ዘፍጥረት 4:1-26

  • ቃየንና አቤል (1-16)

  • የቃየን ዘሮች (17-24)

  • ሴትና ልጁ ሄኖስ (25, 26)

4  አዳምም ከሚስቱ ከሔዋን ጋር የፆታ ግንኙነት ፈጸመ፤ እሷም ፀነሰች።+ ቃየንንም+ በወለደች ጊዜ “በይሖዋ እርዳታ ወንድ ልጅ አፈራሁ”* አለች።  በኋላም ወንድሙን አቤልን+ ወለደች። አቤል የበግ እረኛ ሆነ፤ ቃየን ግን አራሽ ሆነ።  ከጊዜ በኋላም ቃየን የተወሰኑ የምድር ፍሬዎችን ለይሖዋ መባ አድርጎ አቀረበ።  አቤል ግን ከመንጋው በኩራት+ መካከል የተወሰኑትን ከነስባቸው አቀረበ። ይሖዋ አቤልንና ያቀረበውን መባ+ በጥሩ ፊት ሲመለከት  ቃየንንና ያቀረበውን መባ ግን በጥሩ ፊት አልተመለከተም። በመሆኑም ቃየን በጣም ተናደደ፤ እጅግ አዘነ።  ከዚያም ይሖዋ ቃየንን እንዲህ አለው፦ “ለምን ተናደድክ? ለምንስ አዘንክ?  መልካም ወደ ማድረግ ብታዘነብል ኖሮ ሞገስ አታገኝም ነበር?* መልካም ወደ ማድረግ ካላዘነበልክ ግን ኃጢአት በደጅህ እያደባ ነው፤ ሊቆጣጠርህም ይፈልጋል፤ ታዲያ አንተ ትቆጣጠረው ይሆን?”  ከዚያ በኋላ ቃየን ወንድሙን አቤልን “ና ወደ ሜዳ እንሂድ” አለው። በሜዳው ላይ ሳሉም ቃየን ወንድሙን አቤልን ደብድቦ ገደለው።+  በኋላም ይሖዋ ቃየንን “ወንድምህ አቤል የት ነው?” አለው፤ እሱም “እኔ አላውቅም። እኔ የወንድሜ ጠባቂ ነኝ?” አለ። 10  በዚህ ጊዜ እንዲህ አለው፦ “ያደረግከው ነገር ምንድን ነው? ስማ! የወንድምህ ደም ከምድር ወደ እኔ እየጮኸ ነው።+ 11  እንግዲህ የወንድምህን ደም ከእጅህ ለመቀበል+ አፏን ከከፈተችው ምድር እንድትሰደድ ተረግመሃል። 12  ምድርን በምታርስበትም ጊዜ ምርቷን* አትሰጥህም። በምድር ላይ ተንከራታችና ስደተኛ ትሆናለህ።” 13  በዚህ ጊዜ ቃየን ይሖዋን እንዲህ አለው፦ “ለሠራሁት ጥፋት የምቀበለው ቅጣት ልሸከመው ከምችለው በላይ ነው። 14  ይኸው በዚህ ቀን ከምድሪቱ* ልታባርረኝ ነው፤ ከፊትህም እሰወራለሁ፤ እንዲሁም በምድር ላይ ተንከራታችና ስደተኛ እሆናለሁ፤ እንግዲህ በቃ፣ ያገኘኝ ሁሉ ይገድለኛል።” 15  ስለሆነም ይሖዋ “እንግዲያው ቃየንን የሚገድል ማንኛውም ሰው ሰባት እጥፍ የበቀል ቅጣት ይቀበላል” አለው። በመሆኑም ያገኘው ማንም እንዳይገድለው ይሖዋ ለቃየን ምልክት አደረገለት።* 16  ከዚያም ቃየን ከይሖዋ ፊት ርቆ ሄደ፤ ከኤደን በስተ ምሥራቅ+ በሚገኘው በግዞት ምድር* መኖር ጀመረ። 17  ከዚህ በኋላ ቃየን ከሚስቱ+ ጋር የፆታ ግንኙነት ፈጸመ፤ እሷም ፀነሰች፤ ሄኖክንም ወለደች። ከዚያም ቃየን ከተማ መገንባት ጀመረ፤ ከተማዋንም በልጁ በሄኖክ ስም ሰየማት። 18  ከጊዜ በኋላም ሄኖክ ኢራድን ወለደ። ኢራድም መሁያኤልን ወለደ፤ መሁያኤልም መቱሻኤልን ወለደ፤ መቱሻኤል ደግሞ ላሜህን ወለደ። 19  ላሜህም ሁለት ሚስቶች አገባ፤ የመጀመሪያዋ ስም አዳ ሲሆን የሁለተኛዋ ስም ደግሞ ጺላ ነበር። 20  አዳ ያባልን ወለደች። ያባል በድንኳን የሚኖሩና ከብት የሚያረቡ ሰዎች አባት ነበር። 21  የወንድሙ ስም ዩባል ነበር። እሱም የበገና ደርዳሪዎችና የእምቢልታ* ነፊዎች አባት ነበር። 22  ጺላ ደግሞ ቱባልቃይንን ወለደች፤ እሱም መዳብና ብረት እየቀጠቀጠ የተለያዩ መሣሪያዎችን ይሠራ ነበር። የቱባልቃይን እህት ናዕማ ትባል ነበር። 23  ከዚያም ላሜህ ለሚስቶቹ ለአዳና ለጺላ የሚከተለውን ተቀኘ፦ “እናንተ የላሜህ ሚስቶች፣ ቃሌን ስሙ፤የምላችሁንም አዳምጡ፦ አንድ ሰው ስላቆሰለኝ፣አዎ፣ አንድ ወጣት ስለመታኝ ገደልኩት። 24  ቃየንን የሚገድል 7 እጥፍ የበቀል ቅጣት+ የሚደርስበት ከሆነላሜህን የገደለማ 77 ጊዜ የበቀል ቅጣት ይደርስበታል።” 25  አዳም ከሚስቱ ጋር በድጋሚ የፆታ ግንኙነት ፈጸመ፤ እሷም ወንድ ልጅ ወለደች። ስሙንም “ቃየን አቤልን ስለገደለው+ በእሱ ፋንታ አምላክ ሌላ ዘር ተክቶልኛል” በማለት ሴት*+ አለችው። 26  ሴት ደግሞ ወንድ ልጅ ወለደ፤ ስሙንም ሄኖስ+ አለው። በዚያን ዘመን ሰዎች የይሖዋን ስም መጥራት ጀመሩ።*

የግርጌ ማስታወሻ

ወይም “ወለድኩ።”
ወይም “ሐሴት ታደርግ አልነበረም?”
ቃል በቃል “ኃይሏን።”
ቃል በቃል “ከምድር ገጽ።”
ወይም “አበጀለት።”
ወይም “በኖድ ምድር።”
ወይም “የዋሽንት።”
“የተሾመ፤ የተቀመጠ፤ የተመደበ” የሚል ትርጉም አለው።
ወይም “ሰዎች የይሖዋን ስም ማቃለል ጀመሩ።”