ዘፍጥረት 34:1-31

  • ዲና ተደፈረች (1-12)

  • የያዕቆብ ወንዶች ልጆች የተንኮል ድርጊት ፈጸሙ (13-31)

34  ያዕቆብ ከሊያ የወለዳት ዲና+ የተባለችው ልጅ እዚያ አገር ካሉ ወጣት ሴቶች ጋር ጊዜ ለማሳለፍ* ትወጣ ነበር።+  የአገሩ አለቃ የሆነው የሂዋዊው+ የኤሞር ልጅ ሴኬም ዲናን አያት፤ ከዚያም ወሰዳትና አብሯት ተኛ፤ አስገድዶም ደፈራት።  እሱም ልቡ* በያዕቆብ ልጅ በዲና ተማረከ፤ ወጣቷንም አፈቀራት፤ በሚያባብሉ ቃላትም አነጋገራት።*  በመጨረሻም ሴኬም አባቱን ኤሞርን+ “ከዚህች ልጅ ጋር አጋባኝ” አለው።  ያዕቆብ፣ ሴኬም ልጁን ዲናን እንዳስነወራት በሰማ ጊዜ ወንዶች ልጆቹ በመስክ መንጎቹን እየጠበቁ ነበር። በመሆኑም ያዕቆብ ልጆቹ እስኪመለሱ ድረስ ዝም አለ።  በኋላም የሴኬም አባት ኤሞር ከያዕቆብ ጋር ለመነጋገር ወጣ።  ሆኖም የያዕቆብ ወንዶች ልጆች ስለ ሁኔታው ሰሙ፤ ወዲያውኑም ከመስክ መጡ። ሴኬም የያዕቆብን ሴት ልጅ በመድፈር ፈጽሞ መደረግ የማይገባውን ድርጊት ስለፈጸመና+ በዚህም እስራኤልን ስላዋረደ በጣም ተበሳጩ፤ እጅግም ተቆጡ።+  ኤሞርም እንዲህ አላቸው፦ “ልጄ ሴኬም ልጃችሁን በጣም ወዷታል።* እባካችሁ ሚስት እንድትሆነው ስጡት፤  በጋብቻም እንዛመድ። ሴቶች ልጆቻችሁን ዳሩልን፤ የእኛንም ሴቶች ልጆች አግቡ።+ 10  አብራችሁንም መኖር ትችላላችሁ፤ አገራችን አገራችሁ ናት። ኑሩባት፤ ነግዱባት፤ ሀብትም አፍሩባት።” 11  ከዚያም ሴኬም አባቷንና ወንድሞቿን እንዲህ አላቸው፦ “በፊታችሁ ሞገስ ላግኝ እንጂ የምትጠይቁኝን ሁሉ እሰጣለሁ። 12  ብዙ ጥሎሽና ስጦታ ልትጠይቁኝ ትችላላችሁ።+ እኔ የጠየቃችሁኝን ሁሉ ለመስጠት ፈቃደኛ ነኝ። ብቻ ይህችን ወጣት ሚስቴ እንድትሆን ስጡኝ።” 13  የያዕቆብ ወንዶች ልጆችም ሴኬም እህታቸውን ዲናን ስላስነወረ ለእሱና ለአባቱ ለኤሞር ተንኮል ያዘለ መልስ ሰጧቸው። 14  እንዲህም አሏቸው፦ “እንዲህ ያለ ነገር ፈጽሞ አናደርግም፤ እህታችንን ላልተገረዘ ሰው አንሰጥም፤+ ምክንያቱም ይህ ለእኛ ውርደት ነው። 15  በሐሳባችሁ የምንስማማው እኛን ከመሰላችሁና የእናንተ የሆነው ወንድ ሁሉ እንዲገረዝ ካደረጋችሁ ብቻ ነው።+ 16  ከዚያም ሴቶች ልጆቻችንን እንድርላችኋለን፤ እኛም ሴቶች ልጆቻችሁን እናገባለን፤ አብረናችሁም እንኖራለን፤ አንድ ሕዝብም እንሆናለን። 17  የምንላችሁን የማትሰሙና ለመገረዝ ፈቃደኛ የማትሆኑ ከሆነ ግን ልጃችንን ይዘን እንሄዳለን።” 18  የተናገሩትም ነገር ኤሞርንና+ ልጁን ሴኬምን+ ደስ አሰኛቸው። 