ዘፍጥረት 47:1-31

  • ያዕቆብ ከፈርዖን ጋር ተገናኘ (1-12)

  • የዮሴፍ ጥበብ የተሞላበት አስተዳደር (13-26)

  • እስራኤል በጎሸን መኖር ጀመረ (27-31)

47  ስለዚህ ዮሴፍ ወደ ፈርዖን ሄዶ “አባቴና ወንድሞቼ እንዲሁም መንጎቻቸው፣ ከብቶቻቸውና የእነሱ የሆነው ሁሉ ከከነአን ምድር መጥተዋል፤ በጎሸን ምድር ይገኛሉ”+ አለው።+  እሱም ከወንድሞቹ መካከል አምስቱን ወስዶ ፈርዖን ፊት አቀረባቸው።+  ፈርዖንም የዮሴፍን ወንድሞች “ሥራችሁ ምንድን ነው?” ሲል ጠየቃቸው። እነሱም “እኛ አገልጋዮችህም ሆን የቀድሞ አባቶቻችን በግ አርቢዎች ነን” በማለት መለሱለት።+  ከዚያም ፈርዖንን እንዲህ አሉት፦ “ወደዚህ የመጣነው በምድሪቱ ላይ እንደ ባዕድ አገር ሰው ሆነን ለመኖር ነው፤+ ምክንያቱም በከነአን ምድር ረሃቡ በጣም ስለበረታ ለአገልጋዮችህ መንጋ የሚሆን የግጦሽ ቦታ የለም።+ ስለሆነም እባክህ አገልጋዮችህ በጎሸን ምድር እንዲኖሩ ፍቀድላቸው።”+  በዚህ ጊዜ ፈርዖን ዮሴፍን እንዲህ አለው፦ “አባትህና ወንድሞችህ ወደ አንተ መጥተዋል።  የግብፅ ምድር እንደሆነ በእጅህ ነው። አባትህና ወንድሞችህ ምርጥ በሆነው የምድሪቱ ክፍል እንዲኖሩ አድርግ።+ በጎሸን ምድር ይኑሩ፤ ከእነሱ መካከል ጥሩ ችሎታ እንዳላቸው የምታውቃቸው ሰዎች ካሉ በከብቶቼ ላይ ኃላፊ አድርገህ ሹማቸው።”  ከዚያም ዮሴፍ አባቱን ያዕቆብን አስገብቶ ፈርዖን ፊት አቀረበው፤ ያዕቆብም ፈርዖንን ባረከው።  ፈርዖንም ያዕቆብን “ለመሆኑ ዕድሜህ ስንት ነው?” ሲል ጠየቀው።  ያዕቆብም ፈርዖንን እንዲህ አለው፦ “ከቦታ ወደ ቦታ በመንከራተት* ያሳለፍኩት ዘመን 130 ዓመት ነው። የሕይወት ዘመኔ አጭርና ጭንቀት የበዛበት ነበር፤+ ደግሞም አባቶቼ ከቦታ ወደ ቦታ በመንከራተት* ያሳለፉትን ዘመን አያክልም።”+ 10  ከዚህ በኋላ ያዕቆብ ፈርዖንን መረቀው፤ ከፊቱም ወጥቶ ሄደ። 11  በመሆኑም ዮሴፍ፣ አባቱና ወንድሞቹ እንዲሰፍሩ አደረገ፤ ፈርዖንም ባዘዘው መሠረት ምርጥ ከሆነው የግብፅ ምድር፣ የራምሴስን ምድር ርስት አድርጎ ሰጣቸው።+ 12  ዮሴፍም ለአባቱ፣ ለወንድሞቹና ለመላው የአባቱ ቤተሰብ በትናንሽ ልጆቻቸው ቁጥር ልክ ቀለብ ይሰፍርላቸው ነበር። 13  በዚህ ወቅት ረሃቡ እጅግ በርትቶ ስለነበር በመላው ምድር እህል አልነበረም፤ የግብፅም ምድር ሆነ የከነአን ምድር በረሃቡ የተነሳ በጣም ተጎድተው ነበር።+ 14  ዮሴፍም ሰዎች እህል ሲገዙ የከፈሉትን በግብፅ ምድርና በከነአን ምድር የሚገኘውን ገንዘብ በሙሉ እየሰበሰበ ወደ ፈርዖን ቤት ያስገባ ነበር።+ 15  ከጊዜ በኋላ በግብፅ ምድርና በከነአን ምድር ያለው ገንዘብ አለቀ፤ ግብፃውያንም በሙሉ ወደ ዮሴፍ በመምጣት “እህል ስጠን! ገንዘብ ስለጨረስን ብቻ እንዴት ዓይንህ እያየ እንለቅ?” ይሉት ጀመር። 16  ዮሴፍም “ገንዘባችሁ ካለቀ ከብቶቻችሁን አምጡ፤ እኔም በከብቶቻችሁ ምትክ እህል እሰጣችኋለሁ” አላቸው። 17  በመሆኑም ከብቶቻቸውን ወደ ዮሴፍ ያመጡ ጀመር፤ ዮሴፍም በፈረሶቻቸው፣ በመንጎቻቸው፣ በከብቶቻቸውና በአህዮቻቸው ምትክ እህል ይሰጣቸው ነበር፤ በዚያም ዓመት በከብቶቻቸው ሁሉ ምትክ እህል ሲሰጣቸው ከረመ። 