የዮሐንስ ወንጌል 10:1-42

  • እረኛውና ሁለት የበጎች ጉረኖ (1-21)

    • ኢየሱስ ጥሩ እረኛ ነው (11-15)

    • “ሌሎች በጎች አሉኝ” (16)

  • የመታደስ በዓል ሲከበር አይሁዳውያን ከኢየሱስ ጋር ተገናኙ (22-39)

    • ብዙ አይሁዳውያን አላመኑም (24-26)

    • “በጎቼ ድምፄን ይሰማሉ” (27)

    • “እኔና አብ አንድ ነን” (30, 38)

  • በዮርዳኖስ ማዶ የሚገኙ ብዙ ሰዎች አመኑ (40-42)

10  “እውነት እውነት እላችኋለሁ፣ በበሩ ሳይሆን በሌላ በኩል ዘሎ ወደ በጎቹ ጉረኖ የሚገባ ሌባና ዘራፊ ነው።+  በበሩ በኩል የሚገባ ግን የበጎቹ እረኛ ነው።+  በር ጠባቂውም ለእሱ ይከፍትለታል፤+ በጎቹም ድምፁን ይሰማሉ።+ የራሱን በጎች በየስማቸው ጠርቶ እየመራ ያወጣቸዋል።  የራሱ የሆኑትን ሁሉ ካወጣ በኋላ ከፊት ከፊታቸው ይሄዳል፤ በጎቹም ድምፁን ስለሚያውቁ ይከተሉታል።  እንግዳ የሆነውን ግን ይሸሹታል እንጂ በምንም ዓይነት አይከተሉትም፤ ምክንያቱም የእንግዳ ሰዎችን ድምፅ አያውቁም።”  ኢየሱስ ይህን ምሳሌ ነገራቸው፤ እነሱ ግን ምን እያላቸው እንዳለ አልገባቸውም።  ስለዚህ ኢየሱስ እንደገና እንዲህ አለ፦ “እውነት እውነት እላችኋለሁ፣ በጎቹ የሚገቡበት በር እኔ ነኝ።+  አስመሳይ ሆነው በእኔ ስም የመጡ ሁሉ ሌቦችና ዘራፊዎች ናቸው፤ በጎቹ ግን አልሰሟቸውም።  በሩ እኔ ነኝ፤ በእኔ በኩል የሚገባ ሁሉ ይድናል፤ ይገባል፤ ይወጣል፤ መሰማሪያም ያገኛል።+ 10  ሌባው ለመስረቅ፣ ለመግደልና ለማጥፋት ካልሆነ በቀር ለሌላ አይመጣም።+ እኔ የመጣሁት ሕይወት እንዲኖራቸውና እንዲትረፈረፍላቸው ነው። 11  እኔ ጥሩ እረኛ ነኝ፤+ ጥሩ እረኛ ሕይወቱን* ለበጎቹ ሲል አሳልፎ ይሰጣል።+ 12  እረኛ ያልሆነና በጎቹ የራሱ ያልሆኑ ተቀጣሪ ሠራተኛ ተኩላ ሲመጣ ሲያይ በጎቹን ጥሎ ይሸሻል (ተኩላውም በጎቹን ይነጥቃል እንዲሁም ይበታትናል)፤ 13  ሠራተኛው እንዲህ የሚያደርገው ተቀጣሪ ስለሆነና ለበጎቹ ደንታ ስለሌለው ነው። 14  እኔ ጥሩ እረኛ ነኝ። በጎቼን አውቃቸዋለሁ፤ በጎቼም ያውቁኛል፤+ 15  ይህም አብ እኔን እንደሚያውቀኝና እኔም አብን እንደማውቀው ነው፤+ ሕይወቴንም* ለበጎቹ ስል አሳልፌ እሰጣለሁ።+ 16  “ከዚህ ጉረኖ ያልሆኑ ሌሎች በጎች አሉኝ፤+ እነሱንም ማምጣት አለብኝ፤ ድምፄንም ይሰማሉ፤ ሁሉም አንድ መንጋ ይሆናሉ፤ አንድ እረኛም ይኖራቸዋል።+ 17  ሕይወቴን* መልሼ አገኛት ዘንድ አሳልፌ ስለምሰጣት+ አብ ይወደኛል።+ 18  በራሴ ተነሳስቼ አሳልፌ እሰጣታለሁ እንጂ ማንም ሰው ከእኔ አይወስዳትም። ሕይወቴን* አሳልፌ ለመስጠት ሥልጣን አለኝ፤ መልሼ ለመቀበልም ሥልጣን አለኝ።+ ይህን ትእዛዝ የተቀበልኩት ከአባቴ ነው።” 19  ከዚህ ንግግር የተነሳ በአይሁዳውያኑ መካከል እንደገና ክፍፍል ተፈጠረ።+ 20  ብዙዎቹም “ይህ ሰው ጋኔን አለበት፤ አእምሮውን ስቷል። ለምን ትሰሙታላችሁ?” አሉ። 21  ሌሎቹ ደግሞ “ጋኔን የያዘው ሰው እንዲህ አይናገርም። ጋኔን የዓይነ ስውራንን ዓይን ሊከፍት ይችላል እንዴ?” አሉ። 