ዘፍጥረት 43:1-34

  • የዮሴፍ ወንድሞች ቢንያምን ይዘው ለሁለተኛ ጊዜ ወደ ግብፅ ሄዱ (1-14)

  • ዮሴፍ በድጋሚ ከወንድሞቹ ጋር ተገናኘ (15-23)

  • ዮሴፍ ከወንድሞቹ ጋር በማዕድ ተቀመጠ (24-34)

43  ረሃቡ በምድሪቱ ላይ በርትቶ ነበር።+  ስለሆነም ከግብፅ ያመጡትን እህል በልተው ሲጨርሱ+ አባታቸው “ተመልሳችሁ ሂዱና ጥቂት እህል ግዙልን” አላቸው።  በዚህ ጊዜ ይሁዳ እንዲህ አለው፦ “ሰውየው ‘ወንድማችሁን ይዛችሁት ካልመጣችሁ በምንም ዓይነት ዳግመኛ ፊቴን አታዩም’ በማለት በግልጽ አስጠንቅቆናል።+  ወንድማችንን ከእኛ ጋር የምትልከው ከሆነ ወደዚያ ወርደን እህል እንገዛልሃለን።  እሱን የማትልከው ከሆነ ግን ወደዚያ አንወርድም፤ ምክንያቱም ሰውየው ‘ወንድማችሁን ይዛችሁት ካልመጣችሁ በምንም ዓይነት ዳግመኛ ፊቴን አታዩም’ ብሎናል።”+  እስራኤልም+ “ምነው እንዲህ ላለ ችግር ዳረጋችሁኝ? ሌላ ወንድም እንዳላችሁ ለምን ለሰውየው ነገራችሁት?” አላቸው።  እነሱም እንዲህ አሉት፦ “ሰውየው ‘አባታችሁ አሁንም በሕይወት አለ? ሌላስ ወንድም አላችሁ?’ በማለት በቀጥታ ስለ እኛና ስለ ዘመዶቻችን ጠየቀን፤ እኛም ለጥያቄው መልስ ሰጠነው።+ ታዲያ ‘ወንድማችሁን ይዛችሁ ኑ’ ይለናል ብለን እንዴት ልንጠረጥር እንችላለን?”+  ከዚያም ይሁዳ አባቱን እስራኤልን እንዲህ በማለት ለመነው፦ “እኛም ሆን አንተ እንዲሁም ትናንሽ ልጆቻችን+ በረሃብ ከምናልቅ፣ በሕይወት እንድንተርፍ+ ልጁ ከእኔ ጋር እንዲሄድ ፍቀድና+ ተነስተን ወደዚያ እንሂድ።  የልጁን ደህንነት በተመለከተ ኃላፊነቱን እኔ እወስዳለሁ።*+ አንድ ነገር ቢሆን እኔን ተጠያቂ ልታደርገኝ ትችላለህ። ልጁን ወደ አንተ መልሼ ባላመጣውና ባላስረክብህ በሕይወቴ ሙሉ በፊትህ በደለኛ ልሁን። 10  ዝም ብለን ጊዜ ባናጠፋ ኖሮ እስካሁን ሁለት ጊዜ እዚያ ደርሰን በተመለስን ነበር።” 11  በመሆኑም አባታቸው እስራኤል እንዲህ አላቸው፦ “እንግዲህ ሌላ አማራጭ ከጠፋ እንዲህ አድርጉ፦ ምድሪቱ ከምታፈራቸው ምርጥ ነገሮች መካከል ጥቂት በለሳን፣+ ጥቂት ማር፣ ጥሩ መዓዛ ያለው ሙጫ፣ ከርቤ፣+ ለውዝና አልሞንድ ለሰውየው ስጦታ+ እንዲሆን በከረጢቶቻችሁ ይዛችሁ ውረዱ። 12  በተጨማሪም እጥፍ ገንዘብ ያዙ፤ በከረጢቶቻችሁ አፍ ላይ ተደርጎ የተመለሰላችሁንም ገንዘብ ይዛችሁ ሂዱ።+ ምናልባት በስህተት የመጣ ሊሆን ይችላል። 13  በሉ ተነሱና ወንድማችሁን ይዛችሁ ወደ ሰውየው ሂዱ። 14  ሌላውን ወንድማችሁንና ቢንያምን እንዲለቅላችሁ ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ የሰውየውን ልብ ያራራላችሁ። እንግዲህ ልጆቼን አጥቼ ለሐዘን ከተዳረግኩም ምን አደርጋለሁ፤ የመጣውን እቀበላለሁ!”+ 15  ስለዚህ ሰዎቹ ይህን ስጦታና እጥፍ ገንዘብ እንዲሁም ቢንያምን ይዘው ተነሱ። ወደ ግብፅም ወረዱ፤ እንደገናም ዮሴፍ ፊት ቀረቡ።+ 16  ዮሴፍ ቢንያምን ከእነሱ ጋር ሲያየው የቤቱ ኃላፊ የሆነውን ሰው ወዲያውኑ እንዲህ አለው፦ “ሰዎቹን ወደ ቤት ውሰዳቸው፤ አብረውኝ ምሳ ስለሚበሉ እንስሳ አርደህ ምግብ አዘጋጅ።” 