ዘፍጥረት 46:1-34

  • ያዕቆብና ቤተሰቡ ወደ ግብፅ ሄዱ (1-7)

  • ወደ ግብፅ የሄዱት ሰዎች ስም ዝርዝር (8-27)

  • ዮሴፍ በጎሸን ከያዕቆብ ጋር ተገናኘ (28-34)

46  በመሆኑም እስራኤል ያለውን* ሁሉ ይዞ ተነሳ። ቤርሳቤህ+ በደረሰ ጊዜም ለአባቱ ለይስሐቅ አምላክ+ መሥዋዕቶችን አቀረበ።  ከዚያም አምላክ ለእስራኤል ሌሊት በራእይ ተገልጦለት “ያዕቆብ፣ ያዕቆብ!” ሲል ጠራው፤ እሱም “አቤት!” አለ።  አምላክም እንዲህ አለው፦ “እኔ የአባትህ አምላክ የሆንኩት እውነተኛው አምላክ ነኝ።+ ወደ ግብፅ ለመውረድ አትፍራ፤ ምክንያቱም በዚያ ታላቅ ብሔር አደርግሃለሁ።+  እኔ ራሴ ከአንተ ጋር ወደ ግብፅ እወርዳለሁ፤ ደግሞም እኔ ራሴ ከዚያ አወጣሃለሁ፤+ ዮሴፍም ዓይኖችህን በእጁ ይከድናል።”*+  ከዚያ በኋላ ያዕቆብ ከቤርሳቤህ ተነሳ፤ የእስራኤል ወንዶች ልጆችም አባታቸውን ያዕቆብን፣ ልጆቻቸውንና ሚስቶቻቸውን ፈርዖን በላከለት ሠረገሎች ላይ አሳፍረው ጉዞ ጀመሩ።  እነሱም በከነአን ምድር ያፈሩትን ንብረትና መንጎቻቸውን ይዘው ሄዱ። ከዚያም ያዕቆብና ከእሱ ጋር የነበሩት ልጆቹ በሙሉ ወደ ግብፅ መጡ።  እሱም ወንዶች ልጆቹንና ወንዶች የልጅ ልጆቹን እንዲሁም ሴቶች ልጆቹንና ሴቶች የልጅ ልጆቹን ይኸውም ዘሮቹን ሁሉ ይዞ ወደ ግብፅ መጣ።  ወደ ግብፅ የመጡት የእስራኤል ማለትም የያዕቆብ ወንዶች ልጆች ስም ይህ ነው፦+ የያዕቆብ የበኩር ልጅ ሮቤል።+  የሮቤል ወንዶች ልጆች ሃኖክ፣ ፓሉ፣ ኤስሮን እና ካርሚ ነበሩ።+ 10  የስምዖን+ ወንዶች ልጆች የሙኤል፣ ያሚን፣ ኦሃድ፣ ያኪን፣ ጾሃር እንዲሁም ከአንዲት ከነአናዊት የወለደው ሻኡል ነበሩ።+ 11  የሌዊ+ ወንዶች ልጆች ጌድሶን፣ ቀአት እና ሜራሪ ነበሩ።+ 12  የይሁዳ+ ወንዶች ልጆች ኤር፣ ኦናን፣ ሴሎም፣+ ፋሬስ+ እና ዛራ+ ነበሩ፤ ይሁንና ኤር እና ኦናን በከነአን ምድር ሞቱ።+ የፋሬስ ወንዶች ልጆች ኤስሮን እና ሃሙል ነበሩ።+ 13  የይሳኮር ወንዶች ልጆች ቶላ፣ ፑዋ፣ ዮብ እና ሺምሮን ነበሩ።+ 14  የዛብሎን+ ወንዶች ልጆች ሰሬድ፣ ኤሎን እና ያህልኤል ነበሩ።+ 15  ሴት ልጁን ዲናን+ ጨምሮ እነዚህ ሊያ በጳዳንአራም ለያዕቆብ የወለደችለት ልጆች ናቸው። በአጠቃላይ ወንዶች ልጆቹና ሴቶች ልጆቹ 33 ነበሩ።* 16  የጋድ+ ወንዶች ልጆች ጺፍዮን፣ ሃጊ፣ ሹኒ፣ ኤጽቦን፣ ኤሪ፣ አሮድ እና አርዔላይ ነበሩ።+ 17  የአሴር+ ወንዶች ልጆች ይምናህ፣ ይሽዋ፣ ይሽዊ እና በሪአ ሲሆኑ እህታቸውም ሴራህ ትባላለች። የበሪአ ወንዶች ልጆች ሄቤር እና ማልኪኤል ነበሩ።+ 18  ላባ ለልጁ ለሊያ የሰጣት ዚልጳ+ የተባለችው አገልጋይ የወለደቻቸው ወንዶች ልጆች እነዚህ ናቸው። እሷም ለያዕቆብ እነዚህን ወለደችለት፤ እነሱም በአጠቃላይ 16* ነበሩ። 19  የያዕቆብ ሚስት የራሔል ወንዶች ልጆች ዮሴፍና+ ቢንያም+ ነበሩ። 