19  ወጣቱም ያሉትን ነገር ለማድረግ ጊዜ አልወሰደበትም፤+ ምክንያቱም የያዕቆብን ልጅ ወዷት ነበር፤ ደግሞም በአባቱ ቤት ካሉት ሰዎች ሁሉ እጅግ የተከበረ ነበር። 20  በመሆኑም ኤሞርና ልጁ ሴኬም ወደ ከተማዋ በር በመሄድ በከተማቸው የሚኖሩትን ወንዶች+ እንዲህ አሏቸው፦ 21  “እነዚህ ሰዎች ከእኛ ጋር በሰላም መኖር ይፈልጋሉ። ምድሪቱ ለእነሱም ስለምትበቃ በምድሪቱ ይኑሩ፤ እንዲሁም ይነግዱ። ሴቶች ልጆቻቸውን ማግባት፣ የእኛንም ሴቶች ልጆች ለእነሱ መዳር እንችላለን።+ 22  ሆኖም ሰዎቹ ከእኛ ጋር አንድ ሕዝብ በመሆን አብረውን ለመኖር የሚስማሙት፣ ልክ እነሱ እንደተገረዙት የእኛ የሆኑ ወንዶች ሁሉ የሚገረዙ ከሆነ ብቻ ነው።+ 23  እንዲህ ብናደርግ ንብረታቸው፣ ሀብታቸውና ከብቶቻቸው ሁሉ የእኛ ሆኑ ማለት አይደለም? በመሆኑም ከእኛ ጋር ለመኖር ባቀረቡት ሐሳብ እንስማማ።” 24  በከተማው በር የሚወጡ ሁሉ ኤሞርና ልጁ ሴኬም ያሏቸውን ሰሙ፤ በከተማዋም በር የሚወጡ ወንዶች በሙሉ ተገረዙ። 25  ሆኖም በሦስተኛው ቀን፣ ሰዎቹ ገና ቆስለው እያሉ የዲና ወንድሞች+ የሆኑት ሁለቱ የያዕቆብ ልጆች ማለትም ስምዖንና ሌዊ ማንም ሳይጠረጥራቸው ሰይፋቸውን ይዘው ወደ ከተማዋ በመግባት ወንዶቹን ሁሉ ገደሉ።+ 26  ኤሞርንና ልጁን ሴኬምን በሰይፍ ገደሏቸው፤ ከዚያም ዲናን ከሴኬም ቤት ይዘው ሄዱ። 27  ሌሎቹ የያዕቆብ ወንዶች ልጆችም በሬሳ ላይ እየተረማመዱ ከተማዋን ዘረፉ፤ ይህን ያደረጉትም እህታቸው ስለተነወረች ነው።+ 28  እነሱም መንጎቻቸውን፣ ከብቶቻቸውን፣ አህዮቻቸውን እንዲሁም በከተማዋ ውስጥና በመስክ ያገኙትን ሁሉ ወሰዱ። 29  በተጨማሪም ንብረቶቻቸውን በሙሉ ወሰዱ፤ እንዲሁም ትናንሽ ልጆቻቸውንና ሚስቶቻቸውን ማረኩ፤ በየቤቱ ያገኙትን ሁሉ ዘረፉ። 30  በዚህ ጊዜ ያዕቆብ፣ ስምዖንንና ሌዊን+ እንዲህ አላቸው፦ “በዚህች አገር በሚኖሩት በከነአናውያንና በፈሪዛውያን ዘንድ እንደ ጥምብ እንድቆጠር በማድረግ ከፍተኛ ችግር ውስጥ ከተታችሁኝ።* እኔ እንግዲህ በቁጥር አነስተኛ ነኝ፤ እነሱም በእኔ ላይ ጥቃት ለመሰንዘር ግንባር ፈጥረው መምጣታቸው አይቀርም፤ በዚህም የተነሳ እኔም ሆንኩ ቤቴ እንጠፋለን።” 31  እነሱ ግን “ታዲያ ማንም እህታችንን እንደ ዝሙት አዳሪ ቆጥሮ እንዲህ ያለ ድርጊት ይፈጽምባት?” አሉ።

የግርጌ ማስታወሻ

ወይም “በዚያ አገር ያሉ ወጣት ሴቶችን ለማየት።”
ወይም “ነፍሱ።”
ቃል በቃል “ለወጣቷ ልብ ተናገረ።”
ወይም “የልጄ የሴኬም ነፍስ ከልጃችሁ ጋር ተጣብቋል።”
ወይም “እንድገለል አደረጋችሁኝ።”