22  በዚያ ጊዜ በኢየሩሳሌም የመታደስ በዓል* ይከበር ነበር። ወቅቱም ክረምት ነበር፤ 23  ኢየሱስም በቤተ መቅደሱ በሚገኘውና መጠለያ ባለው የሰለሞን መተላለፊያ+ ውስጥ እያለፈ ነበር። 24  በዚህ ጊዜ አይሁዳውያን ከበውት “እስከ መቼ ድረስ ልባችንን* ታንጠለጥላለህ? አንተ ክርስቶስ ከሆንክ በግልጽ ንገረን” አሉት። 25  ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “እኔ ነግሬአችኋለሁ፤ እናንተ ግን አታምኑም። በአባቴ ስም እየሠራኋቸው ያሉት ሥራዎች ስለ እኔ ይመሠክራሉ።+ 26  ሆኖም እናንተ በጎቼ ስላልሆናችሁ አታምኑም።+ 27  በጎቼ ድምፄን ይሰማሉ፤ እኔም አውቃቸዋለሁ፤ እነሱም ይከተሉኛል።+ 28  የዘላለም ሕይወት እሰጣቸዋለሁ፤+ መቼም ቢሆን ጥፋት አይደርስባቸውም፤ ከእጄ የሚነጥቃቸውም የለም።+ 29  አባቴ የሰጠኝ በጎች ከሌሎች ነገሮች ሁሉ ይበልጣሉ፤ እነሱንም ከአባቴ እጅ ሊነጥቃቸው የሚችል የለም።+ 30  እኔና አብ አንድ ነን።”*+ 31  በዚህ ጊዜም አይሁዳውያኑ ሊወግሩት ድንጋይ አነሱ። 32  ኢየሱስም መልሶ “ከአብ ዘንድ ብዙ መልካም ሥራዎች አሳየኋችሁ። ታዲያ የምትወግሩኝ ከእነዚህ ሥራዎች መካከል በየትኛው የተነሳ ነው?” አላቸው። 33  አይሁዳውያኑም “እኛ የምንወግርህ ስለ መልካም ሥራህ ሳይሆን አንተ ሰው ሆነህ ሳለህ ራስህን አምላክ በማድረግ አምላክን ስለተዳፈርክ ነው”+ ሲሉ መለሱለት። 34  ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “በሕጋችሁ ላይ ‘“እናንተ አማልክት* ናችሁ” አልኩ’+ ተብሎ ተጽፎ የለም? 35  የአምላክ ቃል ያወገዛቸውን እሱ ‘አማልክት’+ ብሎ ከጠራቸውና ቅዱስ መጽሐፉ ሊሻር የማይችል ከሆነ 36  አብ የቀደሰኝንና ወደ ዓለም የላከኝን እኔን፣ ‘የአምላክ ልጅ ነኝ’+ ስላልኩ ‘አምላክን ትዳፈራለህ’ ትሉኛላችሁ? 37  እኔ የአባቴን ሥራ እየሠራሁ ካልሆነ አትመኑኝ። 38  የአባቴን ሥራ እየሠራሁ ከሆነ ግን እኔን ባታምኑኝ እንኳ ሥራዬን እመኑ፤+ ይህም አብ ከእኔ ጋር አንድነት እንዳለው እንዲሁም እኔም ከአብ ጋር አንድነት እንዳለኝ እንድታውቁና ይህን ይበልጥ እያወቃችሁ እንድትሄዱ ነው።”+ 39  ስለዚህ እንደገና ሊይዙት ሞከሩ፤ እሱ ግን አመለጣቸው። 40  ከዚያም ዮሐንስ ቀደም ሲል ያጠምቅ ወደነበረበት ከዮርዳኖስ ማዶ ወዳለው ቦታ+ ዳግመኛ ሄደ፤ በዚያም ለተወሰነ ጊዜ ቆየ። 41  ብዙ ሰዎችም ወደ እሱ መጥተው እርስ በርሳቸው “ዮሐንስ አንድም ተአምራዊ ምልክት አላደረገም፤ ሆኖም ዮሐንስ ስለዚህ ሰው የተናገረው ነገር ሁሉ እውነት ነበር” ተባባሉ።+ 42  በዚያም ብዙዎች በእሱ አመኑ።

የግርጌ ማስታወሻ

ወይም “ነፍሱን።”
ወይም “ነፍሴንም።”
ወይም “ነፍሴን።”
ወይም “ነፍሴን።”
ወይም “ቤተ መቅደሱ ለአምላክ የተወሰነበት በዓል (ሃኑካ)።”
ወይም “ነፍሳችንን።”
ወይም “እኔና አብ አንድነት አለን።”
ወይም “እንደ አምላክ ያላችሁ።”