የሐዋርያት ሥራ 19:1-41

  • ጳውሎስ በኤፌሶን፤ በድጋሚ የተጠመቁ ሰዎች (1-7)

  • ጳውሎስ አስተማረ (8-10)

  • የአጋንንት ተጽዕኖ ቢኖርም ስኬት አገኙ (11-20)

  • በኤፌሶን የተቀሰቀሰ ረብሻ (21-41)

19  ከጊዜ በኋላ፣ አጵሎስ+ በቆሮንቶስ በነበረበት ጊዜ ጳውሎስ በመሃል አገር አቋርጦ ወደ ኤፌሶን ወረደ።+ በዚያም አንዳንድ ደቀ መዛሙርትን አገኘ፤  እነሱንም “አማኞች በሆናችሁ ጊዜ መንፈስ ቅዱስ ተቀብላችሁ ነበር?” አላቸው።+ እነሱም “ኧረ እኛ ስለ መንፈስ ቅዱስ የሰማነው ነገር የለም” ሲሉ መለሱለት።  እሱም “ታዲያ ምን ዓይነት ጥምቀት ነው የተጠመቃችሁት?” አላቸው። እነሱም “የዮሐንስን ጥምቀት” አሉት።+  ጳውሎስም እንዲህ አላቸው፦ “ዮሐንስ ያጠምቅ የነበረው የንስሐ ምልክት የሆነውን ጥምቀት ነበር፤+ ሰዎች ከእሱ በኋላ በሚመጣው+ ይኸውም በኢየሱስ እንዲያምኑ ይነግራቸው ነበር።”  እነሱም ይህን ሲሰሙ በጌታ ኢየሱስ ስም ተጠመቁ።  ጳውሎስም እጁን በላያቸው በጫነ ጊዜ መንፈስ ቅዱስ ወረደባቸው፤+ እነሱም በባዕድ ቋንቋዎች መናገርና መተንበይ ጀመሩ።+  ሰዎቹም በአጠቃላይ 12 ገደማ ነበሩ።  ጳውሎስም ወደ ምኩራብ እየገባ+ ንግግር በመስጠትና ስለ አምላክ መንግሥት አሳማኝ በሆነ መንገድ በማስረዳት ለሦስት ወራት ያህል በድፍረት ሲናገር ቆየ።+  ሆኖም አንዳንዶቹ ግትሮች ስለነበሩ ለማመን ፈቃደኞች አልሆኑም፤ የጌታን መንገድ+ በሕዝቡ ፊት ባጥላሉ ጊዜ ከእነሱ በመራቅ+ ደቀ መዛሙርቱን ለይቶ ወሰዳቸው፤ በጢራኖስ የትምህርት ቤት አዳራሽም በየዕለቱ ንግግር ይሰጥ ነበር። 10  ይህም ለሁለት ዓመት ያህል ቀጠለ፤ ከዚህም የተነሳ በእስያ አውራጃ የሚኖሩ አይሁዳውያንና ግሪካውያን ሁሉ የጌታን ቃል ሰሙ። 11  አምላክም በጳውሎስ እጅ በጣም አስደናቂ የሆኑ ነገሮችን መፈጸሙን ቀጠለ፤+ 12  ሰዎችም የጳውሎስን ሰውነት የነኩ ጨርቆችንና ሽርጦችን ወደታመሙት ሰዎች ሲወስዱ+ ሰዎቹ በሽታቸው ይለቃቸው ነበር፤ ርኩሳን መናፍስትም ይወጡ ነበር።+ 13  ይሁንና እየዞሩ አጋንንትን ያስወጡ ከነበሩት አይሁዳውያን አንዳንዶቹም “ጳውሎስ በሚሰብከው በኢየሱስ ስም እንድትወጣ አጥብቄ አዝሃለሁ”+ እያሉ ክፉ መናፍስት በያዟቸው ሰዎች ላይ የጌታ ኢየሱስን ስም ለመጥራት ሞከሩ። 14  አስቄዋ የተባለ የአንድ አይሁዳዊ የካህናት አለቃ ሰባት ወንዶች ልጆችም ይህን ያደርጉ ነበር። 