የሐዋርያት ሥራ 27:1-44

  • ጳውሎስ ወደ ሮም በመርከብ ተወሰደ (1-12)

  • መርከቡ በማዕበል ተመታ (13-38)

  • መርከቡ ተሰባበረ (39-44)

27  እኛም በመርከብ ወደ ጣሊያን እንድንሄድ ስለተወሰነ+ ጳውሎስንና የተወሰኑ እስረኞችን የአውግስጦስ ክፍለ ጦር አባል ለሆነ ዩልዮስ ለሚባል አንድ የጦር መኮንን አስረከቧቸው።  ከአድራሚጢስ ተነስቶ በእስያ አውራጃ የባሕር ዳርቻ ላይ ወደሚገኙት ወደቦች ሊሄድ በተዘጋጀ መርከብ ተሳፍረን ጉዞ ጀመርን፤ በተሰሎንቄ የሚኖረው የመቄዶንያው አርስጥሮኮስም+ አብሮን ነበር።  በማግስቱ ሲዶና ደረስን፤ ዩልዮስም ለጳውሎስ ደግነት* በማሳየት ወደ ወዳጆቹ እንዲሄድና እንክብካቤ እንዲያደርጉለት ፈቀደለት።  ከዚያም ተነስተን በባሕር ላይ ጉዟችንን ቀጠልን፤ ነፋሱ ከፊት ለፊታችን ይነፍስ ስለነበር ቆጵሮስን ተገን አድርገን አለፍን።  ከዚያም በኪልቅያና በጵንፍልያ ዳርቻ በኩል ያለውን ባሕር አቋርጠን በሊቂያ ወደሚገኘው የሚራ ወደብ ደረስን።  በዚያም መኮንኑ ወደ ጣሊያን የሚሄድ ከእስክንድርያ የመጣ መርከብ አግኝቶ አሳፈረን።  ከዚያም ለብዙ ቀናት በዝግታ ተጉዘን በስንት ችግር ቀኒዶስ ደረስን። ነፋሱ እንደ ልብ እንድንጓዝ ስላልፈቀደልን በስልሞና በኩል ቀርጤስን ተገን አድርገን አለፍን።  የባሕሩን ዳርቻ ይዘን በብዙ ችግር በመጓዝ በላሲያ ከተማ አቅራቢያ ወዳለው “መልካም ወደብ” ወደተባለ ስፍራ ደረስን።  ረጅም ጊዜ በመቆየታችንና የስርየት ቀን+ ጾም እንኳ ሳይቀር በማለፉ፣ ወቅቱ በባሕር ላይ ለመጓዝ አደገኛ ነበር፤ በመሆኑም ጳውሎስ አንድ ሐሳብ አቀረበ፤ 10  እንዲህም አላቸው፦ “እናንተ ሰዎች፣ ይህ ጉዞ በጭነቱና በመርከቡ ላይ ብቻ ሳይሆን በሕይወታችንም* ላይ እንኳ ሳይቀር ከፍተኛ ጉዳትና ጥፋት ሊያስከትል እንደሚችል ይታየኛል።” 11  ይሁን እንጂ መኮንኑ ጳውሎስ የተናገረውን ከመቀበል ይልቅ የመርከቡ መሪና የመርከቡ ባለቤት የተናገሩትን ሰማ። 12  ወደቡ የክረምቱን ጊዜ በዚያ ለማሳለፍ አመቺ ስላልነበረ አብዛኞቹ ከዚያ ተነስተው ጉዟቸውን በመቀጠል እንደ ምንም ፊንቄ ወደተባለው የቀርጤስ ወደብ ደርሰው ክረምቱን እዚያ ለማሳለፍ ሐሳብ አቀረቡ፤ ይህ ወደብ ወደ ሰሜን ምሥራቅም ሆነ ወደ ደቡብ ምሥራቅ ለመሄድ የሚያስችል ነበር። 13  የደቡብ ነፋስ በቀስታ እየነፈሰ እንዳለ ባዩ ጊዜ እንዳሰቡት የሆነላቸው መስሏቸው መልሕቁን ነቅለው የቀርጤስን የባሕር ዳርቻ ይዘው መጓዝ ጀመሩ። 14  ይሁንና ብዙም ሳይቆይ አውራቂስ* የሚባል ኃይለኛ አውሎ ነፋስ ከደሴቲቱ ቁልቁል ነፈሰ። 