ዮናስ 4:1-11

  • ዮናስ ተቆጣ፤ ሞትንም ተመኘ (1-3)

  • ይሖዋ ዮናስን ስለ ምሕረት አስተማረው (4-11)

    • “እንዲህ መቆጣትህ ተገቢ ነው?” (4)

    • አንዲት የቅል ተክል ማስተማሪያ ሆና አገለገለች (6-10)

4  ሆኖም ይህ ጉዳይ ዮናስን ፈጽሞ አላስደሰተውም፤ በመሆኑም እጅግ ተቆጣ።  ወደ ይሖዋም እንዲህ ሲል ጸለየ፦ “ይሖዋ ሆይ፣ በገዛ አገሬ ሳለሁ ያሳሰበኝ ጉዳይ ይህ አልነበረም? መጀመሪያውኑም ወደ ተርሴስ ለመሸሽ የሞከርኩት ለዚህ ነበር፤+ አንተ ሩኅሩኅና* መሐሪ አምላክ፣ ለቁጣ የዘገየህና ታማኝ ፍቅርህ የበዛ፣+ አዝነህም ጥፋት ከማምጣት የምትቆጠብ እንደሆንክ አውቃለሁና።  አሁንም ይሖዋ ሆይ፣ በሕይወት ከመኖር ይልቅ መሞት ስለሚሻለኝ እባክህ ግደለኝ።”*+  ይሖዋም “እንዲህ መቆጣትህ ተገቢ ነው?” ብሎ ጠየቀው።  ከዚያም ዮናስ ከከተማዋ ወጥቶ በስተ ምሥራቅ በኩል ተቀመጠ። በዚያም ለራሱ መጠለያ ሠርቶ በከተማዋ ላይ የሚደርሰውን ነገር ለማየት በጥላው ሥር ተቀመጠ።+  በዚህ ጊዜ ይሖዋ አምላክ፣ ዮናስ ራሱን እንዲያስጠልልባትና ከሥቃዩ እንዲያርፍ ሲል አንዲት የቅል ተክል* ከበላዩ እንድታድግ አደረገ። ዮናስም በቅል ተክሏ እጅግ ተደሰተ።  ይሁን እንጂ እውነተኛው አምላክ በሚቀጥለው ቀን፣ ማለዳ ላይ አንድ ትል ላከ፤ ትሉም የቅል ተክሏን በላት፤ ተክሏም ደረቀች።  ፀሐይ መውጣት ስትጀምር አምላክ የሚያቃጥል የምሥራቅ ነፋስ አመጣ፤ ፀሐይዋም የዮናስን አናት አቃጠለችው፤ እሱም ተዝለፈለፈ። እንዲሞትም* ለመነ፤ ደግሞ ደጋግሞም “በሕይወት ከምኖር ብሞት ይሻለኛል” አለ።+  አምላክም ዮናስን “ስለ ቅል ተክሏ እንዲህ መቆጣትህ ተገቢ ነው?” ሲል ጠየቀው።+ እሱም “መቆጣት ሲያንሰኝ ነው፤ እንዲያውም ብሞት ይሻለኛል” አለ። 10  ይሖዋ ግን እንዲህ አለው፦ “አንተ በአንድ ሌሊት አድጋ በአንድ ሌሊት ለጠፋችው፣ ላልደከምክባት ወይም ላላሳደግካት የቅል ተክል አዝነሃል። 11  ታዲያ እኔ ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር* ለይተው የማያውቁ ከ120,000 በላይ የሚሆኑ ሰዎችና በርካታ እንስሶቻቸው ለሚኖሩባት ለታላቂቱ ከተማ ለነነዌ+ ላዝን አይገባም?”+

የግርጌ ማስታወሻ

ወይም “ቸርና።”
ወይም “ነፍሴን ውሰድ።”
“የጉሎ ዛፍ” ሊሆን ይችላል።
ወይም “ነፍሱ እንድትሞትም።”
ወይም “ቀኝና ግራ እጃቸውን።”