15  ክፉው መንፈስ ግን መልሶ “ኢየሱስን አውቀዋለሁ፤+ ጳውሎስንም አውቀዋለሁ፤+ እናንተ ደግሞ ማን ናችሁ?” አላቸው። 16  ከዚያም ክፉው መንፈስ ያደረበት ሰው ዘሎ ጉብ አለባቸው፤ አሸነፋቸውም፤ ስለዚህ ራቁታቸውን ሆነውና ቆስለው ከዚያ ቤት ሸሹ። 17  በኤፌሶን የሚኖሩት አይሁዳውያንና ግሪካውያን ሁሉ ይህን ሰሙ፤ በመሆኑም ሁሉም ፍርሃት አደረባቸው፤ የጌታ ኢየሱስ ስምም ይበልጥ እየገነነ ሄደ። 18  አማኞች ከሆኑት መካከል ብዙዎቹም እየመጡ ያደረጉትን ይናዘዙና በግልጽ ይናገሩ ነበር። 19  ደግሞም አስማት ይሠሩ ከነበሩት መካከል ብዙዎች መጽሐፎቻቸውን አንድ ላይ ሰብስበው በማምጣት በሰው ሁሉ ፊት አቃጠሉ።+ የመጽሐፎቹንም ዋጋ ሲያሰሉ 50,000 የብር ሳንቲሞች* ሆኖ አገኙት። 20  በዚህ መንገድ የይሖዋ* ቃል በኃይል እየተስፋፋና እያሸነፈ ሄደ።+ 21  ይህ ሁሉ ከሆነ በኋላ ጳውሎስ በመቄዶንያና+ በአካይያ በኩል አልፎ ወደ ኢየሩሳሌም ለመሄድ ወሰነ።+ “እዚያ ከሄድኩ በኋላ ደግሞ ወደ ሮም ማቅናት አለብኝ” አለ።+ 22  ስለዚህ ከሚያገለግሉት መካከል ሁለቱን ማለትም ጢሞቴዎስንና+ ኤርስጦስን+ ወደ መቄዶንያ ላካቸው፤ እሱ ግን በእስያ አውራጃ ለተወሰነ ጊዜ ቆየ። 23  በዚህ ወቅት የጌታን መንገድ+ በተመለከተ ታላቅ ሁከት ተፈጠረ።+ 24  ምክንያቱም ድሜጥሮስ የተባለ አንድ የብር አንጥረኛ የአርጤምስን ቤተ መቅደስ የብር ምስሎች እየቀረጸ ለእጅ ጥበብ ባለሙያዎች ከፍተኛ ትርፍ ያስገኝ ነበር።+ 25  ድሜጥሮስ እነሱንና በተመሳሳይ ሙያ የተሰማሩ ሰዎችን ሰብስቦ እንዲህ አለ፦ “እናንተ ሰዎች፣ መቼም ብልጽግናችን የተመካው በዚህ ሥራ ላይ እንደሆነ ታውቃላችሁ። 26  አሁን ግን ይህ ጳውሎስ የተባለ ሰው በኤፌሶን+ ብቻ ሳይሆን በመላው የእስያ አውራጃ ማለት ይቻላል፣ በእጅ የተሠሩ አማልክት ሁሉ በፍጹም አማልክት አይደሉም እያለ ብዙ ሰዎችን አሳምኖ አመለካከታቸውን እንዳስለወጠ ያያችሁትና የሰማችሁት ጉዳይ ነው።+ 27  ከዚህም በላይ አሳሳቢ የሆነው ነገር የእኛ ሥራ መናቁ ብቻ ሳይሆን የታላቋ አምላክ የአርጤምስ ቤተ መቅደስ ዋጋ ቢስ ሆኖ ሊቀርና መላው የእስያ አውራጃም ሆነ ዓለም በሙሉ የሚያመልካት አርጤምስ ገናና ክብሯ ሊገፈፍ መሆኑ ጭምር ነው።” 28  ሰዎቹ ይህን ሲሰሙ በቁጣ ተሞልተው “የኤፌሶኗ አርጤምስ ታላቅ ናት!” እያሉ ይጮኹ ጀመር። 