15  መርከቡ እንቅስቃሴው ስለተገታና ነፋሱን ሰንጥቆ መሄድ ስላልቻለ ዝም ብለን በነፋሱ እየተነዳን ሄድን። 16  ከዚያም ቄዳ የተባለችውን ትንሽ ደሴት ተገን አድርገን በፍጥነት ተጓዝን፤ ሆኖም በመርከቡ ኋለኛ ክፍል የነበረችውን ትንሿን ጀልባ* መቆጣጠር የቻልነው በብዙ ችግር ነበር። 17  ጀልባዋ ወደ ላይ ተጎትታ ከተጫነች በኋላ መርከቡን ዙሪያውን በማሰር አጠናከሩት፤ ከስርቲስ* አሸዋማ ደለል ጋር እንዳይላተሙ ስለፈሩም የሸራውን ገመዶች በመፍታት ሸራውን ዝቅ ካደረጉ በኋላ በነፋስ እየተነዱ ሄዱ። 18  አውሎ ነፋሱ ክፉኛ እያንገላታን ስለነበር በማግስቱ የመርከቡን ጭነት ያቃልሉ ጀመር። 19  በሦስተኛውም ቀን ለመርከቡ የሚያገለግሉትን ቁሳቁሶች በገዛ እጃቸው ወደ ባሕሩ ወረወሩ። 20  ለብዙ ቀናት ፀሐይንም ሆነ ከዋክብትን ማየት ስላልቻልንና ውሽንፍሩ ስለበረታብን በመጨረሻ በሕይወት የመትረፍ ተስፋችን እየተሟጠጠ ሄደ። 21  ሰዎቹ እህል ሳይቀምሱ ብዙ ቀን ከቆዩ በኋላ ጳውሎስ በመካከላቸው ቆሞ እንዲህ አለ፦ “እናንተ ሰዎች፣ ምክሬን ሰምታችሁ ቢሆን ኖሮ ከቀርጤስ ባልተነሳችሁና ይህ ጉዳትና ኪሳራ ባልደረሰ ነበር።+ 22  አሁንም ቢሆን አይዟችሁ! ምክንያቱም መርከቡ ብቻ እንጂ ከእናንተ አንድም ሰው* አይጠፋም። 23  ቅዱስ አገልግሎት የማቀርብለትና ንብረቱ የሆንኩለት አምላክ የላከው መልአክ+ ትናንት ሌሊት አጠገቤ ቆሞ 24  ‘ጳውሎስ ሆይ፣ አትፍራ። ቄሳር ፊት መቅረብ ይገባሃል፤+ አምላክ ለአንተ ሲል ከአንተ ጋር የሚጓዙት ሰዎች ሁሉ እንዲተርፉ ያደርጋል’ ብሎኛል። 25  ስለዚህ እናንተ ሰዎች፣ አይዟችሁ! ምክንያቱም ይህ የተነገረኝ ነገር በትክክል እንደሚፈጸም በአምላክ ላይ እምነት አለኝ። 26  ይሁን እንጂ ከአንዲት ደሴት ዳርቻ ጋር መላተማችን የግድ ነው።”+ 27  በ14ኛው ሌሊት በአድርያ ባሕር ላይ ወዲያና ወዲህ እየተንገላታን ሳለ እኩለ ሌሊት ላይ መርከበኞቹ ወደ አንድ የብስ የተቃረቡ መሰላቸው። 28  ጥልቀቱንም ሲለኩ 36 ሜትር ገደማ* ሆኖ አገኙት፤ ጥቂት ርቀት ከተጓዙም በኋላ በድጋሚ ሲለኩ 27 ሜትር ገደማ* ሆኖ አገኙት። 29  ከዓለት ጋር እንላተማለን ብለው ስለፈሩ ከመርከቡ የኋለኛ ክፍል አራት መልሕቆች ጥለው የሚነጋበትን ጊዜ በጉጉት መጠባበቅ ጀመሩ። 30  ሆኖም መርከበኞቹ ከመርከቡ የፊተኛ ክፍል መልሕቅ የሚጥሉ አስመስለው ትንሿን ጀልባ ወደ ባሕር በማውረድ ከመርከቡ ለማምለጥ ሲሞክሩ 31  ጳውሎስ መኮንኑንና ወታደሮቹን “እነዚህ ሰዎች መርከቡን ጥለው ከሄዱ ልትድኑ አትችሉም” አላቸው።