ዳንኤል 12:1-13

  • ‘የፍጻሜው ዘመንና’ ከዚያ በኋላ ያለው ጊዜ (1-13)

    • ሚካኤል ይነሳል (1)

    • ጥልቅ ማስተዋል ያላቸው ሰዎች ያበራሉ (3)

    • እውነተኛው እውቀት ይበዛል (4)

    • ዳንኤል ዕጣ ፋንታውን ለመቀበል ይነሳል (13)

12  “በዚያ ዘመን ለሕዝብህ* የሚቆመው ታላቁ አለቃ+ ሚካኤል*+ ይነሳል።* ብሔራት ከተቋቋሙበት ጊዜ አንስቶ እስከዚያ ጊዜ ድረስ ሆኖ የማያውቅ የጭንቀት ጊዜ ይመጣል። በዚያን ወቅት ሕዝብህ ይኸውም በመጽሐፍ ላይ ተጽፎ የተገኘ+ እያንዳንዱ ሰው ይተርፋል።+  በምድር አፈር ውስጥ ካንቀላፉትም መካከል ብዙዎቹ ይነሳሉ፤ አንዳንዶቹ ለዘላለም ሕይወት፣ ሌሎቹ ደግሞ ለነቀፋና ለዘላለማዊ ውርደት ይነሳሉ።  “ደግሞም ጥልቅ ማስተዋል ያላቸው ሰዎች እንደ ሰማይ ጸዳል ያበራሉ፤ የጽድቅን ጎዳና እንዲከተሉ ብዙ ሰዎችን የሚረዱም ለዘላለም እንደ ከዋክብት ያበራሉ።  “አንተም ዳንኤል ሆይ፣ እስከ ፍጻሜው ዘመን ድረስ ቃሉን በሚስጥር ያዝ፤ መጽሐፉንም አትመው።+ ብዙዎች መጽሐፉን በሚገባ ይመረምራሉ፤* እውነተኛው እውቀትም ይበዛል።”+  ከዚያም እኔ ዳንኤል ስመለከት ሌሎች ሁለት በዚያ ቆመው አየሁ፤ አንደኛው ከወንዙ በዚህኛው ዳር ቆሞ የነበረ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ ከወንዙ በዚያኛው ዳር ቆሞ ነበር።+  ከዚያም አንዱ፣ ከወንዙ ውኃ በላይ ያለውንና በፍታ የለበሰውን+ ሰው “እነዚህ አስደናቂ ነገሮች ፍጻሜያቸውን የሚያገኙት ከምን ያህል ጊዜ በኋላ ነው?” አለው።  ከዚያም ከወንዙ ውኃ በላይ ያለውና በፍታ የለበሰው ሰው መልስ ሲሰጥ ሰማሁ። እሱም ቀኝ እጁንና ግራ እጁን ወደ ሰማያት ዘርግቶ ለዘላለም ሕያው በሆነው+ በመማል እንዲህ ሲል መልስ ሰጠ፦ “ከተወሰነ ዘመን፣ ዘመናትና የዘመን እኩሌታ* በኋላ ነው። የቅዱሱ ሕዝብ ኃይል ተደምስሶ እንዳበቃ+ እነዚህ ሁሉ ነገሮች ፍጻሜያቸውን ያገኛሉ።”  እኔም ሰማሁ፤ ሆኖም ሊገባኝ አልቻለም፤+ ስለዚህ “ጌታዬ ሆይ፣ የእነዚህ ነገሮች መጨረሻ ምን ይሆን?” አልኩት።  እሱም እንዲህ አለኝ፦ “ዳንኤል ሆይ፣ ሂድ፤ ምክንያቱም የፍጻሜው ዘመን እስኪመጣ ድረስ ቃሉ በሚስጥር የተያዘና የታተመ ይሆናል።+ 10  ብዙዎች ራሳቸውን ያጸዳሉ፣ ያነጻሉ እንዲሁም ይጠራሉ።+ ክፉዎች ደግሞ ክፉ ድርጊት ይፈጽማሉ፤ ከክፉዎች መካከል አንዳቸውም አይረዱትም፤ ጥልቅ ማስተዋል ያላቸው ግን ይረዱታል።+ 11  “የዘወትሩ መሥዋዕት+ ከተቋረጠበትና ጥፋት የሚያመጣው ርኩስ ነገር ከቆመበት+ ጊዜ አንስቶ 1,290 ቀን ይሆናል። 12  “ደግሞም 1,335ቱ ቀን እስከሚያልፍ ድረስ በትዕግሥት የሚጠባበቅ* ሰው ደስተኛ ነው! 13  “አንተ ግን እስከ ፍጻሜው ድረስ ሂድ። ታርፋለህ፤ ሆኖም በዘመኑ ፍጻሜ ዕጣ ፋንታህን ለመቀበል* ትነሳለህ።”+

የግርጌ ማስታወሻ

ቃል በቃል “ለሕዝብህ ወንዶች ልጆች።”
“እንደ አምላክ ያለ ማን ነው?” የሚል ትርጉም አለው።
ቃል በቃል “ይቆማል።”
ቃል በቃል “ወዲያ ወዲህ ይላሉ።”
ሦስት ዘመን ተኩልን ያመለክታል።
ወይም “በጉጉት የሚጠባበቅ።”
ወይም “በተመደበልህ ቦታ።”