17  ሰውየውም ወዲያውኑ ልክ ዮሴፍ እንዳለው አደረገ፤+ ሰዎቹንም ወደ ዮሴፍ ቤት ወሰዳቸው። 18  ሰዎቹ ግን ወደ ዮሴፍ ቤት ሲወሰዱ ፈሩ፤ እንዲህም ይሉ ጀመር፦ “ወደዚህ ያመጡን ባለፈው ጊዜ በከረጢቶቻችን ውስጥ በተመለሰው ገንዘብ የተነሳ ነው። በቃ አሁን ያሠቃዩናል፤ ባሪያ ያደርጉናል፤ አህዮቻችንንም ይቀሙናል!”+ 19  በመሆኑም የዮሴፍ ቤት ኃላፊ ወደሆነው ሰው ቀርበው በቤቱ በራፍ ላይ አነጋገሩት። 20  እነሱም እንዲህ አሉት፦ “ይቅርታ ጌታዬ! እኛ ባለፈው ጊዜ ወደዚህ የመጣነው እህል ለመግዛት ነበር።+ 21  ሆኖም የምናርፍበት ቦታ ደርሰን ከረጢቶቻችንን ስንከፍት የእያንዳንዳችንን ገንዘብ ምንም ሳይጎድል በየከረጢታችን አፍ ላይ አገኘነው።+ ስለዚህ ራሳችን ገንዘቡን መመለስ እንፈልጋለን። 22  እህል ለመግዛት ተጨማሪ ገንዘብ ይዘናል። ገንዘባችንን በከረጢታችን ውስጥ መልሶ ያስቀመጠው ማን እንደሆነ አናውቅም።”+ 23  እሱም “አይዟችሁ፣ አትፍሩ። ይህን ገንዘብ በከረጢቶቻችሁ ውስጥ ያስቀመጠላችሁ የእናንተ አምላክና የአባታችሁ አምላክ ነው። እኔ እንደሆነ ገንዘባችሁ ደርሶኛል” አላቸው። ከዚያም ስምዖንን አውጥቶ ወደ እነሱ አመጣው።+ 24  ከዚያም ሰውየው ሰዎቹን ወደ ዮሴፍ ቤት አስገባቸው፤ እግራቸውን እንዲታጠቡም ውኃ አቀረበላቸው፤ እንዲሁም ለአህዮቻቸው ገፈራ ሰጣቸው። 25  እነሱም እዚያው ምሳ እንደሚበሉ+ ስለሰሙ ዮሴፍ ቀትር ላይ ሲመጣ የሚሰጡትን ስጦታ+ ማዘገጃጀት ጀመሩ። 26  ዮሴፍ ወደ ቤት ሲገባ፣ ያዘጋጁትን ስጦታ ይዘው ወደ እሱ በመግባት አበረከቱለት፤ መሬት ላይም ተደፍተው ሰገዱለት።+ 27  ከዚያም ስለ ደህንነታቸው ጠየቃቸው፤ እንዲህም አላቸው፦ “ባለፈው ጊዜ የነገራችሁኝ አረጋዊ አባታችሁ ደህና ነው? አሁንም በሕይወት አለ?”+ 28  እነሱም “አገልጋይህ አባታችን ደህና ነው። አሁንም በሕይወት አለ” አሉት። ከዚያም መሬት ላይ ተደፍተው ሰገዱ።+ 29  ዮሴፍም ቀና ብሎ ሲመለከት የእናቱን ልጅ ወንድሙን+ ቢንያምን አየ፤ እሱም “ባለፈው ጊዜ ስለ እሱ የነገራችሁኝ ትንሹ ወንድማችሁ ይሄ ነው?” አላቸው።+ ቢንያምንም “የእኔ ልጅ፣ አምላክ ሞገሱን ያሳይህ” አለው። 30  ዮሴፍ ወንድሙን ሲያይ ስሜቱን መቆጣጠር ስላቃተው በፍጥነት ወጣ፤ የሚያለቅስበትንም ቦታ ፈለገ። ብቻውን ወደ አንድ ክፍል ገብቶም አለቀሰ።+ 31  ከዚያም ፊቱን ተጣጥቦ ወጣ፤ እንደ ምንም ስሜቱን ተቆጣጥሮም “ምግብ ይቅረብ” አለ። 32  እነሱም ለዮሴፍ ለብቻው አቀረቡለት፤ ለእነሱም ለብቻቸው አቀረቡላቸው። እንዲሁም በቤቱ ለሚበሉት ግብፃውያን ለብቻቸው አቀረቡላቸው። ይህን ያደረጉት ግብፃውያን ከዕብራውያን ጋር አብረው ምግብ ስለማይበሉ ነው፤ ምክንያቱም ይህ ለግብፃውያን አስጸያፊ ነገር ነው።+ 33  ወንድማማቾቹም* የበኩሩ እንደ ብኩርና መብቱ፣+ ታናሹም እንደ ታናሽነቱ በፊቱ ተቀመጡ፤ እርስ በርሳቸውም በመገረም ይተያዩ ነበር። 34  እሱም ፊቱ ከቀረበው ምግብ እየተነሳ ለእነሱ እንዲሰጣቸው ያደርግ ነበር፤ የቢንያም ድርሻ ግን ከሌሎቹ አምስት እጥፍ እንዲበልጥ ያደርግ ነበር።+ እነሱም እስኪጠግቡ ድረስ አብረውት በሉ፣ ጠጡም።

የግርጌ ማስታወሻ

ወይም “ለእሱ ዋስ እሆናለሁ።”
ቃል በቃል “እነሱም።”