የዮሐንስ ወንጌል 16:1-33

  • የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ሊገደሉ ይችላሉ (1-4ሀ)

  • መንፈስ ቅዱስ የሚያከናውነው ሥራ (4ለ-16)

  • የደቀ መዛሙርቱ ሐዘን ወደ ደስታ ይለወጣል (17-24)

  • “እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ” (25-33)

16  “ይህን ሁሉ የነገርኳችሁ እንዳትሰናከሉ ብዬ ነው።  ሰዎች ከምኩራብ ያባርሯችኋል።+ እንዲያውም እናንተን የሚገድል+ ሁሉ ለአምላክ ቅዱስ አገልግሎት እንዳቀረበ አድርጎ የሚያስብበት ሰዓት ይመጣል።  ሆኖም እነዚህን ነገሮች የሚያደርጉት አብንም ሆነ እኔን ስላላወቁ ነው።+  ይሁንና እነዚህን ነገሮች የነገርኳችሁ የሚፈጸሙበት ሰዓት ሲደርስ አስቀድሜ ነግሬአችሁ እንደነበረ እንድታስታውሱ ነው።+ “ከእናንተ ጋር ስለነበርኩ እነዚህን ነገሮች በመጀመሪያ አልነገርኳችሁም።  አሁን ግን ወደ ላከኝ ልሄድ ነው፤+ ሆኖም ከመካከላችሁ ‘ወዴት ነው የምትሄደው?’ ብሎ የጠየቀኝ የለም።  እነዚህን ነገሮች ስለነገርኳችሁ ልባችሁ በሐዘን ተሞልቷል።+  ይሁንና እውነቱን ለመናገር እኔ የምሄደው ለእናንተው ጥቅም ነው። ምክንያቱም እኔ ካልሄድኩ ረዳቱ*+ በምንም ዓይነት ወደ እናንተ አይመጣም፤ ከሄድኩ ግን እሱን ወደ እናንተ እልከዋለሁ።  እሱ ሲመጣ ስለ ኃጢአት፣ ስለ ጽድቅና ስለ ፍርድ ለዓለም አሳማኝ ማስረጃ ያቀርባል፦  በመጀመሪያ ደረጃ ስለ ኃጢአት+ የተባለው፣ ሰዎች በእኔ ስላላመኑ ነው፤+ 10  ከዚያም ስለ ጽድቅ የተባለው፣ እኔ ወደ አብ ስለምሄድና እናንተ ከእንግዲህ ስለማታዩኝ ነው፤ 11  ስለ ፍርድ የተባለው ደግሞ የዚህ ዓለም ገዢ ስለተፈረደበት ነው።+ 12  “ገና ብዙ የምነግራችሁ ነገር አለኝ፤ አሁን ግን ልትሸከሙት አትችሉም። 13  ይሁን እንጂ እሱ* ይኸውም የእውነት መንፈስ+ ሲመጣ ወደ እውነት ሁሉ ይመራችኋል፤ ምክንያቱም የሚናገረው ከራሱ አመንጭቶ አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ የሰማውን ይናገራል፤ እንዲሁም ወደፊት የሚሆኑትን ነገሮች ያሳውቃችኋል።+ 14  የሚያሳውቃችሁ+ የእኔ ከሆነው ወስዶ ስለሆነ እሱ እኔን ያከብረኛል።+ 15  አብ ያለው ነገር ሁሉ የእኔ ነው።+ የእኔ ከሆነው ወስዶ ያሳውቃችኋል ያልኳችሁ ለዚህ ነው። 16  ከጥቂት ጊዜ በኋላ አታዩኝም፤+ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ደግሞ ታዩኛላችሁ።” 17  በዚህ ጊዜ ከደቀ መዛሙርቱ አንዳንዶቹ እርስ በርሳቸው “‘ከጥቂት ጊዜ በኋላ አታዩኝም፤ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ደግሞ ታዩኛላችሁ’ እንዲሁም ‘ወደ አብ ልሄድ ነውና’ ሲለን ምን ማለቱ ነው?” ተባባሉ። 18  ስለዚህ “‘ከጥቂት ጊዜ በኋላ’ ሲል ምን ማለቱ ነው? ስለ ምን ነገር እየተናገረ እንደሆነ አልገባንም” አሉ። 