ዘፍጥረት 37:1-36

  • የዮሴፍ ሕልሞች (1-11)

  • ዮሴፍና ቅናት ያደረባቸው ወንድሞቹ (12-24)

  • ዮሴፍ ለባርነት ተሸጠ (25-36)

37  ያዕቆብ አባቱ የባዕድ አገር ሰው ሆኖ ይኖርበት በነበረው በከነአን ምድር ኖረ።+  የያዕቆብ ታሪክ ይህ ነው። ዮሴፍ+ የ17 ዓመት ወጣት ሳለ ከአባቱ ሚስቶች ከባላና ከዚልጳ ወንዶች ልጆች+ ጋር በጎች ይጠብቅ+ ነበር። እሱም ስለ ወንድሞቹ መጥፎ ድርጊት የሚገልጽ ወሬ ለአባታቸው ይዞለት መጣ።  እስራኤል ዮሴፍን የወለደው በስተርጅናው ስለነበር ከሌሎቹ ወንዶች ልጆቹ ሁሉ+ ይበልጥ ይወደው ነበር፤ ለእሱም ልዩ የሆነ ቀሚስ* አሠራለት።  ወንድሞቹም አባታቸው ከእነሱ አስበልጦ እንደሚወደው ሲያዩ ይጠሉት ጀመር፤ በሰላምም ሊያናግሩት አልቻሉም።  በኋላም ዮሴፍ ሕልም አለመ፤ ሕልሙንም ለወንድሞቹ ነገራቸው፤+ እነሱም እሱን የሚጠሉበት ተጨማሪ ምክንያት አገኙ።  እሱም እንዲህ አላቸው፦ “እባካችሁ ያየሁትን ሕልም ልንገራችሁ፣ ስሙኝ።  በእርሻ መካከል ነዶ እያሰርን ነበር፤ ከዚያም የእኔ ነዶ ተነስታ ቀጥ ብላ ስትቆም የእናንተ ነዶዎች ደግሞ የእኔን ነዶ ከበው ሰገዱላት።”+  ወንድሞቹም “በእኛ ላይ ንጉሥ ልትሆንና ልትገዛን ታስባለህ ማለት ነው?” አሉት።+ በመሆኑም ያየው ሕልምና የተናገረው ነገር እሱን ይበልጥ እንዲጠሉት አደረጋቸው።  ከዚያም ሌላ ሕልም አለመ፤ ሕልሙንም ለወንድሞቹ እንዲህ ሲል ነገራቸው፦ “ሌላም ሕልም አለምኩ። አሁን ደግሞ ፀሐይ፣ ጨረቃና 11 ከዋክብት ሲሰግዱልኝ አየሁ።”+ 10  ሕልሙንም ለአባቱና ለወንድሞቹ ነገራቸው፤ አባቱም ገሠጸው፤ እንዲህም አለው፦ “ይህ ያለምከው ሕልም ፍቺ ምንድን ነው? እኔም ሆንኩ እናትህና ወንድሞችህ መጥተን መሬት ላይ ተደፍተን እንድንሰግድልህ ታስባለህ?” 11  ወንድሞቹም ይበልጥ ቀኑበት፤+ አባቱ ግን ነገሩን በልቡ ያዘው። 12  ወንድሞቹ የአባታቸውን መንጋ ለማሰማራት ሴኬም+ አቅራቢያ ወደሚገኝ ቦታ ሄደው ነበር። 13  በኋላም እስራኤል ዮሴፍን “ወንድሞችህ በሴኬም አቅራቢያ መንጎቹን እየጠበቁ እንዳሉ አውቀሃል አይደል? በል ና፣ ወደ እነሱ ልላክህ” አለው። እሱም “እሺ፣ እሄዳለሁ!” አለ። 14  በመሆኑም “እባክህ ሂድና ወንድሞችህ ደህና መሆናቸውን እይ። መንጋውም ደህና መሆኑን እይና መጥተህ ትነግረኛለህ” አለው። በዚህም መሠረት ከኬብሮን+ ሸለቆ* ወደዚያ ላከው፤ ዮሴፍም ወደ ሴኬም ሄደ። 15  በኋላም ዮሴፍ በሜዳ ላይ ሲባዝን አንድ ሰው አገኘው። ሰውየውም “ምን ፈልገህ ነው?” ሲል ጠየቀው። 16  እሱም “ወንድሞቼን እየፈለግኩ ነው። መንጎቹን እየጠበቁ ያሉት የት እንደሆነ እባክህ ንገረኝ” አለው። 17  ሰውየውም “ከዚህ ሄደዋል፤ ምክንያቱም ‘ወደ ዶታን እንሂድ’ ሲባባሉ ሰምቻቸዋለሁ” አለው። ስለዚህ ዮሴፍ ወንድሞቹን ፍለጋ ሄደ፤ ዶታን ላይም አገኛቸው። 18  እነሱም ከሩቅ ሲመጣ ተመለከቱት፤ አጠገባቸውም ከመድረሱ በፊት እሱን እንዴት እንደሚገድሉት ይመካከሩ ጀመር። 