ዘፍጥረት 48:1-22

  • ያዕቆብ የዮሴፍን ሁለት ወንዶች ልጆች ባረካቸው (1-12)

  • ኤፍሬም የበለጠ በረከት አገኘ (13-22)

48  ይህ ከሆነ በኋላ ዮሴፍ “አባትህ ደክሟል” ተብሎ ተነገረው። ዮሴፍም ሁለቱን ወንዶች ልጆቹን ምናሴንና ኤፍሬምን ይዞ ሄደ።+  ከዚያም ያዕቆብ “ልጅህ ዮሴፍ ወደ አንተ መጥቷል” ተብሎ ተነገረው። በመሆኑም እስራኤል እንደ ምንም ቀና ብሎ አልጋው ላይ ተቀመጠ።  ያዕቆብም ዮሴፍን እንዲህ አለው፦ “ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ በከነአን ምድር በምትገኘው በሎዛ ተገልጦልኝ ባረከኝ።+  እሱም እንዲህ አለኝ፦ ‘ፍሬያማ እያደረግኩህ ነው፤ ደግሞም አበዛሃለሁ፤ ብዙ ሕዝብ ያቀፈ ጉባኤም አደርግሃለሁ፤+ ይህችን ምድር ከአንተ በኋላ ለሚመጡት ዘሮችህ ዘላቂ ርስት አድርጌ እሰጣቸዋለሁ።’+  አንተ ወዳለህበት ወደ ግብፅ ከመምጣቴ በፊት በግብፅ ምድር የወለድካቸው ሁለት ወንዶች ልጆች የእኔ ናቸው።+ ሮቤልና ስምዖን የእኔ እንደሆኑ ሁሉ ኤፍሬምና ምናሴም የእኔ ይሆናሉ።+  ከእነሱ በኋላ የምትወልዳቸው ልጆች ግን የአንተ ይሆናሉ። እነሱም ርስት+ በሚሰጣቸው ጊዜ በወንድሞቻቸው ስም ይጠራሉ።  እኔም ከጳዳን ስመጣ ኤፍራታ ለመድረስ ረዘም ያለ መንገድ ሲቀረኝ ራሔል በከነአን ምድር ሞተችብኝ።+ በመሆኑም ወደ ኤፍራታ+ ማለትም ወደ ቤተልሔም+ በሚወስደው መንገድ ላይ ቀበርኳት።”  ከዚያም እስራኤል የዮሴፍን ወንዶች ልጆች ሲያይ “እነዚህ እነማን ናቸው?” ሲል ጠየቀው።  ዮሴፍም አባቱን “እነዚህ አምላክ በዚህ ስፍራ የሰጠኝ ወንዶች ልጆቼ ናቸው”+ አለው። በዚህ ጊዜ “እባክህ እንድባርካቸው ወደ እኔ አቅርባቸው” አለው።+ 10  የእስራኤል ዓይኖች በእርጅና የተነሳ ደክመው ነበር፤ እሱም ማየት ተስኖት ነበር። ስለዚህ ዮሴፍ ልጆቹን ወደ እሱ አቀረባቸው። እሱም ሳማቸው፤ እንዲሁም አቀፋቸው። 11  እስራኤልም ዮሴፍን “ዓይንህን አያለሁ ብዬ አላሰብኩም ነበር፤+ አምላክ ግን ልጆችህንም ጭምር ለማየት አበቃኝ” አለው። 12  ከዚያም ዮሴፍ ልጆቹን ከእስራኤል ጉልበቶች መካከል አውጥቶ ፈቀቅ ካደረጋቸው በኋላ በግንባሩ መሬት ላይ ተደፍቶ ሰገደ። 13  ዮሴፍም ሁለቱን ልጆች ወስዶ ኤፍሬምን+ ከራሱ በስተ ቀኝ ከእስራኤል በስተ ግራ፣ ምናሴን+ ደግሞ ከራሱ በስተ ግራ ከእስራኤል በስተ ቀኝ አድርጎ ወደ እሱ አቀረባቸው። 14  ይሁን እንጂ እስራኤል ታናሽየው ኤፍሬም ቢሆንም ቀኝ እጁን በእሱ ራስ ላይ አደረገ፤ ግራ እጁን ደግሞ በምናሴ ራስ ላይ አደረገ። እንዲህ ያደረገው ሆን ብሎ ነው፤ ምክንያቱም ምናሴ የበኩር ልጅ ነበር።+ 15  ከዚያም ዮሴፍን ባረከው፤+ እንዲህም አለው፦ “አባቶቼ አብርሃምና ይስሐቅ በፊቱ የተመላለሱት+ እውነተኛው አምላክ፣እስከ ዛሬዋ ዕለት ድረስ በሕይወቴ ዘመን ሁሉ እረኛ የሆነልኝ እውነተኛው አምላክ፣+ 16  ከአደጋ ሁሉ ያዳነኝ መልአክ+ እነዚህን ልጆች ይባርክ።+ የእኔም ሆነ የአባቶቼ የአብርሃምና የይስሐቅ ስም በእነሱ ይጠራ። በምድርም ላይ ቁጥራቸው እየበዛ ይሂድ።”+ 17  ዮሴፍም አባቱ ቀኝ እጁን በኤፍሬም ራስ ላይ እንዳደረገ ሲያይ ቅር ተሰኘ፤ ስለዚህ የአባቱን እጅ ከኤፍሬም ራስ ላይ አንስቶ በምናሴ ራስ ላይ ሊያደርገው ሞከረ። 18  ዮሴፍም አባቱን “አባቴ፣ እንዲህ አይደለም፤ በኩሩ+ እኮ ይሄኛው ነው። ቀኝ እጅህን በእሱ ራስ ላይ አድርግ” አለው። 19  አባቱ ግን “አውቄአለሁ ልጄ፣ አውቄአለሁ። እሱም ቢሆን ሕዝብ ይሆናል፤ ታላቅም ይሆናል። ይሁን እንጂ ታናሽ ወንድሙ ከእሱ የበለጠ ይሆናል፤+ ዘሩም በዝቶ ብዙ ብሔር ለመሆን ይበቃል”+ በማለት እንቢ አለው። 20  በመሆኑም በዚያው ቀን እንዲህ ሲል እነሱን መባረኩን ቀጠለ፦+ “እስራኤል በአንተ ስም እንዲህ በማለት ይባርክ፦ ‘አምላክ እንደ ኤፍሬምና እንደ ምናሴ ያድርግህ።’” በዚህ ሁኔታ ኤፍሬምን ከምናሴ አስቀደመው። 21  ከዚያም እስራኤል ዮሴፍን እንዲህ አለው፦ “እንግዲህ እኔ የምሞትበት ጊዜ ቀርቧል።+ አምላክ ግን ከእናንተ እንደማይለይ እንዲሁም ወደ አባቶቻችሁ ምድር እንደሚመልሳችሁ የተረጋገጠ ነው።+ 22  በእኔ በኩል ከአሞራውያን እጅ በሰይፌና በቀስቴ የወሰድኩትን መሬት ከወንድሞችህ አንድ ድርሻ መሬት* አስበልጬ ለአንተ ሰጥቼሃለሁ።”

የግርጌ ማስታወሻ

ወይም “አንድ ተዳፋት መሬት።” ቃል በቃል “አንድ ትከሻ።”