ ምሥራቅ በኩል ኪሩቤልና+ ያለማቋረጥ የሚሽከረከር የነበልባል ሰይፍ አስቀመጠ።

የግርጌ ማስታወሻ

ወይም “በጣም መሠሪ፤ እጅግ ተንኮለኛ።”
ወይም “ትመታለህ፤ ትጨፈልቃለህ።”
ወይም “ያቆስላል፤ ይመታል።”
“ምድራዊ ሰው፤ ሰው፤ የሰው ዘር” የሚል ትርጉም አለው።
“ሕያው” የሚል ትርጉም አለው።