ዘፍጥረት 49:1-33

  • ያዕቆብ ሊሞት በተቃረበበት ጊዜ የተናገረው ትንቢት (1-28)

    • ሴሎ ከይሁዳ ይወጣል (10)

  • ያዕቆብ ስለሚቀበርበት ሁኔታ የሰጠው ትእዛዝ (29-32)

  • ያዕቆብ ሞተ (33)

49  ያዕቆብም ወንዶች ልጆቹን ጠርቶ እንዲህ አላቸው፦ “በኋለኞቹ ቀናት ምን እንደሚያጋጥማችሁ እንድነግራችሁ ተሰብሰቡ።  እናንተ የያዕቆብ ወንዶች ልጆች ተሰብሰቡና ስሙ፤ አዎ፣ አባታችሁን እስራኤልን አዳምጡ።  “ሮቤል፣+ አንተ የበኩር ልጄ ነህ፤+ ኃይሌና የብርታቴ የመጀመሪያ ፍሬ ነህ፤ የላቀ ክብርና የላቀ ኃይል ነበረህ።  እንደሚናወጥ ውኃ ስለምትዋልል የበላይ አትሆንም፤ ምክንያቱም አባትህ አልጋ ላይ ወጥተሃል።+ በዚያን ወቅት መኝታዬን አርክሰሃል። በእርግጥም አልጋዬ ላይ ወጥቷል!  “ስምዖንና ሌዊ ወንድማማቾች ናቸው።+ ሰይፎቻቸው የዓመፅ መሣሪያዎች ናቸው።+  ነፍሴ* ሆይ፣ ከእነሱ ጋር አትወዳጂ። ክብሬ ሆይ፣ ከእነሱ ማኅበር ጋር አትተባበር፤ ምክንያቱም በቁጣ ተነሳስተው ሰዎችን ገድለዋል፤+ ደስ ስላላቸውም ብቻ የበሬዎችን ቋንጃ ቆርጠዋል።  ቁጣቸው ጨካኝ፣ ንዴታቸውም ምሕረት የለሽ ስለሆነ የተረገመ ይሁን።+ በያዕቆብ ልበትናቸው፤ በእስራኤልም ላሰራጫቸው።+  “ይሁዳ+ ሆይ፣ ወንድሞችህ ያወድሱሃል።+ እጅህ የጠላቶችህን አንገት ያንቃል።+ የአባትህ ወንዶች ልጆች በፊትህ ይሰግዳሉ።+  ይሁዳ የአንበሳ ደቦል ነው።+ ልጄ፣ በእርግጥም ያደንከውን በልተህ ትነሳለህ። እንደ አንበሳ ያደፍጣል፤ እንደ አንበሳ ይንጠራራል፤ ማንስ ሊያስነሳው ይደፍራል? 10  ሴሎ* እስኪመጣ ድረስ በትረ መንግሥት ከይሁዳ፣+ የአዛዥም በትር ከእግሮቹ መካከል አይወጣም፤+ ለእሱም ሕዝቦች ይታዘዙለታል።+ 11  አህያውን በወይን ተክል ላይ፣ ውርንጭላውንም ምርጥ በሆነ የወይን ተክል ላይ ያስራል፤ ልብሱን በወይን ጠጅ፣ መጎናጸፊያውንም በወይን ፍሬ ጭማቂ ያጥባል። 12  ዓይኖቹ ከወይን ጠጅ የተነሳ የቀሉ፣ ጥርሶቹም ከወተት የተነሳ የነጡ ናቸው። 13  “የዛብሎን+ መኖሪያ በባሕር ዳርቻ፣ መርከቦች መልሕቅ ጥለው በሚቆሙበት ዳርቻ ይሆናል፤+ የወሰኑም ጫፍ በሲዶና አቅጣጫ ይሆናል።+ 14  “ይሳኮር+ በመንታ ጭነት መካከል የሚተኛ አጥንተ ብርቱ አህያ ነው። 15  ማረፊያ ቦታው መልካም፣ ምድሩም አስደሳች መሆኑን ያያል። ሸክሙን ለመሸከም ትከሻውን ዝቅ ያደርጋል፤ ለግዳጅ ሥራ ይንበረከካል። 16  “ከእስራኤል ነገዶች አንዱ የሆነው ዳን+ በሕዝቡ ላይ ይፈርዳል።+ 17  ዳን፣ ጋላቢው ወደ ኋላ እንዲወድቅ የፈረሱን ሰኮና የሚነክስ በመንገድ ዳር ያለ እባብ፣ በመተላለፊያ ላይ ያለ ቀንዳም እባብ ይሁን።+ 18  ይሖዋ ሆይ፣ የአንተን ማዳን እጠባበቃለሁ። 