29  በመሆኑም ከተማዋ በረብሻ ታመሰች፤ ሕዝቡም የመቄዶንያ ሰዎች የሆኑትን የጳውሎስን የጉዞ ጓደኞች ይኸውም ጋይዮስንና አርስጥሮኮስን+ እየጎተቱ ግር ብለው ወደ ጨዋታ ማሳያው ስፍራ ገቡ። 30  ጳውሎስም ሕዝቡ ወዳለበት ሊገባ ፈልጎ ነበር፤ ደቀ መዛሙርቱ ግን ከለከሉት። 31  የጳውሎስ ወዳጆች የነበሩ አንዳንድ የበዓላትና የውድድር አዘጋጆች እንኳ ሳይቀሩ ወደ ጨዋታ ማሳያው ስፍራ በመግባት ራሱን ለአደጋ እንዳያጋልጥ መልእክት በመላክ ለመኑት። 32  በተሰበሰበው ሕዝብ መካከል ከፍተኛ ትርምስ ተፈጥሮ ስለነበር አንዳንዶቹ አንድ ነገር ሲናገሩ ሌሎቹ ደግሞ ሌላ ነገር እየተናገሩ ይጯጯኹ ነበር፤ አብዛኛው ሰው ለምን እዚያ እንደተገኘ እንኳ አያውቅም ነበር። 33  አንዳንዶች እስክንድርን ከሕዝቡ መካከል ባወጡት ጊዜ አይሁዳውያን ወደ ፊት ገፉት፤ እስክንድርም የመከላከያ ሐሳቡን ለሕዝቡ ሊያቀርብ ፈልጎ በእጁ ምልክት ሰጣቸው። 34  ሆኖም አይሁዳዊ መሆኑን ባወቁ ጊዜ ሁሉም በአንድ ድምፅ “የኤፌሶኗ አርጤምስ ታላቅ ናት!” እያሉ ለሁለት ሰዓት ያህል ጮኹ። 35  በመጨረሻ የከተማዋ ዋና ጸሐፊ ሕዝቡን ጸጥ አሰኝቶ እንዲህ አለ፦ “የኤፌሶን ሰዎች ሆይ፣ የታላቋ አርጤምስ ቤተ መቅደስና ከሰማይ የወረደው ምስሏ ጠባቂ የኤፌሶናውያን ከተማ እንደሆነች የማያውቅ ማን አለ? 36  ይህ ፈጽሞ የማይታበል ሐቅ ስለሆነ ልትረጋጉና የችኮላ እርምጃ ከመውሰድ ልትቆጠቡ ይገባል። 37  ምክንያቱም እነዚህ ያመጣችኋቸው ሰዎች ቤተ መቅደስ የዘረፉ ወይም የምናመልካትን አምላክ የሰደቡ አይደሉም። 38  ስለዚህ ድሜጥሮስና+ አብረውት ያሉት የእጅ ጥበብ ባለሙያዎች የሚከሱት ሰው ካለ ችሎት የሚሰየምባቸው ቀናት ያሉ ከመሆኑም ሌላ የሮም አገረ ገዢዎች* አሉ፤ እዚያ መሟገት ይችላሉ። 39  ከዚህ ያለፈ ልታቀርቡት የምትፈልጉት ክስ ካለ ግን በመደበኛ ጉባኤ መዳኘት ይኖርበታል። 40  አለዚያ ዛሬ በተፈጸመው ነገር የተነሳ ሕዝብ አሳድማችኋል ተብለን እንዳንከሰስ ያሰጋል፤ ለዚህ ሁሉ ሁከት መንስኤው ምን እንደሆነ ብንጠየቅ የምንሰጠው አጥጋቢ መልስ የለም።” 41  ይህን ከተናገረ በኋላ የተሰበሰበው ሕዝብ እንዲበተን አደረገ።

የግርጌ ማስታወሻ

ብር ከተባለው ማዕድን የተሠራ ሳንቲም።
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።