የዮሐንስ ወንጌል 14:1-31

  • ወደ አብ መቅረብ የሚቻልበት ብቸኛው መንገድ ኢየሱስ ነው (1-14)

    • “እኔ መንገድ፣ እውነትና ሕይወት ነኝ” (6)

  • ኢየሱስ መንፈስ ቅዱስን እንደሚልክ ቃል ገባ (15-31)

    • “ከእኔ አብ ይበልጣል” (28)

14  “ልባችሁ አይረበሽ።+ በአምላክ እመኑ፤+ በእኔም ደግሞ እመኑ።  በአባቴ ቤት ብዙ መኖሪያ ቦታ አለ። ይህ ባይሆን ኖሮ በግልጽ እነግራችሁ ነበር፤ ለእናንተ ቦታ ለማዘጋጀት እሄዳለሁና።+  ደግሞም ሄጄ ቦታ ባዘጋጀሁላችሁ ጊዜ እኔ ባለሁበት እናንተም እንድትሆኑ እንደገና መጥቼ እኔ ወዳለሁበት እወስዳችኋለሁ።*+  እኔ ወደምሄድበትም ቦታ የሚወስደውን መንገድ ታውቃላችሁ።”  ቶማስም+ “ጌታ ሆይ፣ ወዴት እንደምትሄድ አናውቅም። ታዲያ መንገዱን እንዴት ማወቅ እንችላለን?” አለው።  ኢየሱስም እንዲህ አለው፦ “እኔ መንገድ፣+ እውነትና+ ሕይወት+ ነኝ። በእኔ በኩል ካልሆነ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም።+  እኔን ብታውቁኝ ኖሮ አባቴንም ታውቁት ነበር፤ ከዚህ ጊዜ አንስቶ ታውቁታላችሁ፤ ደግሞም አይታችሁታል።”+  ፊልጶስም “ጌታ ሆይ፣ አብን አሳየንና ይበቃናል” አለው።  ኢየሱስም እንዲህ አለው፦ “ፊልጶስ፣ ከእናንተ ጋር ይህን ያህል ረጅም ጊዜ ኖሬም እንኳ አላወቅከኝም? እኔን ያየ ሁሉ አብንም አይቷል።+ ታዲያ እንዴት ‘አብን አሳየን’ ትላለህ? 10  እኔ ከአብ ጋር አንድነት እንዳለኝና አብ ከእኔ ጋር አንድነት እንዳለው አታምንም?+ የምነግራችሁን ነገር የምናገረው ከራሴ አመንጭቼ አይደለም፤+ ሆኖም ሥራውን እየሠራ ያለው ከእኔ ጋር አንድነት ያለው አብ ነው። 11  እኔ ከአብ ጋር አንድነት እንዳለኝ አብም ከእኔ ጋር አንድነት እንዳለው እመኑኝ፤ ካልሆነ ደግሞ ከተሠሩት ሥራዎች የተነሳ እመኑ።+ 12  እውነት እውነት እላችኋለሁ፣ በእኔ የሚያምን ሁሉ እኔ የምሠራቸውን ሥራዎች ይሠራል፤ እንዲያውም እኔ ወደ አብ ስለምሄድ+ እሱ ከእነዚህ የበለጡ ሥራዎች ይሠራል።+ 13  በተጨማሪም አብ በወልድ አማካኝነት እንዲከበር በስሜ የምትለምኑትን ሁሉ አደርገዋለሁ።+ 14  ማንኛውንም ነገር በስሜ ከለመናችሁ እኔ አደርገዋለሁ። 15  “የምትወዱኝ ከሆነ ትእዛዛቴን ትጠብቃላችሁ።+ 16  እኔም አብን እጠይቃለሁ፤ እሱም ለዘላለም ከእናንተ ጋር የሚሆን ሌላ ረዳት* ይሰጣችኋል፤+ 17  እሱም የእውነት መንፈስ ነው፤+ ዓለም ስለማያየውና ስለማያውቀው ሊቀበለው አይችልም።