የሐዋርያት ሥራ 21:1-40
21 ከእነሱ በግድ ከተለያየን በኋላ በመርከብ ተሳፍረን በቀጥታ በመጓዝ ቆስ ደረስን፤ በማግስቱ ደግሞ ወደ ሮድስ አመራን፤ ከዚያም ወደ ጳጥራ ሄድን።
2 ወደ ፊንቄ የሚሻገር መርከብ ባገኘን ጊዜ ተሳፍረን ጉዟችንን ቀጠልን።
3 የቆጵሮስ ደሴት በታየችን ጊዜ በስተ ግራ ትተናት ወደ ሶርያ አመራን፤ መርከቡ ጭነቱን በጢሮስ ማራገፍ ስለነበረበት እኛም እዚያ ወረድን።
4 ደቀ መዛሙርቱን ፈልገን ካገኘን በኋላ በዚያ ሰባት ቀን ቆየን። እነሱም በመንፈስ ተመርተው ጳውሎስ ወደ ኢየሩሳሌም እንዳይሄድ ደጋግመው ነገሩት።+
5 የቆይታ ጊዜያችን ባለቀ ጊዜ ከዚያ ተነስተን ጉዟችንን ጀመርን፤ ሴቶችንና ልጆችን ጨምሮ ደቀ መዛሙርቱ ሁሉ ከከተማዋ እስክንወጣ ድረስ ሸኙን። ከዚያም በባሕሩ ዳርቻ ተንበርክከን ጸለይን፤
6 በኋላም ተሰነባበትን። ከዚያም እኛ ወደ መርከቡ ገባን፤ እነሱ ደግሞ ወደ ቤታቸው ተመለሱ።
7 ከጢሮስ ተነስተን በመርከብ በመጓዝ ጴጤሌማይስ ደረስን፤ እዚያም ለወንድሞች ሰላምታ ካቀረብን በኋላ አብረናቸው አንድ ቀን ቆየን።
8 በማግስቱ ከዚያ ተነስተን ቂሳርያ ደረስን፤ በዚያም ከሰባቱ ወንዶች አንዱ ወደሆነው ወደ ወንጌላዊው ፊልጶስ+ ቤት ገብተን እሱ ጋ አረፍን።
9 ይህ ሰው ትንቢት የሚናገሩ አራት ያላገቡ* ሴቶች ልጆች ነበሩት።+
10 ለብዙ ቀናት እዚያ ከተቀመጥን በኋላ አጋቦስ+ የሚባል አንድ ነቢይ ከይሁዳ ወረደ።
11 ወደ እኛም መጥቶ የጳውሎስን ቀበቶ በመውሰድ የራሱን እግርና እጅ ካሰረ በኋላ እንዲህ አለ፦ “መንፈስ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ ‘አይሁዳውያን የዚህን ቀበቶ ባለቤት በኢየሩሳሌም እንዲህ አድርገው ያስሩታል፤+ ለአሕዛብም አሳልፈው ይሰጡታል።’”+
12 ይህን ስንሰማ እኛም ሆንን በዚያ የነበሩት ደቀ መዛሙርት ጳውሎስ ወደ ኢየሩሳሌም እንዳይወጣ እንለምነው ጀመር።
13 በዚህ ጊዜ ጳውሎስ “እያለቀሳችሁ ልቤን ለምን ታባባላችሁ? እኔ ስለ ጌታ ኢየሱስ ስም በኢየሩሳሌም ለመታሰር ብቻ ሳይሆን ለመሞትም እንኳ ዝግጁ ነኝ” ሲል መለሰ።+
14 እሱን ለማሳመን ያደረግነው ጥረት ሳይሳካ በመቅረቱ “እንግዲህ የይሖዋ* ፈቃድ ይሁን” ብለን ዝም አልን።*
