የሐዋርያት ሥራ 25:1-27

  • ጳውሎስ፣ ፊስጦስ ፊት ቀረበ (1-12)

    • “ወደ ቄሳር ይግባኝ ብያለሁ!” (11)

  • ፊስጦስ ከንጉሥ አግሪጳ ጋር ተማከረ (13-22)

  • ጳውሎስ፣ አግሪጳ ፊት ቀረበ (23-27)

25  ፊስጦስም+ ወደ አውራጃው ከመጣና ኃላፊነቱን ከተረከበ ከሦስት ቀን በኋላ ከቂሳርያ ወደ ኢየሩሳሌም ወጣ።  የካህናት አለቆችና አንዳንድ የታወቁ አይሁዳውያንም በጳውሎስ ላይ ያላቸውን ክስ ለእሱ አቀረቡ።+ ከዚያም ፊስጦስን ይለምኑት ጀመር፤  ጳውሎስን ወደ ኢየሩሳሌም በማስመጣት እንዲተባበራቸው* ጠየቁት። ይህን ያሉት ግን መንገድ ላይ አድፍጠው ጳውሎስን ሊገድሉት አስበው ስለነበር ነው።+  ይሁን እንጂ ፊስጦስ፣ ጳውሎስ እዚያው ቂሳርያ ታስሮ እንደሚቆይና እሱ ራሱም በቅርቡ ወደዚያ እንደሚመለስ ነገራቸው።  “በመሆኑም ከእናንተ መካከል ሥልጣን ያላቸው ከእኔ ጋር ይውረዱና ሰውየው ያጠፋው ነገር ካለ ይክሰሱት” አላቸው።+  ስለዚህ ፊስጦስ ከስምንት ወይም ከአሥር ቀን ያልበለጠ ጊዜ ከእነሱ ጋር ካሳለፈ በኋላ ወደ ቂሳርያ ወረደ፤ በማግስቱም በፍርድ ወንበር ላይ ተቀምጦ ጳውሎስን እንዲያመጡት አዘዘ።  ጳውሎስ በቀረበ ጊዜ ከኢየሩሳሌም የመጡት አይሁዳውያን በዙሪያው ቆመው በማስረጃ ያልተደገፉ በርካታ ከባድ ክሶች አቀረቡበት።+  ጳውሎስ ግን “እኔ በአይሁዳውያን ሕግ ላይም ሆነ በቤተ መቅደሱ ወይም በቄሳር ላይ ምንም የፈጸምኩት በደል የለም” ሲል የመከላከያ መልሱን ሰጠ።+  ፊስጦስም በአይሁዳውያን ዘንድ ተወዳጅነት ማትረፍ ስለፈለገ+ ጳውሎስን “ወደ ኢየሩሳሌም ወጥተህ ስለዚህ ጉዳይ እዚያ እኔ ባለሁበት መዳኘት ትፈልጋለህ?” ሲል ጠየቀው። 10  ጳውሎስ ግን እንዲህ አለ፦ “እኔ ልዳኝበት በሚገባኝ በቄሳር የፍርድ ወንበር ፊት ቆሜአለሁ። አንተ ራስህ በሚገባ እንደተገነዘብከው በአይሁዳውያን ላይ የፈጸምኩት ምንም በደል የለም። 11  በእርግጥ ጥፋተኛ ሆኜ ከተገኘሁና ለሞት የሚያበቃ ነገር ፈጽሜ ከሆነ+ ከሞት ልዳን አልልም፤ እነዚህ ሰዎች ያቀረቡብኝ ክስ ሁሉ መሠረተ ቢስ ከሆነ ግን እነሱን ለማስደሰት ብሎ ማንም ሰው እኔን ለእነሱ አሳልፎ የመስጠት መብት የለውም። ወደ ቄሳር ይግባኝ ብያለሁ!”+ 12  በዚህ ጊዜ ፊስጦስ ከአማካሪዎቹ ጋር ከተመካከረ በኋላ “ወደ ቄሳር ይግባኝ ስላልክ ወደ ቄሳር ትሄዳለህ” ሲል መለሰለት። 13  የተወሰኑ ቀናት ካለፉ በኋላ ንጉሥ አግሪጳና* በርኒቄ ለፊስጦስ ክብር ይፋዊ ጉብኝት ለማድረግ ወደ ቂሳርያ መጡ። 14  በዚያም ብዙ ቀናት ስለቆዩ ፊስጦስ የጳውሎስን ጉዳይ ለንጉሡ በማቅረብ እንዲህ አለው፦ “ፊሊክስ እስር ቤት የተወው አንድ ሰው አለ፤ 15  ኢየሩሳሌም በነበርኩበት ጊዜ የካህናት አለቆቹና የአይሁዳውያን ሽማግሌዎች ይህን ሰው በመክሰስ+ እንዲፈረድበት ጥያቄ አቅርበው ነበር። 