ዘፍጥረት 44:1-34

  • የዮሴፍ የብር ጽዋ በቢንያም ከረጢት ውስጥ ተገኘ (1-17)

  • ይሁዳ ስለ ቢንያም ተማጸነ (18-34)

44  ከዚህ በኋላ ዮሴፍ የቤቱ ኃላፊ የሆነውን ሰው እንዲህ ሲል አዘዘው፦ “የቻሉትን ያህል እህል በየከረጢቶቻቸው ሙላላቸው፤ የእያንዳንዳቸውንም ገንዘብ በየከረጢቶቻቸው አፍ ላይ አድርገው።+  ሆኖም የእኔን ጽዋ ይኸውም የብር ጽዋዬን ውሰድና እህል ለመግዛት ካመጣው ገንዘብ ጋር አድርገህ በትንሹ ወንድማቸው ከረጢት አፍ ላይ አድርገው።” እሱም ልክ ዮሴፍ እንዳዘዘው አደረገ።  ሰዎቹም ማለዳ ላይ ጎህ ሲቀድ ከነአህዮቻቸው ተሸኙ።  እነሱም ከከተማዋ ብዙም ርቀው ሳይሄዱ ዮሴፍ የቤቱ ኃላፊ የሆነውን ሰው እንዲህ አለው፦ “ተነስ! ሰዎቹን ተከታተላቸው! ስትደርስባቸውም እንዲህ በላቸው፦ ‘ለተደረገላችሁ መልካም ነገር ክፉ የመለሳችሁት ለምንድን ነው?  ይህ ጌታዬ የሚጠጣበትና የሚጠነቁልበት ጽዋ አይደለም? የፈጸማችሁት ድርጊት በጣም አሳፋሪ ነው።’”  እሱም ተከታትሎ ደረሰባቸውና ልክ እንደተባለው አላቸው።  እነሱ ግን እንዲህ አሉት፦ “ጌታዬ እንዲህ ያለ ነገር የሚናገረው ለምንድን ነው? አገልጋዮችህ እንዲህ ያለ ነገር ያደርጋሉ ማለት ፈጽሞ የማይታሰብ ነው።  በከረጢቶቻችን አፍ ላይ ያገኘነውን ገንዘብ እንኳ ከከነአን ምድር ድረስ ይዘን ወደ አንተ መጥተን የለም?+ ታዲያ ከጌታህ ቤት ብር ወይም ወርቅ እንዴት እንሰርቃለን?  ከእኛ ከባሪያዎችህ መካከል የተገኘበት ቢኖር ያ ሰው ይገደል፤ የቀረነውም ለጌታዬ ባሪያዎች እንሆናለን።” 10  እሱም “እሺ፣ እንዳላችሁት ይሁን፤ ጽዋው የተገኘበት ሰው ባሪያዬ ይሆናል፤ የቀራችሁት ግን ነፃ ትሆናላችሁ” አላቸው። 11  ከዚያም እያንዳንዳቸው ወዲያውኑ ከረጢታቸውን መሬት አውርደው መፍታት ጀመሩ። 12  እሱም ከታላቁ ጀምሮ እስከ ታናሹ ድረስ በጥንቃቄ ፈተሸ። በመጨረሻም ጽዋው በቢንያም ከረጢት ውስጥ ተገኘ።+ 13  በዚህ ጊዜ ልብሳቸውን ቀደዱ፤ እያንዳንዳቸውም ጓዛቸውን መልሰው በአህዮቻቸው ላይ በመጫን ወደ ከተማዋ ተመለሱ። 14  ይሁዳና+ ወንድሞቹ ወደ ዮሴፍ ቤት ሲገቡ ዮሴፍ ገና ከቤት አልወጣም ነበር፤ እነሱም በፊቱ መሬት ላይ ተደፉ።+ 15  ዮሴፍም “ይህ ያደረጋችሁት ነገር ምንድን ነው? እንደ እኔ ያለ ሰው ማንኛውንም ነገር በጥንቆላ የማወቅ ችሎታ እንዳለው አታውቁም?” አላቸው።+ 16  በዚህ ጊዜ ይሁዳ እንዲህ አለ፦ “እንግዲህ ለጌታዬ ምን ማለት እንችላለን? ምንስ አፍ አለን? ጻድቅ መሆናችንን እንዴት ማረጋገጥ እንችላለን? እውነተኛው አምላክ ባሪያዎችህ የፈጸሙትን ስህተት አጋልጧል።+ እንግዲህ እኛም ሆን ጽዋው የተገኘበት ሰው ለጌታዬ ባሪያዎች እንሆናለን!” 17  እሱ ግን እንዲህ አላቸው፦ “ይህንማ ፈጽሞ አላደርገውም! ባሪያዬ የሚሆነው ጽዋው የተገኘበት ሰው ነው።+ የቀራችሁት ግን ወደ አባታችሁ በሰላም ሂዱ።” 