15 ከዚህ በኋላ ለጉዞው ተዘጋጅተን ወደ ኢየሩሳሌም መጓዝ ጀመርን።
16 በቂሳርያ ከሚኖሩት ደቀ መዛሙርት አንዳንዶቹ ወደምናርፍበት ሰው ቤት እኛን ለመውሰድ አብረውን ሄዱ፤ ይህ ሰው ምናሶን የተባለ የቆጵሮስ ሰው ሲሆን ከቀድሞዎቹ ደቀ መዛሙርት አንዱ ነበር።
17 ኢየሩሳሌም በደረስን ጊዜ ወንድሞች በደስታ ተቀበሉን።
18 በማግስቱም ጳውሎስ ከእኛ ጋር ወደ ያዕቆብ ሄደ፤+ ሽማግሌዎቹም ሁሉ በዚያ ነበሩ።
19 ሰላምታ ካቀረበላቸውም በኋላ፣ እሱ ባከናወነው አገልግሎት አማካኝነት አምላክ በአሕዛብ መካከል የፈጸማቸውን ነገሮች በዝርዝር ይተርክላቸው ጀመር።
20 እነሱም ይህን ከሰሙ በኋላ አምላክን አመሰገኑ፤ እሱን ግን እንዲህ አሉት፦ “ወንድም፣ ከአይሁዳውያን መካከል በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ አማኞች እንዳሉ ታውቃለህ፤ ደግሞም ሁሉም ለሕጉ ቀናተኞች ናቸው።+
21 እነሱም አንተ በአሕዛብ መካከል ያሉት አይሁዳውያን ሁሉ ልጆቻቸውን እንዳይገርዙም ሆነ የቆየውን ልማድ እንዳይከተሉ በመንገር የሙሴን ሕግ እንዲተዉ ስታስተምር እንደቆየህ ስለ አንተ የሚወራውን ወሬ ሰምተዋል።+
22 እንግዲህ ምን ማድረግ ይሻላል? መምጣትህን እንደሆነ መስማታቸው አይቀርም።
23 ስለዚህ አሁን የምንነግርህን ነገር አድርግ፦ ስእለት ያለባቸው አራት ሰዎች በእኛ ዘንድ አሉ።
24 እነዚህን ሰዎች ይዘህ በመሄድ ከእነሱ ጋር የመንጻት ሥርዓት ፈጽም፤ ራሳቸውንም እንዲላጩ የሚያስፈልገውን ገንዘብ ክፈልላቸው። ይህን ካደረግክ በአንተ ላይ የተወራው ሁሉ ከንቱ መሆኑንና አንተም ሕጉን እያከበርክ በሥርዓት እንደምትኖር ሁሉም ሰው ያውቃል።+
25 ከአሕዛብ የመጡትን አማኞች በተመለከተ ግን ለጣዖት ከተሠዋ፣+ ከደም፣+ ታንቆ ከሞተ* እንስሳ ሥጋና+ ከፆታ ብልግና* እንዲርቁ+ ወስነን ደብዳቤ ጽፈንላቸዋል።”
26 ከዚያም ጳውሎስ በማግስቱ ሰዎቹን ይዞ በመሄድ አብሯቸው የመንጻት ሥርዓቱን ፈጸመ፤+ የመንጻት ሥርዓቱ የሚያበቃበትን ቀንና ለእያንዳንዳቸው መባ የሚቀርብበትን ጊዜ ለማሳወቅም ወደ ቤተ መቅደሱ ገባ።
27 ሰባቱ ቀናት ሊጠናቀቁ በተቃረቡበት ጊዜ ከእስያ የመጡ አይሁዳውያን ጳውሎስን በቤተ መቅደሱ ውስጥ ሲያዩት ሕዝቡን ሁሉ ለሁከት በማነሳሳት ያዙት፤