+ 32  በዚህ ጊዜ ወታደሮቹ የትንሿን ጀልባ ገመዶች ቆርጠው ብቻዋን ተንሳፋ እንድትቀር አደረጓት። 33  ሊነጋ ሲል ጳውሎስ እንዲህ በማለት ምግብ እንዲቀምሱ ሁሉንም አበረታታቸው፦ “እህል የሚባል ነገር ሳትቀምሱ እንዲሁ ልባችሁ ተንጠልጥሎ ስትጠባበቁ ይኸው ዛሬ 14ኛ ቀናችሁ ነው። 34  ስለዚህ ለራሳችሁ ደህንነት ስለሚበጅ እህል እንድትቀምሱ እለምናችኋለሁ፤ ምክንያቱም ከእናንተ መካከል ከራስ ፀጉሩ አንድ እንኳ የሚጠፋበት የለም።” 35  ይህን ካለ በኋላ ዳቦ ወስዶ በሁሉ ፊት አምላክን አመሰገነ፤ ቆርሶም ይበላ ጀመር። 36  በዚህ ጊዜ ሁሉም ተበረታተው ምግብ እየወሰዱ ይበሉ ጀመር። 37  መርከቡ ላይ በአጠቃላይ 276 ሰዎች* ነበርን። 38  በልተው ከጠገቡ በኋላ ስንዴውን ወደ ባሕሩ በመጣል የመርከቡን ጭነት አቃለሉ።+ 39  ሲነጋም የደረሱበትን አገር ለይተው ማወቅ አልቻሉም፤+ ሆኖም አሸዋማ የሆነ የባሕር ወሽመጥ ተመለከቱ፤ ስለዚህ እንደ ምንም ብለው መርከቡን ወደ ባሕሩ ዳርቻ ለማድረስ ወሰኑ። 40  በመሆኑም መልሕቆቹን ቆርጠው ባሕሩ ውስጥ ጣሉ፤ በዚያው ጊዜም የመቅዘፊያዎቹን ገመዶች ፈቱ፤ የፊተኛውንም ሸራ ነፋስ እንዲያገኘው ከፍ ካደረጉ በኋላ ወደ ባሕሩ ዳርቻ አመሩ። 41  ሆኖም ድንገት በባሕር ውስጥ ካለ የአሸዋ ቁልል ጋር ተላተሙ፤ በዚህ ጊዜ መርከቡ መሬት ስለነካ የፊተኛው ክፍሉ ሊንቀሳቀስ በማይችል ሁኔታ አሸዋው ውስጥ ተቀረቀረ፤ የመርከቡ የኋለኛ ክፍል ግን በማዕበል እየተመታ ይሰባበር ጀመር።+ 42  በዚህ ጊዜ ወታደሮቹ ከእስረኞቹ አንዳቸውም እንኳ ዋኝተው እንዳያመልጡ ሊገድሏቸው ወሰኑ። 43  መኮንኑ ግን ጳውሎስን ለማዳን ቆርጦ ስለነበር ያሰቡትን እንዳይፈጽሙ ከለከላቸው። ከዚያም መዋኘት የሚችሉ ወደ ባሕሩ እየዘለሉ እንዲገቡና ቀድመው ወደ የብስ እንዲደርሱ አዘዘ፤ 44  የቀሩትም ሰዎች አንዳንዶቹ በሳንቃዎች፣ ሌሎቹ ደግሞ በመርከቡ ስብርባሪዎች ላይ እየተንጠላጠሉ እንዲወጡ አዘዘ። በዚህ መንገድ ሁሉም በደህና ወደ የብስ ደረሱ።+

የግርጌ ማስታወሻ

ወይም “ሰብዓዊ ደግነት።”
ወይም “በነፍሳችንም።”
የሰሜን ምሥራቅ ነፋስን ያመለክታል።
ሕይወት አድን ጀልባ።
ወይም “ነፍስ።”
በጥልቀት መለኪያ (ፋተም) ሃያ። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
በጥልቀት መለኪያ (ፋተም) አሥራ አምስት። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
ወይም “ነፍሳት።”