የሐዋርያት ሥራ 9:1-43

  • ሳኦል ወደ ደማስቆ እየተጓዘ ሳለ (1-9)

  • ሐናንያ ሳኦልን እንዲረዳው ተላከ (10-19ሀ)

  • ሳኦል በደማስቆ ስለ ኢየሱስ ሰበከ (19ለ-25)

  • ሳኦል ወደ ኢየሩሳሌም ሄደ (26-31)

  • ሳኦል ወደ ኢየሩሳሌም ሄደ (32-35)

  • ለጋስ የሆነችው ዶርቃ ከሞት ተነሳች (36-43)

9  ሳኦል ግን አሁንም በጌታ ደቀ መዛሙርት ላይ በመዛትና እነሱን ለመግደል ቆርጦ በመነሳት+ ወደ ሊቀ ካህናቱ ሄደ፤  የጌታን መንገድ የሚከተሉትን+ በዚያ የሚያገኛቸውን ወንዶችና ሴቶች ሁሉ አስሮ ወደ ኢየሩሳሌም ለማምጣት በደማስቆ ለሚገኙ ምኩራቦች ደብዳቤ እንዲጽፍለት ጠየቀው።  እየተጓዘም ሳለ ወደ ደማስቆ ሲቃረብ ድንገት ከሰማይ የመጣ ብርሃን በዙሪያው አንጸባረቀ፤+  እሱም መሬት ላይ ወደቀ፤ ከዚያም “ሳኦል፣ ሳኦል ለምን ታሳድደኛለህ?” የሚል ድምፅ ሰማ።  ሳኦልም “ጌታዬ፣ አንተ ማን ነህ?” ሲል ጠየቀው። እሱም እንዲህ አለው፦ “እኔ አንተ የምታሳድደኝ+ ኢየሱስ ነኝ።+  አሁን ተነስተህ ወደ ከተማዋ ግባ፤ ምን ማድረግ እንዳለብህም ይነገርሃል።”  አብረው እየተጓዙ የነበሩትም ሰዎች ድምፅ የሰሙ ቢሆንም ማንንም ባለማየታቸው የሚናገሩት ጠፍቷቸው ዝም ብለው ቆሙ።+  ሳኦልም ከወደቀበት ተነሳ፤ ዓይኖቹ ቢገለጡም ምንም ነገር ማየት አልቻለም። በመሆኑም እጁን ይዘው እየመሩ ወደ ደማስቆ ወሰዱት።  ለሦስት ቀንም ምንም ሳያይ+ እንዲሁም ሳይበላና ሳይጠጣ ቆየ። 10  በደማስቆ ሐናንያ የሚባል አንድ ደቀ መዝሙር ነበር፤+ ጌታም በራእይ “ሐናንያ!” አለው። እሱም “ጌታ ሆይ፣ እነሆኝ” አለ። 11  ጌታም እንዲህ አለው፦ “ተነስተህ ‘ቀጥተኛ’ ወደተባለው መንገድ ሂድ፤ በይሁዳም ቤት ሳኦል የሚባለውን የጠርሴስ ሰው+ ፈልግ። እሱም አሁን እየጸለየ ነው፤ 12  ሐናንያ የሚባል ሰው እንደሚመጣና ዓይኑ ይበራለት ዘንድ እጁን እንደሚጭንበት በራእይ አይቷል።”+ 13  ሐናንያ ግን እንዲህ ሲል መለሰ፦ “ጌታ ሆይ፣ ይህ ሰው በኢየሩሳሌም ባሉ ቅዱሳን አገልጋዮችህ ላይ ምን ያህል ጉዳት እንዳደረሰ ከብዙዎች ሰምቻለሁ። 14  ወደዚህ ስፍራ የመጣው ስምህን የሚጠሩትን ሁሉ ለማሰር ከካህናት አለቆች ሥልጣን ተሰጥቶት ነው።”+ 15  ጌታ ግን እንዲህ አለው፦ “ይህ ሰው በአሕዛብ እንዲሁም በነገሥታትና በእስራኤል ልጆች ፊት ስሜን እንዲሸከም+ ለእኔ የተመረጠ ዕቃ+ ስለሆነ ወደ እሱ ሂድ። 