28 እንዲህ እያሉም ጮኹ፦ “የእስራኤል ሰዎች ሆይ፣ እርዱን! በሄደበት ቦታ ሁሉ ለሚያገኛቸው ሰዎች ሕዝባችንን፣ ሕጋችንንና ይህን ስፍራ የሚቃወም ትምህርት የሚያስተምረው ይህ ሰው ነው። በዚህ ላይ ደግሞ የግሪክ ሰዎችን ወደ ቤተ መቅደሱ ይዞ በመምጣት ይህን ቅዱስ ስፍራ አርክሷል።”+
29 ይህን ያሉት ቀደም ሲል የኤፌሶኑን ሰው ጢሮፊሞስን+ ከእሱ ጋር ከተማው ውስጥ አይተውት ስለነበር ነው፤ ደግሞም ጳውሎስ ይህን ሰው ወደ ቤተ መቅደሱ ይዞት የገባ መስሏቸው ነበር።
30 በመሆኑም ከተማዋ በሙሉ ታወከች፤ ሕዝቡም ግር ብለው እየሮጡ በመምጣት ጳውሎስን ያዙት፤ እየጎተቱም ከቤተ መቅደሱ አወጡት፤ በሮቹም ወዲያው ተዘጉ።
31 ሊገድሉትም እየሞከሩ ሳለ መላዋ ኢየሩሳሌም እንደታወከች የሚገልጽ ወሬ ለሠራዊቱ ሻለቃ ደረሰው፤
32 እሱም ወዲያውኑ ወታደሮችንና የጦር መኮንኖችን ይዞ እየሮጠ ወደ እነሱ ወረደ። እነሱም ሻለቃውንና ወታደሮቹን ሲያዩ ጳውሎስን መደብደባቸውን ተዉ።
33 በዚህ ጊዜ የሠራዊቱ ሻለቃ ቀርቦ በቁጥጥር ሥር አዋለውና በሁለት ሰንሰለት እንዲታሰር አዘዘ፤+ ከዚያም ማን እንደሆነና ምን እንዳደረገ ጠየቀ።
34 ከሕዝቡም መካከል አንዳንዶች አንድ ነገር ሲናገሩ ሌሎቹ ደግሞ ሌላ ነገር ይናገሩ ነበር። ስለዚህ ሻለቃው ከጫጫታው የተነሳ ምንም የተጨበጠ ነገር ማግኘት ስላልቻለ ወደ ጦር ሰፈሩ እንዲወሰድ አዘዘ።
35 ሆኖም ጳውሎስ ወደ ደረጃው በደረሰ ጊዜ ከሕዝቡ ዓመፅ የተነሳ ወታደሮቹ ተሸክመውት ለመሄድ ተገደዱ፤
36 ብዙ ሕዝብም እየተከተለ “ግደለው!” እያለ ይጮኽ ነበር።
37 ጳውሎስ ወደ ጦር ሰፈሩ ሊያስገቡት በተቃረቡ ጊዜ ሻለቃውን “አንዴ ላናግርህ?” አለው። ሻለቃውም እንዲህ አለው፦ “ግሪክኛ መናገር ትችላለህ እንዴ?
38 አንተ ከዚህ ቀደም ዓመፅ አነሳስተህ 4,000 ነፍሰ ገዳዮችን ወደ ምድረ በዳ ያሸፈትከው ግብፃዊ አይደለህም?”
39 በዚህ ጊዜ ጳውሎስ “እኔ እንኳ በኪልቅያ የምትገኘው የታወቀችው የጠርሴስ+ ከተማ ነዋሪ የሆንኩ አይሁዳዊ ነኝ።+ ስለዚህ ለሕዝቡ እናገር ዘንድ እንድትፈቅድልኝ እለምንሃለሁ” አለ።
40 ከፈቀደለት በኋላ ጳውሎስ ደረጃው ላይ ቆሞ ለሕዝቡ በእጁ ምልክት ሰጠ። ታላቅ ጸጥታ በሰፈነ ጊዜ በዕብራይስጥ ቋንቋ+ እንዲህ ሲል ለሕዝቡ መናገር ጀመረ፦