የይሁዳ ደብዳቤ 1:1-25
1 የኢየሱስ ክርስቶስ ባሪያና የያዕቆብ+ ወንድም ከሆነው ከይሁዳ፣ ለተጠሩትና+ አባታችን በሆነው አምላክ ለተወደዱት እንዲሁም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ይሆኑ ዘንድ ጥበቃ ለተደረገላቸው፦+
2 ምሕረት፣ ሰላምና ፍቅር ይብዛላችሁ።
3 የተወደዳችሁ ወንድሞች፣ ሁላችንም ስለምናገኘው መዳን+ ልጽፍላችሁ እጅግ ጓጉቼ የነበረ ቢሆንም ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለቅዱሳን ስለተሰጠው እምነት ብርቱ ተጋድሎ እንድታደርጉ+ ለማሳሰብ ልጽፍላችሁ ተገደድኩ።
4 ይህን ያደረግኩት ፍርድ እንደሚጠብቃቸው በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ አስቀድሞ የተነገረላቸው አንዳንድ ሰዎች ሾልከው ስለገቡ ነው፤ እነዚህ ሰዎች ፈሪሃ አምላክ የሌላቸው፣ በአምላካችን ጸጋ እያሳበቡ ማንአለብኝነት የሚንጸባረቅበት ድርጊት*+ የሚፈጽሙ እንዲሁም የዋጀንንና እሱ ብቻ ጌታችን* የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን የሚክዱ ናቸው።+
5 ምንም እንኳ ይህን ሁሉ አስቀድማችሁ በሚገባ ታውቁ የነበረ ቢሆንም ይሖዋ* ሕዝቡን ከግብፅ ምድር እንዳዳነ፣+ በኋላም እምነት ያላሳዩትን እንዳጠፋ ላስታውሳችሁ እወዳለሁ።+
6 በተጨማሪም መጀመሪያ የነበራቸውን ቦታ ያልጠበቁትንና ተገቢ የሆነውን የመኖሪያ ስፍራቸውን የተዉትን መላእክት+ በታላቁ ቀን ለሚፈጸምባቸው ፍርድ በዘላለም እስራት በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ አቆይቷቸዋል።+
7 በተመሳሳይም ሰዶምና ገሞራ እንዲሁም በዙሪያቸው የነበሩ ከተሞች ራሳቸውን ልቅ ለሆነ የፆታ ብልግና* አሳልፈው የሰጡ ከመሆኑም ሌላ ከተፈጥሮ ውጭ የሆነ የሥጋ ፍላጎታቸውን ያሳድዱ ነበር፤+ በመሆኑም በዘላለም እሳት ፍርድ ተቀጥተው ለእኛ የማስጠንቀቂያ ምሳሌ ሆነዋል።+
8 ያም ሆኖ ግን እነዚህ ሕልም አላሚዎች ሥጋን ያረክሳሉ፤ ሥልጣንን ይንቃሉ፤ የተከበሩትንም ይሳደባሉ።+
9 ይሁንና የመላእክት አለቃ+ ሚካኤል+ የሙሴን ሥጋ+ በተመለከተ ከዲያብሎስ ጋር በተከራከረ ጊዜ የስድብ ቃል በመናገር ሊፈርድበት አልደፈረም፤+ ከዚህ ይልቅ “ይሖዋ* ይገሥጽህ” አለው።+
10 እነዚህ ሰዎች ግን ስለማያውቁት ነገር ሁሉ ትችት ይሰነዝራሉ።+ ደግሞም አእምሮ እንደሌላቸው እንስሳት፣+ በደመ ነፍስ የሚረዷቸውን ነገሮች ሁሉ ሲያደርጉ የራሳቸውን ሥነ ምግባር ያበላሻሉ።
11 በቃየን+ መንገድ ስለሄዱ፣ ለጥቅም ሲሉ የበለዓምን+ የተሳሳተ መንገድ በጭፍን ስለተከተሉና በቆሬ+ የዓመፅ ንግግር+ ስለጠፉ ወዮላቸው!