16  እኔም ስለ ስሜ ሲል ምን ያህል መከራ መቀበል እንዳለበት በግልጽ አሳየዋለሁ።”+ 17  ስለዚህ ሐናንያ ሄደ፤ ወደተባለውም ቤት ገባ፤ እጁንም በላዩ ጭኖ እንዲህ አለው፦ “ወንድሜ ሳኦል፣ ወደዚህ ስትመጣ መንገድ ላይ የተገለጠልህ ጌታ ኢየሱስ የዓይንህ ብርሃን እንዲመለስልህና በመንፈስ ቅዱስ እንድትሞላ እኔን ልኮኛል።”+ 18  ወዲያውም ከዓይኖቹ ላይ ቅርፊት የሚመስሉ ነገሮች ወደቁ፤ እሱም እንደገና ማየት ቻለ። ከዚያም ተነስቶ ተጠመቀ፤ 19  እንዲሁም ምግብ በልቶ ብርታት አገኘ። በደማስቆ ካሉ ደቀ መዛሙርት ጋር የተወሰኑ ቀናት ቆየ፤+ 20  ወዲያውም ስለ ኢየሱስ እሱ የአምላክ ልጅ እንደሆነ በምኩራቦቹ ውስጥ መስበክ ጀመረ። 21  የሰሙት ሁሉ ግን እጅግ በመደነቅ እንዲህ ይሉ ነበር፦ “ይህ ሰው በኢየሩሳሌም ይህን ስም የሚጠሩትን ሲያጠፋ የነበረው አይደለም?+ ወደዚህስ የመጣው እነሱን እያሰረ ለካህናት አለቆች ለማስረከብ አልነበረም?”+ 22  ሳኦል ግን ይበልጥ እየበረታ ሄደ፤ በደማስቆ የሚኖሩ አይሁዶችን ኢየሱስ እሱ ክርስቶስ እንደሆነ አሳማኝ ማስረጃ እያቀረበ አፋቸውን ያስይዛቸው ነበር።+ 23  በርካታ ቀናት ካለፉ በኋላ አይሁዳውያን እሱን ለመግደል አሴሩ።+ 24  ይሁን እንጂ ሳኦል ሴራቸውን አወቀ። እነሱም ሊገድሉት ስለፈለጉ ቀን ከሌት የከተማዋን በሮች ነቅተው ይጠብቁ ነበር። 25  ስለዚህ የእሱ ደቀ መዛሙርት ሳኦልን ወስደው በሌሊት በከተማዋ ቅጥር ላይ ባለ መስኮት በማሾለክ በቅርጫት አወረዱት።+ 26  ኢየሩሳሌም በደረሰ ጊዜ+ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ለመቀላቀል ጥረት አደረገ፤ እነሱ ግን ደቀ መዝሙር መሆኑን ስላላመኑ ሁሉም ፈሩት። 27  ስለዚህ በርናባስ+ ረዳው፤ ሳኦልንም ወደ ሐዋርያት ወስዶ በመንገድ ላይ ጌታን እንዴት እንዳየውና+ እሱም እንዴት እንዳናገረው እንዲሁም በደማስቆ በኢየሱስ ስም እንዴት በድፍረት እንደተናገረ በዝርዝር ነገራቸው።+ 28  እሱም በኢየሩሳሌም በነፃነት እየተንቀሳቀሰና በጌታ ስም በድፍረት እየተናገረ አብሯቸው ቆየ። 29  ግሪክኛ ተናጋሪ ከሆኑ አይሁዳውያን ጋር ይነጋገርና ይከራከር ነበር፤ እነሱ ግን ሊገድሉት ሞከሩ።+ 30  ወንድሞች ይህን ሲያውቁ ወደ ቂሳርያ ይዘውት ወረዱ፤ ከዚያም ወደ ጠርሴስ ላኩት።