18  ያም ዓመት ካለቀ በኋላ በቀጣዩ ዓመት ሕዝቡ ወደ እሱ በመምጣት እንዲህ ይለው ጀመር፦ “ከጌታዬ የምንደብቀው ምንም ነገር የለም፤ ገንዘባችንንም ሆነ ከብቶቻችንን ለጌታዬ አስረክበናል። ከእኛ ከራሳችንና ከመሬታችን በስተቀር በጌታዬ ፊት ምንም የቀረን ነገር የለም። 19  ዓይንህ እያየ ለምን እንለቅ? መሬታችንስ ለምን ጠፍ ሆኖ ይቅር? እኛንም ሆነ መሬታችንን በእህል ግዛን፤ እኛ ለፈርዖን ባሪያዎች እንሁን፤ መሬታችንም የእሱ ይሁን። በሕይወት እንድንኖርና እንዳንሞት እንዲሁም መሬታችን ጠፍ ሆኖ እንዳይቀር የምንዘራው እህል ስጠን።” 20  በመሆኑም ዮሴፍ የግብፃውያንን መሬት በሙሉ ለፈርዖን ገዛለት፤ ምክንያቱም ረሃቡ እጅግ ስለበረታባቸው ሁሉም ግብፃውያን መሬታቸውን ሸጠው ነበር፤ ስለዚህ ምድሪቱ የፈርዖን ሆነች። 21  ዮሴፍም በግብፅ ምድር ከዳር እስከ ዳር ያለው ሕዝብ ወደ ከተሞች እንዲገባ አደረገ።+ 22  ዮሴፍ ያልገዛው የካህናቱን መሬት ብቻ ነበር፤ ምክንያቱም ፈርዖን ለካህናቱ ቀለብ ይሰፍርላቸው ነበር፤+ እነሱም የሚኖሩት ፈርዖን በሚሰፍርላቸው ቀለብ ነበር። መሬታቸውን ያልሸጡትም ለዚህ ነው። 23  ከዚያም ዮሴፍ ሕዝቡን እንዲህ አላቸው፦ “ይኸው ዛሬ እናንተንም ሆነ መሬታችሁን ለፈርዖን ገዝቻለሁ። ዘር ይኸውላችሁ፤ እናንተም በመሬቱ ላይ ዝሩ። 24  ባፈራም ጊዜ አንድ አምስተኛውን ለፈርዖን ስጡ፤+ አራቱ እጅ ግን ለመሬታችሁ ዘር እንዲሁም ለራሳችሁ፣ በቤታችሁ ላሉትና ለልጆቻችሁ ምግብ እንዲሆናችሁ የእናንተ ይሆናል።” 25  እነሱም “አንተ ሕይወታችንን አትርፈህልናል፤+ በጌታዬ ፊት ሞገስ እናግኝ እንጂ እኛ ለፈርዖን ባሪያዎች እንሆናለን” አሉት።+ 26  ከዚያም ዮሴፍ አንድ አምስተኛው ለፈርዖን እንዲሰጥ የሚያዝ ሕግ አወጣ፤ ይህም ሕግ እስከ ዛሬ ድረስ በግብፅ ምድር ይሠራበታል። የፈርዖን ያልሆነው የካህናቱ መሬት ብቻ ነበር።+ 27  እስራኤላውያንም በግብፅ አገር፣ በጎሸን ምድር መኖራቸውን ቀጠሉ።+ በዚያም ተደላድለው ይኖሩ ጀመር፤ ፍሬያማም ሆኑ፤ ቁጥራቸውም እጅግ እየበዛ ሄደ።+ 28  ያዕቆብም በግብፅ ምድር ለ17 ዓመት ኖረ፤ በመሆኑም ያዕቆብ በሕይወት የኖረበት ዘመን 147 ዓመት ሆነ።+ 29  እስራኤልም የሚሞትበት ቀን ሲቃረብ+ ልጁን ዮሴፍን ጠርቶ እንዲህ አለው፦ “እንግዲህ በፊትህ ሞገስ አግኝቼ ከሆነ እባክህ እጅህን ከጭኔ በታች አድርግ፤ ለእኔም ታማኝ ፍቅርና ታማኝነት አሳየኝ። እባክህ በግብፅ አትቅበረኝ።+ 30  በምሞትበት* ጊዜ ከግብፅ አውጥተህ በአባቶቼ መቃብር ቅበረኝ።”+ እሱም “እሺ፣ እንዳልከኝ አደርጋለሁ” አለው። 31  ያዕቆብም “በል ማልልኝ” አለው፤ እሱም ማለለት።+ በዚህ ጊዜ እስራኤል በአልጋው ራስጌ ላይ ሰገደ።+

የግርጌ ማስታወሻ

ወይም “በጊዜያዊ ነዋሪነት፤ እንደ ባዕድ አገር ሰው ሆኜ።”
ወይም “በጊዜያዊ ነዋሪነት፤ እንደ ባዕድ አገር ሰው ሆነው።”
ቃል በቃል “ከአባቶቼ ጋር በማንቀላፋበት።”