18  ይሁዳም ወደ እሱ ቀርቦ እንዲህ አለው፦ “እባክህ ጌታዬ እማጸንሃለሁ፤ ባሪያህ አንዲት ቃል ብቻ ይናገር፤ ጌታዬም ይስማው፤ እባክህ በባሪያህ ላይ አትቆጣ፤ ምክንያቱም አንተ ልክ እንደ ፈርዖን ነህ።+ 19  ጌታዬ እኛን ባሪያዎቹን ‘አባት ወይም ወንድም አላችሁ?’ በማለት ጠይቆን ነበር። 20  እኛም ለጌታዬ እንዲህ ስንል መለስንለት፦ ‘አረጋዊ አባት አለን፤ እንዲሁም በስተርጅናው የወለደው የሁላችንም ታናሽ የሆነ ወንድም አለን።+ ወንድሙ ግን ሞቷል፤+ በመሆኑም ከአንድ እናት ከተወለዱት መካከል የቀረው እሱ ብቻ ነው፤+ አባቱም በጣም ይወደዋል።’ 21  ከዚያም አንተ እኛን ባሪያዎችህን ‘እንዳየው ወደ እኔ አምጡት’ አልከን።+ 22  እኛ ግን ጌታዬን ‘ልጁ ከአባቱ ሊለይ አይችልም። ከተለየው ደግሞ አባቱ ያለጥርጥር ይሞታል’+ አልነው። 23  አንተም እኛን ባሪያዎችህን ‘ትንሹን ወንድማችሁን ይዛችሁት ካልመጣችሁ ከእንግዲህ ፊቴን አታዩም’ አልከን።+ 24  “በመሆኑም ወደ ባሪያህ ወደ አባታችን ሄደን የጌታዬን ቃል ነገርነው። 25  ከጊዜ በኋላም አባታችን ‘ተመልሳችሁ ሂዱና ጥቂት እህል ግዙልን’ አለን።+ 26  እኛ ግን እንዲህ አልነው፦ ‘ወደዚያ መሄድ አንችልም። ትንሹ ወንድማችን ከእኛ ጋር ካልሄደ የሰውየውን ፊት ማየት ስለማንችል ትንሹ ወንድማችን አብሮን የሚሄድ ከሆነ ወደዚያ እንወርዳለን።’+ 27  በዚህ ጊዜ ባሪያህ አባታችን እንዲህ አለን፦ ‘ሚስቴ ከሁለት ወንዶች ልጆች ሌላ ምንም እንዳልወለደችልኝ እናንተ ራሳችሁ በሚገባ ታውቃላችሁ።+ 28  ሆኖም አንዱ እንደወጣ በመቅረቱ “መቼም አውሬ ቦጫጭቆት መሆን አለበት!” አልኩ፤+ ይኸው ከዚያን ጊዜ ወዲህ አይቼው አላውቅም። 29  ይሄኛውንም ልጅ ከእኔ ለይታችሁ ብትወስዱትና አደጋ ደርሶበት ቢሞት ሽበቴን በሥቃይ+ ወደ መቃብር*+ ታወርዱታላችሁ።’ 30  “እንግዲህ ወደ ባሪያህ ወደ አባቴ ስመለስ ልጁ ከእኛ ጋር ከሌለ፣ የአባታችን ሕይወት* ከልጁ ሕይወት* ጋር በጥብቅ የተቆራኘ ስለሆነ 31  አባታችን ልጁ አብሮን አለመኖሩን ሲያይ ይሞታል፤ ባሪያዎችህም የባሪያህን የአባታችንን ሽበት በሐዘን ወደ መቃብር* ያወርዱታል። 32  እኔ ባሪያህ ‘ልጁን ወደ አንተ መልሼ ባላመጣው በአባቴ ፊት ለዘላለም በደለኛ ልሁን’ ብዬ ለአባቴ ቃል ገብቻለሁ።+ 33  ስለዚህ እባክህ ልጁ ከወንድሞቹ ጋር እንዲሄድ እኔ ባሪያህ በልጁ ፋንታ እዚሁ ቀርቼ ለጌታዬ ባሪያ ልሁን። 34  ልጁን ሳልይዝ እንዴት ወደ አባቴ እመለሳለሁ? በአባቴ ላይ እንዲህ ያለ መከራ ሲደርስ ማየት አልችልም!”

የግርጌ ማስታወሻ

ወይም “ሲኦል።” የሰው ልጆችን ሁሉ መቃብር ያመለክታል። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ወይም “ነፍስ።”
ወይም “ነፍስ።”
ወይም “ሲኦል።” የሰው ልጆችን ሁሉ መቃብር ያመለክታል። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።