+ 31  በዚያ ወቅት በይሁዳ፣ በገሊላና በሰማርያ ያለው ጉባኤ+ ሁሉ ሰላም አገኘ፤ በእምነትም እየጠነከረ ሄደ፤ መላው ጉባኤ ይሖዋን* በመፍራትና መንፈስ ቅዱስ ከሚሰጠው ማጽናኛ+ ጋር በመስማማት ይኖር ስለነበር በቁጥር እየበዛ ሄደ። 32  ጴጥሮስም በየቦታው እየተዘዋወረ በነበረበት ወቅት በልዳ ወደሚኖሩት ቅዱሳን ደግሞ ወረደ።+ 33  በዚያም ሽባ በመሆኑ የተነሳ ለስምንት ዓመት የአልጋ ቁራኛ የሆነ ኤንያስ የተባለ አንድ ሰው አገኘ። 34  ጴጥሮስም “ኤንያስ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ይፈውስሃል።+ ተነሳና አልጋህን አንጥፍ” አለው።+ እሱም ወዲያውኑ ተነሳ። 35  በልዳ እና በሳሮን ሜዳ የሚኖሩ ሁሉ እሱን አይተው በጌታ አመኑ። 36  በኢዮጴ ጣቢታ የምትባል አንዲት ደቀ መዝሙር ነበረች፤ የስሟም ትርጉም “ዶርቃ”* ማለት ነው። እሷም መልካም በማድረግና ምጽዋት በመስጠት የምትታወቅ ነበረች። 37  በዚያን ጊዜም ታማ ሞተች። ሰዎችም አጠቧትና በደርብ ላይ በሚገኘው ክፍል ውስጥ አስቀመጧት። 38  ልዳ ለኢዮጴ ቅርብ ስለነበረች ደቀ መዛሙርቱ ጴጥሮስ በዚያች ከተማ እንዳለ ሲሰሙ “እባክህ ፈጥነህ ወደ እኛ ና” ብለው እንዲለምኑት ሁለት ሰዎች ወደ እሱ ላኩ። 39  በዚህ ጊዜ ጴጥሮስ ተነስቶ አብሯቸው ሄደ። እዚያም ሲደርስ ደርብ ላይ ወደሚገኘው ክፍል ይዘውት ወጡ፤ መበለቶቹም ሁሉ በዙሪያው ቆመው እያለቀሱ ዶርቃ ከእነሱ ጋር በነበረችበት ጊዜ የሠራቻቸውን በርካታ ልብሶችና ቀሚሶች* ያሳዩት ነበር። 40  ጴጥሮስም ሁሉም እንዲወጡ ካደረገ በኋላ+ ተንበርክኮ ጸለየ። ከዚያም ወደ አስከሬኑ ዞር ብሎ “ጣቢታ፣ ተነሽ!” አለ። እሷም ዓይኖቿን ገለጠች፤ ጴጥሮስንም ባየች ጊዜ ቀና ብላ ተቀመጠች።+ 41  እሱም እጇን ይዞ አስነሳት፤ ቅዱሳኑንና መበለቶቹንም ጠርቶ ሕያው መሆኗን አሳያቸው።+ 42  ይህ ነገር በመላው ኢዮጴ ታወቀ፤ ብዙዎችም በጌታ አመኑ።+ 43  ጴጥሮስም በኢዮጴ ስምዖን በተባለ አንድ ቆዳ ፋቂ ቤት ለበርካታ ቀናት ተቀመጠ።+

የግርጌ ማስታወሻ

ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
“ዶርቃ” ግሪክኛ ሲሆን “ጣቢታ” ደግሞ አረማይክ ነው፤ የሁለቱም ትርጉም “የሜዳ ፍየል” ማለት ነው።
ወይም “መደረቢያዎች።”