የዮሐንስ ወንጌል 3:1-36

  • ኢየሱስና ኒቆዲሞስ (1-21)

    • ዳግመኛ መወለድ (3-8)

    • አምላክ ዓለምን ወዷል (16)

  • ዮሐንስ ስለ ኢየሱስ የሰጠው የመጨረሻ ምሥክርነት (22-30)

  • ከላይ የመጣው (31-36)

3  ከፈሪሳውያን ወገን፣ የአይሁዳውያን ገዢ የሆነ ኒቆዲሞስ+ የሚባል ሰው ነበር።  ይህ ሰው በማታ ወደ ኢየሱስ መጥቶ+ እንዲህ አለው፦ “ረቢ፣+ አንተ ከአምላክ ዘንድ የመጣህ አስተማሪ እንደሆንክ እናውቃለን፤ ምክንያቱም አምላክ ከእሱ ጋር ካልሆነ በቀር+ አንተ የምትፈጽማቸውን ተአምራዊ ምልክቶች መፈጸም የሚችል አንድም ሰው የለም።”+  ኢየሱስም መልሶ “እውነት እውነት እልሃለሁ፣ አንድ ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ*+ በቀር የአምላክን መንግሥት ሊያይ አይችልም”+ አለው።  ኒቆዲሞስም “ሰው ከሸመገለ በኋላ እንዴት ሊወለድ ይችላል? ዳግም ወደ እናቱ ማህፀን ገብቶ ሊወለድ ይችላል?” አለው።  ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰ፦ “እውነት እውነት እልሃለሁ፣ ሰው ከውኃና+ ከመንፈስ+ ካልተወለደ በቀር ወደ አምላክ መንግሥት ሊገባ አይችልም።  ከሥጋ የተወለደ ሥጋ ነው፤ ከመንፈስ የተወለደ ደግሞ መንፈስ ነው።  ‘ዳግመኛ መወለድ አለባችሁ’ ስላልኩህ አትገረም።  ነፋስ ወደፈለገው አቅጣጫ ይነፍሳል፤ ድምፁንም ትሰማለህ፤ ሆኖም ከየት እንደሚመጣና ወዴት እንደሚሄድ አታውቅም። ከመንፈስ የተወለደም ሁሉ እንደዚሁ ነው።”+  ኒቆዲሞስም መልሶ “ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል?” አለው። 10  ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰለት፦ “አንተ የእስራኤል አስተማሪ ሆነህ ሳለህ እነዚህን ነገሮች አታውቅም? 11  እውነት እውነት እልሃለሁ፣ እኛ የምናውቀውን እንናገራለን፤ ያየነውንም እንመሠክራለን፤ እናንተ ግን እኛ የምንሰጠውን ምሥክርነት አትቀበሉም። 12  ስለ ምድራዊ ነገሮች ነግሬአችሁ የማታምኑ ከሆነ ስለ ሰማያዊ ነገሮች ብነግራችሁ እንዴት ታምናላችሁ? 13  ደግሞም ከሰማይ ከወረደው+ ከሰው ልጅ በቀር ወደ ሰማይ የወጣ የለም።+ 14  ሙሴ በምድረ በዳ እባቡን እንደሰቀለ፣+ የሰው ልጅም እንዲሁ ሊሰቀል ይገባዋል፤+ 15  ይኸውም በእሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው ነው።+ 16  “አምላክ ዓለምን እጅግ ከመውደዱ የተነሳ+ በልጁ የሚያምን* ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ ሲል አንድያ ልጁን ሰጥቷል።+ 17  ምክንያቱም አምላክ ልጁን ወደ ዓለም የላከው በዓለም ላይ እንዲፈርድ ሳይሆን ዓለም በእሱ አማካኝነት እንዲድን ነው።+ 18  በእሱ የሚያምን ሁሉ አይፈረድበትም።