የሐዋርያት ሥራ 22:1-30

  • ጳውሎስ ለሕዝቡ የመከላከያ መልስ ሰጠ (1-21)

  • ጳውሎስ የሮም ዜግነቱን ተጠቀመበት (22-29)

  • የሳንሄድሪን ሸንጎ ተሰበሰበ (30)

22  “ወንድሞችና አባቶች፣ አሁን ለእናንተ የማቀርበውን የመከላከያ መልስ ስሙ።”+  እነሱም በዕብራይስጥ ቋንቋ ሲናገር በሰሙ ጊዜ ይበልጥ ጸጥ አሉ፤ እሱም እንዲህ አለ፦  “እኔ ኪልቅያ ውስጥ በምትገኘው በጠርሴስ+ የተወለድኩ አይሁዳዊ ነኝ፤+ ሆኖም የተማርኩት በዚህችው ከተማ በገማልያል+ እግር ሥር ተቀምጬ ሲሆን የአባቶችን ሕግ በጥብቅ እንድከተል የሚያስችል ትምህርት ቀስሜአለሁ፤+ ዛሬ እናንተ ሁላችሁ እንዲህ እንደምትቀኑ ሁሉ እኔም ለአምላክ እቀና ነበር።+  ወንዶችንም ሆነ ሴቶችን በማሰርና ለወህኒ ቤት አሳልፌ በመስጠት የጌታን መንገድ የሚከተሉትን እስከ ሞት ድረስ ስደት አደርስባቸው ነበር፤+  ይህን በተመለከተም ሊቀ ካህናቱና መላው የሽማግሌዎች ጉባኤ ሊመሠክሩ ይችላሉ። ከእነሱም በደማስቆ ላሉ ወንድሞቻችን የተጻፈ ደብዳቤ ተቀብዬ በዚያ ያሉትን አስሬ ወደ ኢየሩሳሌም በማምጣት ለማስቀጣት በጉዞ ላይ ነበርኩ።  “ሆኖም በጉዞ ላይ ሳለሁ ወደ ደማስቆ ስቃረብ፣ እኩለ ቀን ገደማ ላይ ድንገት ከሰማይ የመጣ ኃይለኛ ብርሃን በዙሪያዬ አንጸባረቀ፤+  እኔም መሬት ላይ ወደቅኩ፤ ከዚያም ‘ሳኦል፣ ሳኦል ለምን ታሳድደኛለህ?’ የሚል ድምፅ ሰማሁ።  እኔም መልሼ ‘ጌታዬ፣ አንተ ማን ነህ?’ አልኩት። እሱም ‘እኔ አንተ የምታሳድደኝ የናዝሬቱ ኢየሱስ ነኝ’ አለኝ።  ከእኔ ጋር የነበሩት ሰዎች ብርሃኑን አይተዋል፤ ሆኖም እሱ ሲያነጋግረኝ ድምፁን አልሰሙም።* 10  በዚህ ጊዜ ‘ጌታ ሆይ፣ ምን ባደርግ ይሻላል?’ አልኩት። ጌታም ‘ተነስተህ ወደ ደማስቆ ሂድ፤ እዚያም ልታደርገው የሚገባህ ነገር ሁሉ ይነገርሃል’ አለኝ።+ 11  ይሁንና ከብርሃኑ ድምቀት የተነሳ ዓይኔ ማየት ስለተሳነው አብረውኝ የነበሩት ሰዎች እጄን ይዘው እየመሩ ደማስቆ አደረሱኝ። 12  “ከዚያም ሕጉን በሚገባ በመጠበቅ ለአምላክ ያደረ እንዲሁም እዚያ በሚኖሩት አይሁዳውያን ሁሉ የተመሠከረለት ሐናንያ የሚባል አንድ ሰው 13  ወደ እኔ መጣ። አጠገቤም ቆሞ ‘ወንድሜ ሳኦል፣ ዓይኖችህ ይብሩልህ!’ አለኝ። እኔም በዚያው ቅጽበት ቀና ብዬ አየሁት።+ 14  እሱም እንዲህ አለኝ፦ ‘የአባቶቻችን አምላክ ፈቃዱን እንድታውቅ፣ ጻድቁን እንድታይና+ ድምፁን እንድትሰማ መርጦሃል፤ 15  ይህን ያደረገው ስላየኸውና ስለሰማኸው ነገር በሰው ሁሉ ፊት ለእሱ ምሥክር እንድትሆን ነው።