20  ዮሴፍ በግብፅ ምድር ሳለ ምናሴንና+ ኤፍሬምን*+ ወለደ፤ እነዚህም የኦን* ካህን የሆነው የጶጥፌራ ልጅ አስናት+ የወለደችለት ናቸው። 21  የቢንያም+ ወንዶች ልጆች ቤላ፣ ቤኬር፣ አሽቤል፣ ጌራ፣+ ንዕማን፣ ኤሂ፣ ሮሽ፣ ሙጲም፣ ሁፒም+ እና አርድ+ ነበሩ። 22  እነዚህ ራሔል ለያዕቆብ የወለደችለት ወንዶች ልጆች ናቸው፤ እነሱም በአጠቃላይ 14* ነበሩ። 23  የዳን+ ልጅ* ሁሺም+ ነበር። 24  የንፍታሌም+ ወንዶች ልጆች ያህጽኤል፣ ጉኒ፣ የጼር እና ሺሌም ነበሩ።+ 25  ላባ ለልጁ ለራሔል የሰጣት ባላ የተባለችው አገልጋይ የወለደቻቸው ወንዶች ልጆች እነዚህ ናቸው። እሷም ለያዕቆብ እነዚህን ወለደችለት፤ እነሱም በአጠቃላይ ሰባት* ነበሩ። 26  የያዕቆብ ዝርያዎች የሆኑትና ከእሱ ጋር ወደ ግብፅ የገቡት ሰዎች፣* የልጆቹን ሚስቶች ሳይጨምር በአጠቃላይ 66 ነበሩ።+ 27  ዮሴፍ በግብፅ የወለዳቸው ወንዶች ልጆች ሁለት* ነበሩ። ወደ ግብፅ የገቡት የያዕቆብ ቤተሰቦች በአጠቃላይ 70* ነበሩ።+ 28  ያዕቆብ ወደ ጎሸን እየሄደ መሆኑን ለዮሴፍ እንዲነግረው ይሁዳን+ ከእሱ አስቀድሞ ላከው። ወደ ጎሸን ምድር+ በደረሱም ጊዜ 29  ዮሴፍ ሠረገላው እንዲዘጋጅለት ካደረገ በኋላ አባቱን እስራኤልን ለመቀበል ወደ ጎሸን ሄደ። ባገኘውም ጊዜ አንገቱ ላይ ተጠምጥሞ ረዘም ላለ ጊዜ አለቀሰ። 30  ከዚያም እስራኤል ዮሴፍን “ከእንግዲህ ብሞት አይቆጨኝም፤ ዓይንህን ለማየት በቅቻለሁ፤ በሕይወት መኖርህንም አረጋግጫለሁ” አለው። 31  ከዚያም ዮሴፍ ወንድሞቹንና የአባቱን ቤተሰቦች እንዲህ አላቸው፦ “ወደ ፈርዖን ወጥቼ ሁኔታውን ልንገረው፤+ እንዲህም ልበለው፦ ‘በከነአን ምድር ይኖሩ የነበሩት ወንድሞቼና የአባቴ ቤተሰቦች ወደ እኔ መጥተዋል።+ 32  እነሱ እረኞችና+ ከብት አርቢዎች+ ናቸው፤ መንጎቻቸውን፣ ከብቶቻቸውንና ያላቸውን ሁሉ ይዘው መጥተዋል።’+ 33  እንግዲህ ፈርዖን ጠርቶ ‘ሥራችሁ ምንድን ነው?’ ብሎ ሲጠይቃችሁ 34  ‘እኛ አገልጋዮችህም ሆን የቀድሞ አባቶቻችን ከልጅነታችን ጀምሮ ከብት አርቢዎች ነን’ በሉት።+ ግብፃውያን በግ ጠባቂዎችን ስለሚጸየፉ+ በጎሸን ምድር እንድትኖሩ+ ይፈቅድላችኋል።”

የግርጌ ማስታወሻ

ወይም “የእሱ የሆኑትን።”
ያዕቆብ በሚሞትበት ጊዜ ዓይኖቹን መክደንን ያመለክታል።
ወይም “የወንዶችና የሴቶች ልጆቹ ነፍስ ሁሉ 33 ነበር።”
ወይም “16 ነፍስ።”
ሂልያፖሊስን ያመለክታል።
የሰብዓ ሊቃናት ትርጉም አምስት ተጨማሪ ስሞችን ይጠቅሳል። እስጢፋኖስ በሥራ 7:14 ላይ 70 ነፍስ በማለት ፋንታ 75 ነፍስ ያለው ከዚህ ትርጉም ስለጠቀሰ ሊሆን ይችላል።
ወይም “14 ነፍስ።”
ቃል በቃል “ወንዶች ልጆች።”
ወይም “ሰባት ነፍስ።”
ወይም “ነፍሳት።”
ወይም “ሁለት ነፍስ።”
ወይም “70 ነፍስ።” የሰብዓ ሊቃናት ትርጉም “ሰባ አምስት” ነፍስ ይላል። ዘፍ 46:20 ላይ የሚገኘውን የግርጌ ማስታወሻ ተመልከት።