+ በእሱ የማያምን ሁሉ ግን በአምላክ አንድያ ልጅ ስም ስለማያምን ቀድሞውኑም ተፈርዶበታል።+ 19  እንግዲህ የሚፈረድባቸው በዚህ መሠረት ነው፦ ብርሃን ወደ ዓለም መጣ፤+ ሰዎች ግን ሥራቸው ክፉ ስለነበረ ከብርሃን ይልቅ ጨለማን ወደዱ። 20  መጥፎ ነገር የሚያደርግ* ሁሉ ብርሃንን ይጠላልና፤ እንዲሁም ሥራው እንዳይጋለጥበት ወደ ብርሃን አይመጣም። 21  ትክክል የሆነውን የሚያደርግ ሁሉ ግን ያደረገው ነገር ከአምላክ ፈቃድ ጋር በሚስማማ መንገድ የተከናወነ መሆኑ እንዲታይ ወደ ብርሃን ይመጣል።”+ 22  ከዚህ በኋላ ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ወደ ይሁዳ ገጠራማ ክልል ሄዱ፤ በዚያም ከእነሱ ጋር ለተወሰነ ጊዜ ቆየ፤ ያጠምቅም ነበር።+ 23  ይሁንና ዮሐንስም በሳሊም አቅራቢያ በሄኖን ብዙ ውኃ በመኖሩ+ በዚያ እያጠመቀ ነበር፤ ሰዎችም እየመጡ ይጠመቁ ነበር፤+ 24  በዚህ ጊዜ ዮሐንስ ገና እስር ቤት አልገባም ነበር።+ 25  የዮሐንስ ደቀ መዛሙርት የመንጻት ሥርዓትን በተመለከተ ከአንድ አይሁዳዊ ጋር ተከራከሩ። 26  ከዚያ በኋላ ወደ ዮሐንስ መጥተው “ረቢ፣ በዮርዳኖስ ማዶ ከአንተ ጋር የነበረውና ስለ እሱ የመሠከርክለት ሰው+ እያጠመቀ ነው፤ ሰዉም ሁሉ ወደ እሱ እየሄደ ነው” አሉት። 27  ዮሐንስም መልሶ እንዲህ አለ፦ “አንድ ሰው ከሰማይ ካልተሰጠው በቀር አንዳች ነገር ሊያገኝ አይችልም። 28  ‘እኔ ክርስቶስ አይደለሁም፤+ ከዚህ ይልቅ ከእሱ በፊት የተላክሁ ነኝ’+ እንዳልኩ እናንተ ራሳችሁ ትመሠክራላችሁ። 29  ሙሽራይቱ የሙሽራው ናት።+ ይሁን እንጂ የሙሽራው ጓደኛ በዚያ ቆሞ ሲሰማው በሙሽራው ድምፅ የተነሳ እጅግ ደስ ይለዋል። በመሆኑም የእኔ ደስታ ተፈጽሟል። 30  እሱ እየጨመረ መሄድ አለበት፤ እኔ ግን እየቀነስኩ መሄድ አለብኝ።” 31  ከላይ የሚመጣው+ ከሌሎች ሁሉ በላይ ነው። ከምድር የሆነው ምድራዊ ነው፤ የሚናገረውም ስለ ምድራዊ ነገሮች ነው። ከሰማይ የሚመጣው ከሌሎች ሁሉ በላይ ነው።+ 32  ስላየውና ስለሰማው ነገር ይመሠክራል፤+ ነገር ግን ምሥክርነቱን የሚቀበል ሰው የለም።+ 33  ምሥክርነቱን የተቀበለ ሰው ሁሉ አምላክ እውነተኛ መሆኑን አረጋግጧል።*+ 34  ምክንያቱም አምላክ የላከው የአምላክን ቃል ይናገራል፤+ አምላክ መንፈሱን ቆጥቦ* አይሰጥምና። 35  አብ ወልድን ይወዳል፤+ ደግሞም ሁሉንም ነገር በእጁ ሰጥቶታል።+ 36  በወልድ የሚያምን* የዘላለም ሕይወት አለው፤+ ወልድን የማይታዘዝ ግን የአምላክ ቁጣ በላዩ ይኖራል+ እንጂ ሕይወትን አያይም።+

የግርጌ ማስታወሻ

“ከላይ ካልተወለደ” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ወይም “በልጁ እንደሚያምን በተግባር የሚያሳይ።”
መጥፎ ነገር መሥራትን ልማድ የሚያደርግን ሰው ያመለክታል።
ቃል በቃል “በማኅተም አጽንቷል።”
ወይም “ለክቶ።”
ወይም “በወልድ እንደሚያምን በተግባር የሚያሳይ።”