19  ኢየሱስ ሊጠይቁት እንደፈለጉ ተረድቶ እንዲህ አላቸው፦ “እርስ በርሳችሁ ስለዚህ ጉዳይ የምትጠያየቁት ‘ከጥቂት ጊዜ በኋላ አታዩኝም፤ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ደግሞ ታዩኛላችሁ’ ስላልኩ ነው? 20  እውነት እውነት እላችኋለሁ፣ እናንተ ታለቅሳላችሁ እንዲሁም ዋይ ዋይ ትላላችሁ፤ ዓለም ግን ይደሰታል፤ እናንተ ታዝናላችሁ፤ ሆኖም ሐዘናችሁ ወደ ደስታ ይለወጣል።+ 21  አንዲት ሴት የመውለጃዋ ሰዓት ደርሶ ስታምጥ ትጨነቃለች፤ ሕፃኑን ከወለደች በኋላ ግን አንድ ሰው ወደ ዓለም በመምጣቱ ከደስታዋ የተነሳ ሥቃይዋን ሁሉ ትረሳለች። 22  ስለዚህ እናንተም አሁን አዝናችኋል፤ ሆኖም እንደገና ስለማያችሁ ልባችሁ በደስታ ይሞላል፤+ ደስታችሁን ደግሞ ማንም አይነጥቃችሁም። 23  በዚያን ጊዜ እኔን ምንም ጥያቄ አትጠይቁኝም። እውነት እውነት እላችኋለሁ፣ አብን ማንኛውንም ነገር በስሜ ብትጠይቁት+ ይሰጣችኋል።+ 24  እስካሁን ድረስ በስሜ አንድም ነገር አልጠየቃችሁም። ደስታችሁ የተሟላ እንዲሆን ጠይቁ፤ ትቀበላላችሁ። 25  “እነዚህን ነገሮች የነገርኳችሁ በምሳሌ ነው። ይሁንና ለእናንተ በምሳሌ የማልናገርበት ሰዓት ይመጣል፤ ከዚህ ይልቅ ስለ አብ በግልጽ እነግራችኋለሁ። 26  በዚያ ቀን አብን በስሜ ትለምናላችሁ፤ ይህን ስል ስለ እናንተ አብን እጠይቃለሁ ማለቴ አይደለም። 27  ምክንያቱም እናንተ እኔን ስለወደዳችሁኝና+ የአምላክ ተወካይ ሆኜ እንደመጣሁ ስላመናችሁ+ አብ ራሱ ይወዳችኋል። 28  እኔ የአብ ተወካይ ሆኜ ወደ ዓለም መጥቻለሁ። አሁን ደግሞ ዓለምን ትቼ ወደ አብ ልሄድ ነው።”+ 29  ደቀ መዛሙርቱም እንዲህ አሉ፦ “አሁን እኮ በግልጽ እየተናገርክ ነው፤ በምሳሌም አልተናገርክም። 30  አሁን ሁሉን ነገር እንደምታውቅና ማንም ጥያቄ እስኪጠይቅህ ድረስ መጠበቅ እንደማያስፈልግህ ተረዳን። ስለሆነም ከአምላክ ዘንድ እንደመጣህ እናምናለን።” 31  ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “አሁን አመናችሁ? 32  እነሆ፣ ሁላችሁም ወደየቤታችሁ የምትበታተኑበትና እኔን ብቻዬን ትታችሁ የምትሄዱበት ሰዓት ቀርቧል፤+ እንዲያውም ደርሷል። ይሁንና አብ ከእኔ ጋር ስላለ ብቻዬን አይደለሁም።+ 33  እነዚህን ነገሮች የነገርኳችሁ በእኔ አማካኝነት ሰላም እንዲኖራችሁ ነው።+ በዓለም ሳላችሁ መከራ ይደርስባችኋል፤ ነገር ግን አይዟችሁ! እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ።”+

የግርጌ ማስታወሻ

ወይም “አጽናኙ።”
ዮሐ 16:13, 14 ላይ የተጠቀሰው “እሱ” የሚለው ቃል፣ ቁጥር 7 ላይ “ረዳቱ” ተብሎ የተጠቀሰውን ያመለክታል። ኢየሱስ “ረዳቱ” (እዚህ ላይ በግሪክኛ በተባዕታይ ፆታ ተጠቅሷል) የሚለውን ቃል የተጠቀመው አካል የሌለውን ኃይል ይኸውም መንፈስ ቅዱስን በሰውኛ ዘይቤ ለመግለጽ ነው፤ ግሪክኛው ቋንቋ መንፈስ ቅዱስን ሲገልጽ ተባዕታይም ሆነ አንስታይ ፆታ አይጠቀምም።