16  እኔ ግን ክስ የቀረበበት ሰው ከከሳሾቹ ጋር ፊት ለፊት ተገናኝቶ ለቀረበበት ክስ የመከላከያ መልስ መስጠት የሚችልበት አጋጣሚ ሳያገኝ እንዲሁ ሰውን ለማስደሰት ተብሎ ብቻ አሳልፎ መስጠት የሮማውያን ሥርዓት እንዳልሆነ ገለጽኩላቸው።+ 17  ስለዚህ ከሳሾቹ ወደዚህ በመጡ ጊዜ ምንም ሳልዘገይ በማግስቱ በፍርድ ወንበር ላይ ተቀምጬ ሰውየውን እንዲያመጡት አዘዝኩ። 18  ከሳሾቹም ቆመው በተናገሩ ጊዜ እኔ የጠበቅኩትን ያህል ከባድ በደል እንደፈጸመ የሚያሳይ ክስ አላቀረቡበትም።+ 19  ከዚህ ይልቅ ከእሱ ጋር ይከራከሩ የነበረው ስለ ገዛ አምልኳቸውና*+ ስለሞተው፣ ጳውሎስ ግን ሕያው ነው ስለሚለው ኢየሱስ ስለተባለ ሰው ነው።+ 20  እኔም ይህን ክርክር እንዴት እንደምፈታው ግራ ስለገባኝ ጳውሎስ ወደ ኢየሩሳሌም ሄዶ ስለዚህ ጉዳይ እዚያ መፋረድ ይፈልግ እንደሆነ ጠየቅኩት።+ 21  ጳውሎስ ግን አውግስጦስ* ውሳኔ እስኪሰጥ ድረስ ታስሮ እንዲቆይ ይግባኝ ጠየቀ፤+ በመሆኑም ወደ ቄሳር እስከምልከው ድረስ በእስር ቤት እንዲቆይ አዘዝኩ።” 22  በዚህ ጊዜ አግሪጳ ፊስጦስን “እኔም ይህ ሰው ሲናገር ብሰማው ደስ ይለኝ ነበር” አለው።+ እሱም “እንግዲያውስ ነገ ትሰማዋለህ” አለው። 23  ስለዚህ በማግስቱ አግሪጳና በርኒቄ በታላቅ ክብር ደምቀው እንዲሁም በሻለቃዎችና በከተማዋ ታላላቅ ሰዎች ታጅበው ወደ መሰብሰቢያ አዳራሹ ገቡ፤ ፊስጦስም ትእዛዝ በሰጠ ጊዜ ጳውሎስ እንዲቀርብ ተደረገ። 24  ፊስጦስም እንዲህ አለ፦ “ንጉሥ አግሪጳና ከእኛ ጋር እዚህ የተሰበሰባችሁ ሁሉ፣ ይህ የምታዩት ሰው በኢየሩሳሌምም ሆነ እዚህ፣ አይሁዳውያን ሁሉ ከእንግዲህ በሕይወት ሊኖር አይገባውም እያሉ በመጮኽ ለእኔ አቤቱታ ያቀረቡበት ሰው ነው።+ 25  እኔ ግን ለሞት የሚያበቃ ምንም ነገር እንዳልፈጸመ ተረድቻለሁ።+ በመሆኑም እሱ ራሱ ወደ አውግስጦስ ይግባኝ ስላለ ልልከው ወስኛለሁ። 26  ይሁንና ስለ እሱ ወደ ጌታዬ የምጽፈው ምንም የተረጋገጠ ነገር አላገኘሁም። ስለዚህ አሁን በችሎቱ ፊት ከተመረመረ በኋላ ልጽፈው የምችለው ነገር አገኝ ዘንድ በእናንተ ሁሉ ፊት በተለይ ደግሞ በአንተ በንጉሥ አግሪጳ ፊት አቀረብኩት። 27  ምክንያቱም አንድን እስረኛ የተከሰሰበትን ምክንያት ሳይገልጹ መላክ ተገቢ አልመሰለኝም።”

የግርጌ ማስታወሻ

ቃል በቃል “ለእነሱ እንዲያደላ።”
እዚህ ላይ የተጠቀሰው ዳግማዊ ሄሮድስ አግሪጳ ነው።
ወይም “ስለ ገዛ ሃይማኖታቸውና።”
ለሮም ንጉሠ ነገሥት የሚሰጥ የማዕረግ ስም ነው።