የሐዋርያት ሥራ 8:1-40
8 ሳኦልም በእሱ መገደል ተስማምቶ ነበር።+
በዚያ ቀን በኢየሩሳሌም በሚገኘው ጉባኤ ላይ ከባድ ስደት ተነሳ፤ ከሐዋርያት በስተቀር ደቀ መዛሙርቱ በሙሉ በይሁዳና በሰማርያ ክልሎች ሁሉ ተበተኑ።+
2 ሆኖም ለአምላክ ያደሩ ሰዎች እስጢፋኖስን ወስደው ቀበሩት፤ ታላቅ ለቅሶም አለቀሱለት።
3 ሳኦልም በጉባኤው ላይ ከፍተኛ ጥቃት ማድረስ ጀመረ። በየቤቱ እየገባ ወንዶችንም ሆነ ሴቶችን ጎትቶ በማውጣት ወህኒ ቤት ያስገባቸው ነበር።+
4 ይሁን እንጂ የተበተኑት ደቀ መዛሙርት በሄዱበት ቦታ ሁሉ የአምላክን ቃል ምሥራች ሰበኩ።+
5 በዚህ ጊዜ ፊልጶስ ወደ ሰማርያ+ ከተማ* ሄዶ ስለ ክርስቶስ ይሰብክላቸው ጀመር።
6 ሕዝቡ ፊልጶስ የሚናገረውን ሲሰሙና የፈጸማቸውን ተአምራዊ ምልክቶች ሲመለከቱ ሁሉም በአንድ ልብ በትኩረት ይከታተሉት ጀመር።
7 ርኩሳን መናፍስት ያደሩባቸው ብዙ ሰዎችም ነበሩ፤ ርኩሳን መናፍስቱም በከፍተኛ ድምፅ እየጮኹ ይወጡ ነበር።+ በተጨማሪም ሽባና አንካሳ የነበሩ በርካታ ሰዎች ተፈወሱ።
8 ከዚህም የተነሳ በዚያች ከተማ ታላቅ ደስታ ሆነ።
9 በዚያች ከተማ ስምዖን የሚባል አንድ ሰው ነበር፤ ይህ ሰው ከዚህ ቀደም አስማት እየሠራ የሰማርያን ሕዝብ ያስደምም የነበረ ሲሆን ታላቅ ሰው እንደሆነ አድርጎም ይናገር ነበር።
10 ከትንሹ አንስቶ እስከ ትልቁ ድረስ፣ ሰዎች ሁሉ “ይህ ሰው ታላቅ ተብሎ የሚጠራ ‘የአምላክ ኃይል’ ነው” በማለት ትልቅ ቦታ ይሰጡት ነበር።
11 ረዘም ላለ ጊዜ በአስማት ሥራው ሲያስደንቃቸው ስለቆየ የሚለውን ሁሉ ይቀበሉ ነበር።
12 ይሁንና ስለ አምላክ መንግሥትና ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ስም ምሥራች እያወጀ የነበረውን ፊልጶስን ባመኑት ጊዜ+ ወንዶችም ሴቶችም ይጠመቁ ጀመር።+
13 ስምዖን ራሱም አማኝ ሆነ፤ ከተጠመቀም በኋላ ከፊልጶስ+ አይለይም ነበር፤ ምልክቶችና ታላላቅ ተአምራት ሲፈጸሙ በማየት ይደነቅ ነበር።
14 በኢየሩሳሌም ያሉ ሐዋርያት የሰማርያ ሰዎች የአምላክን ቃል እንደተቀበሉ ሲሰሙ+ ጴጥሮስንና ዮሐንስን ላኩላቸው፤
15 እነሱም ወደዚያ ወርደው መንፈስ ቅዱስን እንዲቀበሉ ጸለዩላቸው።+
16 ምክንያቱም በጌታ ኢየሱስ ስም ተጠመቁ እንጂ መንፈስ ቅዱስ ገና በአንዳቸውም ላይ አልወረደም ነበር።+
17 ከዚያም ጴጥሮስና ዮሐንስ እጃቸውን ጫኑባቸው፤+ እነሱም መንፈስ ቅዱስን ተቀበሉ።
18 ስምዖንም ሐዋርያት እጃቸውን የጫኑበት ሰው ሁሉ መንፈስ ቅዱስ እንደሚቀበል አይቶ ገንዘብ እንደሚሰጣቸው ቃል በመግባት
19 “እጄን የምጭንበት ሰው ሁሉ መንፈስ ቅዱስን እንዲቀበል ይህን ሥልጣን ለእኔም ስጡኝ” አላቸው።
20 ጴጥሮስ ግን እንዲህ አለው፦ “የአምላክን ነፃ ስጦታ በገንዘብ ማግኘት እንደምትችል ስላሰብክ የብር ገንዘብህ ከአንተ ጋር ይጥፋ።+