12 እነዚህ ሰዎች ፍቅራችሁን ለመግለጽ በምታዘጋጁት ግብዣ ላይ ተገኝተው አብረዋችሁ ሲመገቡ ልክ በባሕር ውስጥ እንደተደበቀ ዓለት+ ከመሆናቸውም ሌላ ያላንዳች ኀፍረት ለሆዳቸው ብቻ የሚያስቡ እረኞች ናቸው፤+ በነፋስ ወዲያና ወዲህ የሚነዱ ዝናብ የሌላቸው ደመናዎች+ እንዲሁም በመከር ጊዜ ፍሬ የማይገኝባቸው፣ ሁለት ጊዜ የሞቱና* ከሥራቸው የተነቀሉ ዛፎች ናቸው፤
13 አረፋ እንደሚደፍቅ ኃይለኛ የባሕር ማዕበል አሳፋሪ ድርጊታቸውን ይገልጣሉ፤+ ለዘላለም ድቅድቅ ጨለማ ውስጥ የሚጣሉ ተንከራታች ከዋክብት ናቸው።+
14 ከአዳም ጀምሮ ሰባተኛ ትውልድ የሆነው ሄኖክ+ ስለ እነዚህ ሰዎች እንዲህ ሲል ተንብዮአል፦ “እነሆ! ይሖዋ* ከአእላፋት* ቅዱሳን መላእክቱ ጋር መጥቷል፤+
15 የመጣውም በሁሉ ላይ ለመፍረድ፣+ ፈሪሃ አምላክ የሌላቸው ሰዎች ለአምላክ አክብሮት በጎደለው መንገድ የፈጸሙትን ክፉ ድርጊትና ፈሪሃ አምላክ የሌላቸው ኃጢአተኞች በእሱ ላይ የተናገሩትን ክፉ ቃል ለማጋለጥ ነው።”+
16 እነዚህ ሰዎች የሚያጉረመርሙና+ ኑሯቸውን የሚያማርሩ እንዲሁም የራሳቸውን ምኞት የሚከተሉ ናቸው፤+ ጉራ መንዛት ይወዳሉ፤ ለጥቅማቸው ሲሉም ሌሎችን ይክባሉ።+
17 የተወደዳችሁ ወንድሞች፣ እናንተ ግን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያት አስቀድመው የነገሯችሁን ቃል* አስታውሱ፤
18 እነሱ “በመጨረሻው ዘመን መጥፎ ምኞታቸውን የሚከተሉ ዘባቾች ይነሳሉ” ይሏችሁ ነበር።+
19 እነዚህ ሰዎች ክፍፍል የሚፈጥሩ፣+ የእንስሳ ባሕርይ ያላቸውና* መንፈሳዊ ያልሆኑ* ናቸው።
20 የተወደዳችሁ ወንድሞች፣ እናንተ ግን እጅግ ቅዱስ በሆነው እምነታችሁ ላይ ራሳችሁን ገንቡ፤ እንዲሁም በመንፈስ ቅዱስ ጸልዩ፤+
21 ይህን የምታደርጉት የዘላለም ሕይወት የሚያስገኝላችሁን+ የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ምሕረት እየተጠባበቃችሁ ከአምላክ ፍቅር ሳትወጡ እንድትኖሩ ነው።+
22 በተጨማሪም ጥርጣሬ ላደረባቸው+ ምሕረት አሳዩ፤+
23 ከእሳት ነጥቃችሁ በማውጣት አድኗቸው።+ ለሌሎች ምሕረት ማሳየታችሁንም ቀጥሉ፤ ሆኖም ይህን ስታደርጉ ለራሳችሁ መጠንቀቅና በሥጋ ሥራ ያደፈውን ልብሳቸውን መጥላት ይኖርባችኋል።+
24 እንዳትሰናከሉ ሊጠብቃችሁና ነቀፋ የሌለባችሁ አድርጎ በታላቅ ደስታ፣ በክብሩ ፊት ሊያቆማችሁ ለሚችለው፣+
25 አዳኛችን ለሆነው ብቸኛው አምላክ ከዘመናት ሁሉ በፊት፣ አሁንና እስከ ዘላለም በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ክብር፣ ግርማ፣ ኃይልና ሥልጣን ይሁን። አሜን።