ዘፍጥረት 9:1-29

  • ለመላው የሰው ዘር የተሰጠ መመሪያ (1-7)

    • ስለ ደም የተሰጠ ሕግ (4-6)

  • የቀስተ ደመና ቃል ኪዳን (8-17)

  • ስለ ኖኅ ዘሮች የተነገሩ ትንቢቶች (18-29)

9  አምላክም ኖኅንና ወንዶች ልጆቹን ባረካቸው፤ እንዲህም አላቸው፦ “ብዙ ተባዙ፤ ምድርንም ሙሏት።+  አስፈሪነታችሁና አስደንጋጭነታችሁ በምድር ላይ ባለ በእያንዳንዱ ሕያው ፍጡር፣ በሰማያት ላይ በሚበር በእያንዳንዱ ፍጡር እንዲሁም በመሬት ላይ በሚንቀሳቀስ ማንኛውም ፍጡርና በባሕር ውስጥ ባለ ዓሣ ሁሉ ላይ ይሁን። ይኸው ሁሉም በእጃችሁ ውስጥ* እንዲሆኑ ተሰጥተዋል።+  በሕይወት የሚንቀሳቀስ እያንዳንዱ እንስሳ ምግብ ይሁናችሁ።+ የለመለመውን ተክል እንደሰጠኋችሁ ሁሉ እነዚህን በሙሉ ሰጥቻችኋለሁ።+  ብቻ ሕይወቱ* ማለትም ደሙ+ በውስጡ ያለበትን ሥጋ አትብሉ።+  ከዚህም በተጨማሪ ሕይወታችሁ የሆነውን ደማችሁን* የሚያፈሰውን ሁሉ ተጠያቂ አደርገዋለሁ። እያንዳንዱን ሕያው ፍጡር ተጠያቂ አደርገዋለሁ፤ እያንዳንዱንም ሰው ለወንድሙ ሕይወት ተጠያቂ አደርገዋለሁ።+  አምላክ ሰውን በአምሳሉ ስለሠራው+ የሰውን ደም የሚያፈስ ማንም ሰው የእሱም ደም በሰው እጅ ይፈስሳል።+  እናንተ ግን ብዙ ተባዙ፤ ቁጥራችሁም በምድር ላይ እጅግ ይጨምር፤ ደግሞም ተባዙ።”+  አምላክም ኖኅንና ከእሱ ጋር ያሉትን ወንዶች ልጆቹን እንዲህ አላቸው፦  “እኔም አሁን፣ ከእናንተና ከእናንተ በኋላ ከሚመጡት ዘሮቻችሁ ጋር ቃል ኪዳኔን እመሠርታለሁ፤+ 10  እንዲሁም ከእናንተ ጋር ካለው ከእያንዳንዱ ሕያው ፍጡር* ማለትም ከወፎች፣ ከእንስሳት፣ አብረዋችሁ በምድር ላይ ከሚኖሩት ሕያዋን ፍጥረታት በሙሉ እንዲሁም ከመርከቡ ከወጡት ሁሉ ጋር ይኸውም በምድር ላይ ከሚገኝ ከእያንዳንዱ ሕያው ፍጡር ጋር ቃል ኪዳኔን እመሠርታለሁ።+ 11  አዎ፣ ከእንግዲህ ሥጋ* ሁሉ በጥፋት ውኃ እንደማይጠፋ እንዲሁም የጥፋት ውኃ ከእንግዲህ ወዲህ ምድርን ፈጽሞ እንደማያጠፋት ከእናንተ ጋር ቃል ኪዳኔን እመሠርታለሁ።”+ 12  በተጨማሪም አምላክ እንዲህ አለ፦ “በእኔና በእናንተ እንዲሁም ከእናንተ ጋር ባለው በእያንዳንዱ ሕያው ፍጡር* መካከል ለመሠረትኩት ቃል ኪዳን ምልክቱ ይህ ነው፤ ይህም ቃል ኪዳን በመጪዎቹ ትውልዶች ሁሉ ጸንቶ ይኖራል። 13  ቀስተ ደመናዬን በደመናው ላይ አደርጋለሁ፤ ይህም በእኔና በምድር መካከል ላለው ቃል ኪዳን ምልክት ሆኖ ያገለግላል። 