19  እነሱም እንዲህ ተባባሉ፦ “ያውና! ያ ሕልም አላሚ መጣ።+ 20  ኑ፣ እንግደለውና ከውኃ ጉድጓዶቹ በአንዱ ውስጥ እንጣለው፤ ከዚያም ኃይለኛ አውሬ በልቶታል እንላለን። እስቲ የሕልሞቹን መጨረሻ እናያለን።” 21  ሮቤል+ ይህን ሲሰማ ከእነሱ ሊያስጥለው አሰበ፤ በመሆኑም “ሕይወቱን* እንኳ አናጥፋ”+ አለ። 22  ከዚያም እንዲህ አላቸው፦ “ደም አታፍስሱ።+ በምድረ በዳ በሚገኘው በዚህ የውኃ ጉድጓድ ውስጥ ጣሉት እንጂ ጉዳት አታድርሱበት።”*+ ይህን ያላቸው ከእነሱ ሊያስጥለውና ወደ አባቱ ሊመልሰው አስቦ ነበር። 23  ዮሴፍ ወደ ወንድሞቹ እንደደረሰም የለበሰውን ያን ልዩ ቀሚስ+ ገፈፉት፤ 24  ወስደውም የውኃ ጉድጓዱ ውስጥ ጣሉት። ጉድጓዱም ባዶ ነበር፤ ውኃም አልነበረበትም። 25  ከዚያም ሊበሉ ተቀመጡ። ቀና ብለው ሲመለከቱም እስማኤላውያን+ ነጋዴዎች ግመሎቻቸውን አግተልትለው ከጊልያድ ሲመጡ አዩ። እነሱም በግመሎቻቸው ላይ ጥሩ መዓዛ ያለው ሙጫ፣ በለሳንና ከርቤ+ ጭነው ወደ ግብፅ እየወረዱ ነበር። 26  በዚህ ጊዜ ይሁዳ ወንድሞቹን እንዲህ አላቸው፦ “ወንድማችንን ብንገድለውና ደሙን ብንሸሽግ ምን እንጠቀማለን?+ 27  ኑ፣ ለእስማኤላውያን እንሽጠው፤+ እጃችንን አንሰንዝርበት። ደግሞም እኮ እሱ ወንድማችን፣ የገዛ ሥጋችን ነው።” እነሱም በወንድማቸው ሐሳብ ተስማሙ። 28  ምድያማውያን+ ነጋዴዎች በአጠገባቸው ሲያልፉም ዮሴፍን ከውኃ ጉድጓዱ አውጥተው በ20 የብር ሰቅል ለእስማኤላውያን ሸጡት።+ እነሱም ዮሴፍን ወደ ግብፅ ወሰዱት። 29  በኋላም ሮቤል ወደ ውኃ ጉድጓዱ ተመልሶ ዮሴፍ በዚያ አለመኖሩን ሲመለከት ልብሱን ቀደደ። 30  ወደ ወንድሞቹም ተመልሶ “ልጁ የለም! እንግዲህ ምንድን ነው የማደርገው?” አላቸው። 31  ስለዚህ የዮሴፍን ቀሚስ ወሰዱ፤ አንድ ፍየል ካረዱ በኋላም ቀሚሱን ደሙ ውስጥ ነከሩት። 32  ከዚያም ያን ልዩ ቀሚስ እንዲህ ከሚል መልእክት ጋር ወደ አባታቸው ላኩት፦ “ይህን አገኘን፤ እባክህ ይህ የልጅህ ቀሚስ መሆን አለመሆኑን እስቲ እየው።”+ 33  እሱም ልብሱን አገላብጦ ካየው በኋላ “ይሄማ የልጄ ቀሚስ ነው! ኃይለኛ አውሬ በልቶት መሆን አለበት! በቃ ዮሴፍን አውሬ ቦጫጭቆታል ማለት ነው!” አለ። 34  ከዚያም ያዕቆብ ልብሱን ቀደደ፤ በወገቡም ላይ ማቅ ታጥቆ ለብዙ ቀናት ለልጁ አለቀሰ። 35  ወንዶችና ሴቶች ልጆቹ ሁሉ ሊያጽናኑት ሞከሩ፤ እሱ ግን ፈጽሞ ሊጽናና አልቻለም፤ “በልጄ ሐዘን እንደተቆራመድኩ ወደ መቃብር* እወርዳለሁ!”+ ይል ነበር። አባቱም ለልጁ ማልቀሱን አላቋረጠም። 36  በዚህ ጊዜ ምድያማውያን ዮሴፍን ግብፅ ውስጥ ጶጢፋር ለተባለ ሰው ሸጡት፤ ይህ ሰው የፈርዖን የቤተ መንግሥት ባለሥልጣንና+ የዘቦች አለቃ+ ነበር።

የግርጌ ማስታወሻ

ወይም “የሚያምር ረጅም ልብስ።”
ወይም “ረባዳማ ሜዳ።”
ወይም “ነፍሱን።”
ወይም “እጃችሁን አታሳርፉበት።”
ወይም “ሲኦል።” የሰው ልጆችን ሁሉ መቃብር ያመለክታል። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።