+ 16  ታዲያ አሁን ምን ትጠብቃለህ? ተነስና ተጠመቅ፤ ስሙንም እየጠራህ+ ኃጢአትህን ታጠብ።’+ 17  “ሆኖም ወደ ኢየሩሳሌም ከተመለስኩ በኋላ+ በቤተ መቅደሱ ውስጥ እየጸለይኩ ሳለ ሰመመን ውስጥ ገባሁ፤ 18  ጌታም ‘ስለ እኔ የምትሰጠውን ምሥክርነት ስለማይቀበሉ ፍጠን፤ ከኢየሩሳሌም ቶሎ ብለህ ውጣ’ ሲለኝ አየሁት።+ 19  እኔም እንዲህ አልኩት፦ ‘ጌታ ሆይ፣ በየምኩራቡ እየዞርኩ በአንተ የሚያምኑትን አስርና እገርፍ እንደነበረ እነሱ ራሳቸው በሚገባ ያውቃሉ፤+ 20  ደግሞም የአንተ ምሥክር የነበረው የእስጢፋኖስ ደም ሲፈስ እኔ በድርጊቱ በመስማማት እዚያ ቆሜ የገዳዮቹን ልብስ ስጠብቅ ነበር።’+ 21  እሱ ግን ‘በሩቅ ወዳሉ አሕዛብ ስለምልክህ ተነስተህ ሂድ’ አለኝ።”+ 22  ሕዝቡ ይህን እስኪናገር ድረስ ጸጥ ብለው ሲያዳምጡት ቆዩ። ከዚያም “ይህ ሰው መኖር የማይገባው ስለሆነ ከምድር ገጽ ይወገድ!” ብለው ጮኹ። 23  ደግሞም እየጮኹ መደረቢያቸውን ይወረውሩና አፈር ወደ ላይ ይበትኑ ስለነበር+ 24  የሠራዊቱ ሻለቃ ጳውሎስን ወደ ጦር ሰፈሩ እንዲያስገቡት ትእዛዝ ሰጠ፤ ደግሞም በጳውሎስ ላይ እንዲህ የሚጮኹት ለምን እንደሆነ በትክክል ማወቅ ስለፈለገ እየተገረፈ እንዲመረመር አዘዘ። 25  ሆኖም ሊገርፉት ወጥረው ባሰሩት ጊዜ ጳውሎስ አጠገቡ የቆመውን መኮንን “አንድን ሮማዊ* ሳይፈረድበት* ለመግረፍ ሕግ ይፈቅድላችኋል?” አለው።+ 26  መኮንኑ ይህን ሲሰማ ወደ ሠራዊቱ ሻለቃ ሄዶ “ምን ለማድረግ ነው ያሰብከው? ይህ ሰው እኮ ሮማዊ ነው” አለው። 27  ሻለቃውም ወደ ጳውሎስ ቀርቦ “ሮማዊ ነህ እንዴ?” አለው። እሱም “አዎ” አለው። 28  ሻለቃውም መልሶ “እኔ ይህን የዜግነት መብት የገዛሁት ብዙ ገንዘብ አውጥቼ ነው” አለው። ጳውሎስ ደግሞ “እኔ ግን በመወለድ አገኘሁት” አለ።+ 29  ስለዚህ እያሠቃዩ ሊመረምሩት የነበሩት ሰዎች ወዲያውኑ ከእሱ ራቁ፤ የሠራዊቱ ሻለቃም በሰንሰለት አስሮት ስለነበር ሮማዊ መሆኑን ሲገነዘብ ፈራ።+ 30  በመሆኑም በማግስቱ አይሁዳውያን የከሰሱት ለምን እንደሆነ በትክክል ማወቅ ስለፈለገ ፈታውና የካህናት አለቆቹ እንዲሁም መላው የሳንሄድሪን ሸንጎ እንዲሰበሰቡ አዘዘ። ከዚያም ጳውሎስን አውርዶ በመካከላቸው አቆመው።+

የግርጌ ማስታወሻ

ወይም “ድምፅ ቢሰሙም ምን እንደተባለ አላስተዋሉም።”
ወይም “የሮም ዜጋ።”
ወይም “ችሎት ፊት ሳይቀርብ።”