14  ምድርን በደመና በጋረድኩ ጊዜ ሁሉ ቀስተ ደመናው በደመናው ላይ ይታያል። 15  እኔም ከእናንተ እንዲሁም ከማንኛውም ዓይነት ሕያው ፍጡር* ሁሉ ጋር የገባሁትን ቃል ኪዳን አስታውሳለሁ፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሥጋን ሁሉ ለማጥፋት የጥፋት ውኃ ፈጽሞ አይወርድም።+ 16  ቀስተ ደመናው በደመናው ላይ ይታያል፤ እኔም እሱን በማይበት ጊዜ በአምላክና በምድር ላይ በሚኖር በማንኛውም ዓይነት ሕያው ፍጡር* መካከል ያለውን ዘላለማዊ ቃል ኪዳን አስታውሳለሁ።” 17  አምላክም “በእኔና በምድር ላይ በሚኖር ሥጋ ሁሉ መካከል ለመሠረትኩት ቃል ኪዳን ምልክቱ ይህ ነው”+ በማለት ለኖኅ በድጋሚ ነገረው። 18  ከመርከቡ የወጡት የኖኅ ወንዶች ልጆች ሴም፣ ካምና ያፌት ናቸው።+ ከጊዜ በኋላ ካም፣ ከነአንን ወለደ።+ 19  የኖኅ ወንዶች ልጆች እነዚህ ሦስቱ ነበሩ፤ የምድር ሕዝብ ሁሉ የተገኘው ከእነሱ ሲሆን በኋላም ወደተለያየ አካባቢ ተሰራጨ።+ 20  ኖኅም ገበሬ ሆነ፤ የወይን እርሻም አለማ። 21  አንድ ቀን ኖኅ የወይን ጠጅ ጠጥቶ ሰከረ፤ በድንኳኑም ውስጥ ራቁቱን ሆነ። 22  የከነአን አባት ካምም የአባቱን እርቃን አየ፤ ውጭ ላሉት ሁለት ወንድሞቹም ነገራቸው። 23  ስለዚህ ሴምና ያፌት ልብስ ወስደው ትከሻቸው ላይ በማድረግ የኋሊት እየተራመዱ ገቡ። በዚህ መንገድም ፊታቸውን ወደ አባታቸው ሳያዞሩ እርቃኑን ሸፈኑ፤ በመሆኑም የአባታቸውን እርቃን አላዩም። 24  ኖኅ ከወይን ጠጅ ስካሩ ሲነቃ ታናሽ ልጁ ያደረገበትን አወቀ፤ 25  እንዲህም አለ፦ “ከነአን የተረገመ ይሁን።+ ለወንድሞቹም የባሪያ ባሪያ ይሁን።”+ 26  በተጨማሪም እንዲህ አለ፦ “የሴም አምላክ ይሖዋ ይወደስ፤ከነአንም የእሱ ባሪያ ይሁን።+ 27  አምላክ ለያፌት ሰፊ መሬት ይስጠው፤በሴም ድንኳኖች ውስጥም ይኑር። ከነአን ለእሱም ጭምር ባሪያ ይሁን።” 28  ኖኅ ከጥፋት ውኃው በኋላ 350 ዓመት ኖረ።+ 29  በመሆኑም ኖኅ በአጠቃላይ 950 ዓመት ኖረ፤ ከዚያም ሞተ።

የግርጌ ማስታወሻ

ወይም “በሥልጣናችሁ ሥር።”
ወይም “ነፍሱ።”
ወይም “የነፍሳችሁን ደም።”
ወይም “ነፍስ።”
ወይም “ሕይወት ያለው ነገር።”
ወይም “ነፍስ።”
ወይም “ከእያንዳንዱ ሥጋ ሕያው ነፍስ።”
ወይም “በእያንዳንዱ ሥጋ ሕያው ነፍስ ሁሉ።”