ዮናስ 3:1-10
3 ከዚያም የይሖዋ ቃል ለሁለተኛ ጊዜ እንዲህ ሲል ወደ ዮናስ መጣ፦+
2 “ተነስተህ ወደ ታላቂቱ ከተማ ወደ ነነዌ+ ሂድ፤ የምነግርህንም መልእክት በመካከሏ አውጅ።”
3 ዮናስም የይሖዋን ቃል በመታዘዝ ተነስቶ ወደ ነነዌ+ ሄደ።+ ነነዌ እጅግ ታላቅ ከተማ የነበረች ስትሆን* በእግር የሦስት ቀን ያህል መንገድ ታስኬድ ነበር።
4 ዮናስም ወደ ከተማዋ ገብቶ የአንድ ቀን መንገድ ከተጓዘ በኋላ “ነነዌ በ40 ቀን ውስጥ ትደመሰሳለች” ብሎ አወጀ።
5 የነነዌም ሰዎች በአምላክ አመኑ፤+ ከትልቁም አንስቶ እስከ ትንሹ ድረስ ጾም አወጁ፤ ማቅም ለበሱ።
6 የነነዌ ንጉሥ መልእክቱን በሰማ ጊዜ ከዙፋኑ ተነስቶ ልብሰ መንግሥቱን አወለቀ፤ ማቅም ለብሶ አመድ ላይ ተቀመጠ።
7 በተጨማሪም በመላው ነነዌ አዋጅ አስነገረ፤“ንጉሡና መኳንንቱ ያወጡት ድንጋጌ፦ ሰውም ሆነ እንስሳ፣ ከብትም ሆነ መንጋ ምንም ነገር አይቅመስ። ምግብ አይብሉ፤ ውኃም አይጠጡ።
8 ሰውም ሆነ እንስሳ ማቅ ይልበስ፤ ሁሉም አጥብቆ ወደ አምላክ ይጩኽ፤ ክፉ መንገዳቸውንና የሚፈጽሙትን ግፍ ይተዉ።
9 እኛ እንዳንጠፋ፣ እውነተኛው አምላክ ሊያመጣው ያሰበውን ነገር እንደገና በማጤን* ከሚነደው ቁጣው ይመለስ እንደሆነ ማን ያውቃል?”
10 እውነተኛው አምላክ ያደረጉትን ነገር ይኸውም ከክፉ መንገዳቸው እንዴት እንደተመለሱ አየ፤+ በእነሱም ላይ አመጣዋለሁ ያለውን ነገር መልሶ በማጤን* ጥፋቱን ከማምጣት ተቆጠበ።+