+ እናንተ ግን አብሯችሁ ስለሚኖርና በውስጣችሁ ስላለ ታውቁታላችሁ። 18  ሐዘን ላይ* ትቻችሁ አልሄድም። ወደ እናንተ እመጣለሁ።+ 19  ከጥቂት ጊዜ በኋላ ዓለም ከቶ አያየኝም፤ እናንተ ግን ታዩኛላችሁ፤+ ምክንያቱም እኔ እኖራለሁ፤ እናንተም ትኖራላችሁ። 20  እኔ ከአባቴ ጋር አንድነት እንዳለኝ፣ እናንተ ከእኔ ጋር አንድነት እንዳላችሁና እኔም ከእናንተ ጋር አንድነት እንዳለኝ በዚያን ቀን ታውቃላችሁ።+ 21  እኔን የሚወደኝ ትእዛዛቴን የሚቀበልና የሚጠብቅ ነው። እኔን የሚወደኝን ሁሉ ደግሞ አባቴ ይወደዋል፤ እኔም እወደዋለሁ፤ ራሴንም እገልጥለታለሁ።” 22  የአስቆሮቱ ሳይሆን ሌላው ይሁዳ+ “ጌታ ሆይ፣ ለዓለም ሳይሆን ለእኛ ራስህን ለመግለጥ ያሰብከው ለምንድን ነው?” አለው። 23  ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰለት፦ “ማንም ሰው እኔን የሚወደኝ ከሆነ ቃሌን ይጠብቃል፤+ አባቴም ይወደዋል፣ እኛም ወደ እሱ መጥተን መኖሪያችንን ከእሱ ጋር እናደርጋለን።+ 24  እኔን የማይወደኝ ሁሉ ቃሌን አይጠብቅም። ይህ እየሰማችሁት ያለው ቃል ደግሞ የላከኝ የአብ ነው እንጂ የእኔ አይደለም።+ 25  “አሁን ከእናንተ ጋር እያለሁ እነዚህን ነገሮች ነግሬአችኋለሁ። 26  ሆኖም አብ በስሜ የሚልከው ረዳት* ይኸውም መንፈስ ቅዱስ ሁሉንም ነገር ያስተምራችኋል እንዲሁም የነገርኳችሁን ነገር ሁሉ እንድታስታውሱ ያደርጋችኋል።+ 27  ሰላምን እተውላችኋለሁ፤ ሰላሜን እሰጣችኋለሁ።+ እኔ ሰላም የምሰጣችሁ ዓለም በሚሰጥበት መንገድ አይደለም። ልባችሁ አይረበሽ፤ በፍርሃትም አይዋጥ። 28  ‘እሄዳለሁ ወደ እናንተም ተመልሼ እመጣለሁ’ እንዳልኳችሁ ሰምታችኋል። ብትወዱኝስ ወደ አብ በመሄዴ ደስ ባላችሁ ነበር፤ ከእኔ አብ ይበልጣልና።+ 29  በመሆኑም በሚፈጸምበት ጊዜ እንድታምኑ ከመፈጸሙ በፊት አሁን ነግሬአችኋለሁ።+ 30  የዚህ ዓለም ገዢ+ እየመጣ ስለሆነ ከዚህ በኋላ ከእናንተ ጋር ብዙ አልነጋገርም፤ እሱም በእኔ ላይ ምንም ኃይል የለውም።+ 31  ይሁን እንጂ እኔ አብን እንደምወድ ዓለም እንዲያውቅ አብ ባዘዘኝ መሠረት+ እየሠራሁ ነው። ተነሱ ከዚህ እንሂድ።

የግርጌ ማስታወሻ

ወይም “ወደ ቤቴ እወስዳችኋለሁ።”
ወይም “አጽናኝ።”
ወይም “ወላጅ አልባ እንደሆኑ ልጆች።”
ወይም “አጽናኝ።”