21 ልብህ በአምላክ ፊት ቀና ስላልሆነ በዚህ አገልግሎት ምንም ዓይነት ድርሻም ሆነ ዕድል ፋንታ የለህም።
22 ስለዚህ ከዚህ ክፋትህ ንስሐ ግባ፤ ምናልባት የልብህ ክፉ ሐሳብ ይቅር ይባልልህ እንደሆነ ይሖዋን* ተማጸን፤
23 መራራ መርዝና* የክፋት ባሪያ እንደሆንክ አያለሁና።”
24 ስምዖንም መልሶ “ከተናገራችሁት ነገር አንዱም እንዳይደርስብኝ እባካችሁ ይሖዋን* ማልዱልኝ” አላቸው።
25 ጴጥሮስና ዮሐንስ የተሟላ ምሥክርነት ከሰጡና የይሖዋን* ቃል ከተናገሩ በኋላ የሰማርያ ሰዎች በሚኖሩባቸው በርካታ መንደሮች ምሥራቹን እያወጁ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ።+
26 ይሁንና የይሖዋ* መልአክ+ ፊልጶስን “ተነስተህ በደቡብ በኩል ከኢየሩሳሌም ወደ ጋዛ በሚወስደው መንገድ ሂድ” አለው። (ይህ መንገድ የበረሃ መንገድ ነው።)
27 እሱም ተነስቶ ሄደ፤ የኢትዮጵያ ንግሥት የህንደኬ* ባለሥልጣንና የገንዘቧ ሁሉ ኃላፊ የሆነ አንድ ኢትዮጵያዊ ጃንደረባም* አገኘ። ይህ ሰው ለአምልኮ ወደ ኢየሩሳሌም ሄዶ ነበር፤+
28 እየተመለሰም ሳለ በሠረገላው ውስጥ ተቀምጦ የነቢዩ ኢሳይያስን መጽሐፍ ድምፁን ከፍ አድርጎ ያነብ ነበር።
29 መንፈስም ፊልጶስን “ሂድና ወደዚህ ሠረገላ ቅረብ” አለው።
30 ፊልጶስ ከሠረገላው ጎን እየሮጠ ጃንደረባው የነቢዩ ኢሳይያስን መጽሐፍ ጮክ ብሎ ሲያነብ ሰማና “ለመሆኑ የምታነበውን ትረዳዋለህ?” አለው።
31 እሱም “የሚመራኝ ሰው ሳይኖር እንዴት ልረዳው እችላለሁ?” አለው። ፊልጶስንም ሠረገላው ላይ ወጥቶ አብሮት እንዲቀመጥ ለመነው።
32 ያነበው የነበረው የቅዱስ መጽሐፉ ክፍል የሚከተለው ነበር፦ “እንደ በግ ለመታረድ ተነዳ፤ በሸላቹ ፊት ዝም እንደሚል ጠቦት እሱም አፉን አልከፈተም።+
33 ውርደት በደረሰበት ወቅት ፍትሕ ተነፈገ።+ ስለ ትውልዱ ማን በዝርዝር ሊናገር ይችላል? ምክንያቱም ሕይወቱ ከምድር ላይ ተወግዷል።”+
34 ጃንደረባውም ፊልጶስን “እባክህ ንገረኝ፣ ነቢዩ ይህን የተናገረው ስለ ማን ነው? ስለ ራሱ ነው ወይስ ስለ ሌላ ሰው?” አለው።
35 ፊልጶስም መናገር ጀመረ፤ ከዚህ ቅዱስ መጽሐፍ አንስቶም ስለ ኢየሱስ የሚገልጸውን ምሥራች ነገረው።
36 እየተጓዙም ሳሉ ውኃ ወዳለበት ቦታ ደረሱ፤ ጃንደረባውም “ውኃ ይኸውና፤ እንዳልጠመቅ የሚከለክለኝ ምን ነገር አለ?” አለው።
37 *——
38 ከዚያም ሠረገላው እንዲቆም አዘዘ፤ ሁለቱም ወርደው ውኃው ውስጥ ገቡ፤ ፊልጶስም ጃንደረባውን አጠመቀው።
39 ከውኃውም በወጡ ጊዜ፣ የይሖዋ* መንፈስ ወዲያውኑ ፊልጶስን ወሰደው፤ ጃንደረባውም ፊልጶስን ከዚያ በኋላ አላየውም፤ ይሁንና ደስ ብሎት ጉዞውን ቀጠለ።
40 በኋላ ግን ፊልጶስ በአሽዶድ ታየ፤ ቂሳርያም እስኪደርስ ድረስ በሚያልፍበት ክልል በሚገኙ ከተሞች ሁሉ ምሥራቹን ያውጅ ነበር።+