ዳንኤል 1:1-21
1 የይሁዳ ንጉሥ ኢዮዓቄም+ በነገሠ በሦስተኛው ዓመት የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነጾር ወደ ኢየሩሳሌም መጥቶ ከበባት።+
2 ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ይሖዋ የይሁዳን ንጉሥ ኢዮዓቄምንና በእውነተኛው አምላክ ቤት* ውስጥ ካሉት ዕቃዎች መካከል የተወሰኑትን በእጁ አሳልፎ ሰጠው፤+ እሱም በሰናኦር+ ምድር* ወደሚገኘው ወደ አምላኩ ቤት* አመጣቸው። ዕቃዎቹን በአምላኩ ግምጃ ቤት ውስጥ አስቀመጣቸው።+
3 ከዚያም ንጉሡ የቤተ መንግሥቱ ዋና ባለሥልጣን የሆነውን አሽፈኔዝን ከንጉሡና ከመሳፍንቱ ዘር የሆኑትን ጨምሮ አንዳንድ እስራኤላውያንን* እንዲያመጣ አዘዘው።+
4 እነሱም ምንም እንከን የሌለባቸው፣ መልከ መልካሞች፣ ጥበብ፣ እውቀትና ማስተዋል ያላቸው+ እንዲሁም በንጉሡ ቤተ መንግሥት ውስጥ ማገልገል የሚችሉ ወጣቶች* መሆን ነበረባቸው። የከለዳውያንን ጽሑፍና ቋንቋም እንዲያስተምራቸው አዘዘው።
5 በተጨማሪም ንጉሡ ለእሱ ከሚቀርበው ምርጥ ምግብና ከሚጠጣው የወይን ጠጅ ላይ የዕለት ቀለብ እንዲሰጣቸው አደረገ። እነዚህ ወጣቶች ለሦስት ዓመት ከሠለጠኑ በኋላ* ንጉሡን ለማገልገል የሚሰማሩ ናቸው።
6 ከእነሱ መካከል ከይሁዳ ነገድ የሆኑት ዳንኤል፣*+ ሃናንያህ፣* ሚሳኤልና* አዛርያስ* ይገኙበታል።+
7 ዋናው ባለሥልጣንም ስም* አወጣላቸው፤ ዳንኤልን ብልጣሶር፣+ ሃናንያህን ሲድራቅ፣ ሚሳኤልን ሚሳቅ፣ አዛርያስን ደግሞ አብደናጎ ብሎ ጠራቸው።+
8 ዳንኤል ግን በንጉሡ ምርጥ ምግብ ወይም በሚጠጣው የወይን ጠጅ ላለመርከስ በልቡ ቁርጥ ውሳኔ አደረገ። በመሆኑም በዚህ መንገድ ራሱን እንዳያረክስ ዋናውን ባለሥልጣን ፈቃድ ጠየቀው።
9 እውነተኛው አምላክም ዋናው ባለሥልጣን ለዳንኤል ሞገስና* ምሕረት እንዲያሳየው አደረገ።+
10 ሆኖም ዋናው ባለሥልጣን ዳንኤልን እንዲህ አለው፦ “የምትበሉትንና የምትጠጡትን የመደበላችሁን ጌታዬን ንጉሡን እፈራለሁ። እኩዮቻችሁ ከሆኑት ከሌሎቹ ወጣቶች* ይልቅ ፊታችሁ ተጎሳቁሎ ቢያይስ? እኔን* በንጉሡ ፊት በደለኛ ታደርጉኛላችሁ።”
11 ዳንኤል ግን ዋናው ባለሥልጣን በዳንኤል፣ በሃናንያህ፣ በሚሳኤልና በአዛርያስ ላይ ጠባቂ አድርጎ የሾመውን ሰው እንዲህ አለው፦
12 “እባክህ አገልጋዮችህን ለአሥር ቀን ያህል ፈትነን፤ የምንበላው አትክልትና የምንጠጣው ውኃ ይሰጠን፤
13 ከዚያም የእኛን ቁመና የንጉሡን ምርጥ ምግብ ከሚበሉት ወጣቶች* ቁመና ጋር አወዳድር፤ በኋላም ባየኸው መሠረት በአገልጋዮችህ ላይ የፈለግከውን ነገር አድርግ።”
14 እሱም በሐሳባቸው ተስማማ፤ ለአሥር ቀንም ፈተናቸው።
15 ከአሥር ቀን በኋላም የንጉሡን ምርጥ ምግብ ከሚበሉት ወጣቶች* ሁሉ ይበልጥ ቁመናቸው የተሻለና ጤናማ ሆነው* ተገኙ።
16 ስለዚህ ጠባቂው ምርጥ በሆነው ምግባቸውና በወይን ጠጃቸው ምትክ አትክልት ይሰጣቸው ነበር።
17 እውነተኛው አምላክም ለእነዚህ አራት ወጣቶች* በሁሉም ዓይነት የጽሑፍና የጥበብ መስክ እውቀትና ጥልቅ ማስተዋል ሰጣቸው፤ ዳንኤልም ሁሉንም ዓይነት ራእዮችና ሕልሞች የመረዳት ችሎታ ተሰጠው።+
18 ንጉሡ በፊቱ እንዲያቀርቧቸው የቀጠረው ጊዜ ሲደርስ+ ዋናው ባለሥልጣን ናቡከደነጾር ፊት አቀረባቸው።
19 ንጉሡ ሲያነጋግራቸው ከወጣቶቹ መካከል እንደ ዳንኤል፣ ሃናንያህ፣ ሚሳኤልና አዛርያስ ያለ አልተገኘም፤+ እነሱም በንጉሡ ፊት ማገልገላቸውን ቀጠሉ።
20 ንጉሡ ጥበብና ማስተዋል የሚጠይቁ ጉዳዮችን ሁሉ አንስቶ በጠየቃቸው ጊዜ በመላ ግዛቱ ካሉት አስማተኛ ካህናትና ጠንቋዮች ሁሉ+ አሥር እጅ በልጠው አገኛቸው።
21 ዳንኤልም እስከ ንጉሥ ቂሮስ+ የመጀመሪያ ዓመት ድረስ በዚያ ቆየ።
የግርጌ ማስታወሻ
^ ወይም “ቤተ መቅደስ።”
^ የባቢሎንን ምድር ያመለክታል።
^ ወይም “ቤተ መቅደስ።”
^ ቃል በቃል “አንዳንድ የእስራኤል ወንዶች ልጆችን።”
^ ቃል በቃል “ልጆች።”
^ “እንክብካቤ ከተደረገላቸው በኋላ” ማለትም ሊሆን ይችላል።
^ “እንደ አምላክ ያለ ማን ነው?” ማለት ሊሆን ይችላል።
^ “ይሖዋ ረድቶናል” የሚል ትርጉም አለው።
^ “ይሖዋ ሞገስ አሳየ” የሚል ትርጉም አለው።
^ “አምላክ ፈራጄ ነው” የሚል ትርጉም አለው።
^ የባቢሎናውያን ስም።
^ ወይም “ደግነትና።”
^ ቃል በቃል “ራሴን።”
^ ቃል በቃል “ልጆች።”
^ ቃል በቃል “ልጆች።”
^ ቃል በቃል “ልጆች።”
^ ቃል በቃል “ቁመናቸው ተሽሎና ሥጋቸው ወፍሮ።”
^ ቃል በቃል “ልጆች።”