ዘፍጥረት 8:1-22

  • የጥፋት ውኃው ከምድር ላይ እየቀነሰ ሄደ (1-14)

    • ኖኅ ርግብ ላከ (8-12)

  • ከመርከቡ ወጡ (15-19)

  • አምላክ ምድርን በተመለከተ የገባው ቃል (20-22)

8  ሆኖም አምላክ ኖኅን እንዲሁም ከእሱ ጋር በመርከቡ ውስጥ የነበሩትን የዱር እንስሳትና የቤት እንስሳት ሁሉ አሰበ።+ አምላክም ነፋስ በምድር ላይ እንዲነፍስ አደረገ፤ ውኃውም መጉደል ጀመረ።  የጥልቁ ውኃ ምንጮችና የሰማያት የውኃ በሮች ተደፈኑ፤ በመሆኑም ከሰማያት የሚወርደው ዝናብ መዝነቡን አቆመ።*+  ከዚያም ውኃው ቀስ በቀስ ከምድር ላይ እየቀነሰ ሄደ። ከ150 ቀናት በኋላም ውኃው ጎደለ።  በሰባተኛው ወር፣ ከወሩም በ17ኛው ቀን መርከቡ በአራራት ተራሮች ላይ አረፈ።  ውኃውም እስከ አሥረኛው ወር ድረስ ቀስ በቀስ እየቀነሰ ሄደ። በአሥረኛው ወር፣ ከወሩም በመጀመሪያው ቀን የተራሮቹ አናት ታየ።+  ከ40 ቀንም በኋላ ኖኅ የሠራውን የመርከቡን መስኮት+ ከፍቶ  አንድ ቁራ ወደ ውጭ ላከ፤ ቁራው ከመርከቡ ውጭ ሲበር ይቆይና ተመልሶ ይመጣ ነበር፤ ውኃው ከምድር ላይ እስኪደርቅ ድረስ እንዲሁ ያደርግ ነበር።  በኋላም ውኃው ከምድር ላይ መጉደሉን ለማረጋገጥ አንዲት ርግብ ላከ።  ርግቧ ምንም የምታርፍበት* ቦታ ስላላገኘች እሱ ወደነበረበት መርከብ ተመልሳ መጣች፤ ምክንያቱም ውኃው ገና መላውን ምድር እንደሸፈነው ነበር።+ በመሆኑም እጁን ወደ ውጭ ዘርግቶ ተቀበላትና ወደ መርከቡ አስገባት። 10  ከዚያም ሌላ ሰባት ቀን ከጠበቀ በኋላ ርግቧን በድጋሚ ከመርከቡ አውጥቶ ለቀቃት። 11  ርግቧም አመሻሹ ላይ ወደ እሱ በመጣች ጊዜ አዲስ የተቀጠፈ ለምለም የወይራ ቅጠል በአፏ እንደያዘች አየ! ስለዚህ ኖኅ ውኃው ከምድር ላይ መጉደሉን+ አወቀ። 12  እንደገና ሌላ ሰባት ቀን ጠበቀ። ከዚያም ርግቧን አውጥቶ ለቀቃት፤ በዚህ ጊዜ ግን ርግቧ ወደ እሱ ተመልሳ አልመጣችም። 13  ኖኅ በተወለደ በ601ኛው ዓመት፣+ በመጀመሪያው ወር፣ ከወሩም በመጀመሪያው ቀን ውኃው ከመሬቱ ላይ ሸሸ፤ ኖኅም የመርከቡን ሽፋን አንስቶ ተመለከተ፤ በዚህ ጊዜ መሬቱ ደርቆ ነበር። 14  በሁለተኛው ወር፣ ከወሩም በ27ኛው ቀን ምድሪቱ ሙሉ በሙሉ ደረቀች። 15  ከዚያም አምላክ ኖኅን እንዲህ አለው፦ 16  “አንተ፣ ሚስትህ፣ ወንዶች ልጆችህና የልጆችህ ሚስቶች ከመርከቡ ውጡ።+ 17  በምድር ላይ እንዲዋለዱ፣ እንዲራቡና በምድር ላይ እንዲባዙ*+ አብሮህ ያለውን እያንዳንዱን ዓይነት ሕያው ፍጡር ሁሉ+ ይኸውም የሚበርሩ ፍጥረታትን፣ እንስሳትን እንዲሁም በምድር ላይ መሬት ለመሬት የሚሄዱ እንስሳትን ይዘህ ውጣ።” 18  ስለዚህ ኖኅ ከወንዶች ልጆቹ፣+ ከሚስቱና ከልጆቹ ሚስቶች ጋር አብሮ ወጣ። 19  እያንዳንዱ ሕያው ፍጡር፣ መሬት ለመሬት የሚሄድ እያንዳንዱ እንስሳና እያንዳንዱ የሚበር ፍጡር እንዲሁም በምድር ላይ የሚንቀሳቀስ ማንኛውም ነገር በወገን በወገኑ እየሆነ ከመርከቡ ወጣ።+ 20  ከዚያም ኖኅ ለይሖዋ መሠዊያ ሠራ፤+ ንጹሕ ከሆኑት እንስሳት ሁሉ እንዲሁም ንጹሕ ከሆኑት የሚበርሩ ፍጥረታት ሁሉ+ የተወሰኑትን ወስዶ በመሠዊያው ላይ የሚቃጠል መባ አቀረበ።+ 21  ይሖዋም ደስ የሚያሰኘውን* መዓዛ አሸተተ። ስለዚህ ይሖዋ በልቡ እንዲህ አለ፦ “በሰው የተነሳ ከእንግዲህ ወዲህ ፈጽሞ ምድርን አልረግምም፤+ ምክንያቱም የሰው የልብ ዝንባሌ ከልጅነቱ ጀምሮ መጥፎ ነው፤+ ደግሞም አሁን እንዳደረግኩት ሕያው ፍጡርን ሁሉ ፈጽሞ ዳግመኛ አላጠፋም።+ 22  ከአሁን ጀምሮ በምድር ላይ ዘር መዝራትና ማጨድ፣ ቅዝቃዜና ሙቀት፣ በጋና ክረምት እንዲሁም ቀንና ሌሊት ፈጽሞ አይቋረጡም።”+

የግርጌ ማስታወሻ

ወይም “ዝናብ ተገታ።”
ወይም “እግሯን የምታሳርፍበት።”
ወይም “እንዲርመሰመሱ።”
ወይም “የሚያረጋጋውን፤ የሚያበርደውን።” ቃል በቃል “እረፍት የሚሰጠውን።”