19  “ጋድ+ ደግሞ የወራሪዎች ቡድን አደጋ ይጥልበታል፤ እሱ ግን ዱካውን ተከታትሎ ይመታዋል።+ 20  “የአሴር+ ምግብ የተትረፈረፈ* ይሆናል፤ በንጉሥ ፊት የሚቀርብ ምግብ ያዘጋጃል።+ 21  “ንፍታሌም+ ሸንቃጣ የሜዳ ፍየል ነው። ከአፉም ያማሩ ቃላት ይወጣሉ።+ 22  “ዮሴፍ+ ፍሬያማ የሆነ ዛፍ ቀንበጥ ነው፤ ቅርንጫፎቹን በግንብ ላይ የሚሰድ በምንጭ ዳር ያለ ፍሬያማ የሆነ ዛፍ ቀንበጥ ነው። 23  ቀስተኞች ግን እረፍት ነሱት፤ ቀስታቸውንም ወረወሩበት፤ ለእሱም ጥላቻ አደረባቸው።+ 24  ሆኖም ቀስቱ ከቦታው ንቅንቅ አላለም፤+ እጆቹም ብርቱና ቀልጣፋ ናቸው።+ ይህም ከያዕቆብ ኃያል አምላክ እጆች፣ ከእረኛው፣ ከእስራኤል ዓለት የተገኘ ነው። 25  እሱ* ከአባትህ አምላክ የተገኘ ነው፤ አምላክም ይረዳሃል፤ እሱም ሁሉን ቻይ ከሆነው አምላክ ጋር ይሆናል። አምላክም ከላይ ከሰማያት በሚገኙ በረከቶች፣ ከታች ከጥልቁ በሚገኙ በረከቶች+ እንዲሁም ከጡትና ከማህፀን በሚገኙ በረከቶች ይባርክሃል። 26  የአባትህ በረከቶች ከዘላለማዊ ተራሮች ከሚመጡት በረከቶችና ጸንተው ከሚኖሩት ኮረብቶች ከሚገኙት መልካም ነገሮች የላቁ ይሆናሉ።+ በረከቶቹም በዮሴፍ ራስ ላይ፣ ከወንድሞቹ መካከል ተነጥሎ በወጣው በእሱ አናት ላይ ይሆናሉ።+ 27  “ቢንያም+ እንደ ተኩላ ይቦጫጭቃል።+ ያደነውን ጠዋት ላይ ይበላል፤ ምሽት ላይ ደግሞ ምርኮ ያከፋፍላል።”+ 28  እነዚህ ሁሉ 12ቱ የእስራኤል ነገዶች ናቸው፤ አባታቸው በባረካቸው ጊዜ የነገራቸው ነገር ይህ ነው። ለእያንዳንዳቸውም የሚገባቸውን በረከት ሰጣቸው።+ 29  ከዚህ በኋላ የሚከተሉትን ትእዛዛት ሰጣቸው፦ “እንግዲህ እኔ ወደ ወገኖቼ ልሰበሰብ* ነው።+ በሂታዊው በኤፍሮን እርሻ ውስጥ በሚገኘው ዋሻ+ ከአባቶቼ ጋር ቅበሩኝ፤ 30  አብርሃም ለመቃብር ስፍራ ብሎ ከሂታዊው ከኤፍሮን በገዛው እርሻ ይኸውም በከነአን ምድር በማምሬ ፊት ለፊት በሚገኘው በማክፈላ እርሻ ውስጥ ባለው ዋሻ ቅበሩኝ። 31  አብርሃምንና ሚስቱን ሣራን የቀበሯቸው እዚያ ነው።+ ይስሐቅንና ሚስቱን ርብቃንም የቀበሯቸው እዚያ ነው፤+ እኔም ብሆን ሊያን የቀበርኳት እዚያው ነው። 32  እርሻውም ሆነ በውስጡ ያለው ዋሻ የተገዛው ከሄት ወንዶች ልጆች ነው።”+ 33  በዚህ መንገድ ያዕቆብ ለወንዶች ልጆቹ እነዚህን መመሪያዎች ሰጥቶ ጨረሰ። ከዚያም እግሮቹን ወደ አልጋው አውጥቶ የመጨረሻ እስትንፋሱን ተነፈሰ፤ ወደ ወገኖቹም ተሰበሰበ።*+

የግርጌ ማስታወሻ

“የእሱ የሆነው፤ ባለቤት የሆነው” የሚል ትርጉም አለው።
ቃል በቃል “ስብ።”
ዮሴፍን ያመለክታል።
ይህ አባባል ሞትን የሚያመለክት ቅኔያዊ አነጋገር ነው።
ይህ አባባል ሞትን የሚያመለክት ቅኔያዊ አነጋገር ነው።