ዳንኤል 4:1-37
4 “ከንጉሥ ናቡከደነጾር፣ በመላው ምድር ለሚኖሩ ከተለያዩ ብሔራትና ቋንቋዎች ለተውጣጡ ሕዝቦች፦ ሰላም ይብዛላችሁ!
2 ልዑሉ አምላክ ለእኔ ያደረጋቸውን ተአምራዊ ምልክቶችና ድንቅ ሥራዎች ስነግራችሁ ደስ ይለኛል።
3 ተአምራዊ ምልክቱ እንዴት ታላቅ ነው! ድንቅ ሥራውም በዓይነቱ ልዩ ነው! መንግሥቱ የዘላለም መንግሥት ነው፤ የመግዛት ሥልጣኑም ከትውልድ እስከ ትውልድ ይዘልቃል።+
4 “እኔ ናቡከደነጾር በቤቴ ዘና ብዬ፣ በቤተ መንግሥቴም ደልቶኝ እኖር ነበር።
5 አንድ አስፈሪ ሕልም አየሁ። በአልጋዬ ላይ ተኝቼ ሳለሁ ወደ አእምሮዬ ይመጡ የነበሩት ምስሎችና ራእዮች አስፈሩኝ።+
6 ስለዚህ ያየሁትን ሕልም ትርጉም እንዲያሳውቁኝ የባቢሎንን ጠቢባን ሁሉ በፊቴ እንዲያቀርቧቸው አዘዝኩ።+
7 “በዚህ ጊዜ አስማተኞቹ ካህናት፣ ጠንቋዮቹ፣ ከለዳውያኑና* ኮከብ ቆጣሪዎቹ+ ገቡ። ያየሁትን ሕልም ስነግራቸው ትርጉሙን ሊያሳውቁኝ አልቻሉም።+
8 በመጨረሻም በአምላኬ ስም+ ብልጣሶር ተብሎ የተጠራውና+ የቅዱሳን አማልክት መንፈስ ያለበት ዳንኤል በፊቴ ቀረበ፤+ እኔም ያየሁትን ሕልም ነገርኩት፦
9 “‘የአስማተኛ ካህናት አለቃ የሆንከው ብልጣሶር ሆይ፣+ የቅዱሳን አማልክት መንፈስ በአንተ ውስጥ እንዳለና+ ለመግለጥ የሚያስቸግርህ ምንም ዓይነት ሚስጥር እንደሌለ በሚገባ አውቃለሁ።+ በመሆኑም በሕልሜ ያየኋቸውን ራእዮችና ትርጉማቸውን ግለጽልኝ።
10 “‘በአልጋዬ ላይ ተኝቼ ሳለሁ ባየኋቸው ራእዮች ላይ፣ በምድር መካከል ቁመቱ እጅግ ረጅም የሆነ አንድ ዛፍ+ ቆሞ ተመለከትኩ።+
11 ዛፉም አድጎ ጠንካራ ሆነ፤ ጫፉም እስከ ሰማያት ደረሰ፤ እስከ ምድር ዳርቻ ድረስም ይታይ ነበር።
12 ቅጠሉ ያማረ፣ ፍሬውም በጣም ብዙ ሲሆን ዛፉ ላይ ለሁሉ የሚሆን መብል ነበር። የዱር እንስሳት በጥላው ሥር ያርፉ፣ የሰማይ ወፎችም በቅርንጫፎቹ ላይ ይቀመጡ ነበር፤ ፍጥረታትም ሁሉ ከእሱ ይመገቡ ነበር።*
13 “‘በአልጋዬ ላይ ተኝቼ ራእዮቹን ስመለከት ቅዱስ የሆነ አንድ ጠባቂ ከሰማያት ሲወርድ አየሁ።+
14 እሱም ከፍ ባለ ድምፅ እንዲህ አለ፦ “ዛፉን ቁረጡ፤+ ቅርንጫፎቹን ጨፍጭፉ፤ ቅጠሎቹን አራግፉ፤ ፍሬውንም በትኑ! የዱር እንስሳቱ ከሥሩ፣ ወፎቹም ከቅርንጫፎቹ ላይ ይሽሹ።
15 ጉቶው ግን በብረትና በመዳብ ታስሮ በሜዳ ሣር መካከል ከነሥሩ መሬት ውስጥ ይቆይ። በሰማያትም ጠል ይረስርስ፤ ዕጣ ፋንታውም በምድር ተክሎች መካከል ከአራዊት ጋር ይሁን።+
16 ልቡ ከሰው ልብ ይለወጥ፤ የአውሬም ልብ ይሰጠው፤ ሰባት ዘመናትም+ ይለፉበት።+
17 ይህ ነገር በጠባቂዎች ታውጇል፤+ የፍርድ ውሳኔውም በቅዱሳኑ ተነግሯል፤ ይህም ልዑሉ አምላክ በሰው ልጆች መንግሥት ላይ እንደሚገዛ+ እንዲሁም መንግሥቱን ለወደደው እንደሚሰጥና ከሰዎች ሁሉ የተናቀውን እንደሚሾምበት በሕይወት ያሉ ሁሉ ያውቁ ዘንድ ነው።”
18 “‘እኔ ንጉሥ ናቡከደነጾር ያየሁት ሕልም ይህ ነው፤ አሁንም ብልጣሶር ሆይ፣ በመንግሥቴ ውስጥ የሚኖሩት ሌሎቹ ጠቢባን ሁሉ ትርጉሙን ሊያሳውቁኝ ስላልቻሉ አንተ ትርጉሙን ንገረኝ።+ የቅዱሳን አማልክት መንፈስ በውስጥህ ስላለ ትርጉሙን ልታሳውቀኝ ትችላለህ።’
19 “በዚህ ጊዜ ብልጣሶር የተባለው ዳንኤል+ ለጥቂት ጊዜ በድንጋጤ ተዋጠ፤ ወደ አእምሮው የመጣው ሐሳብም በጣም አስፈራው።
“ንጉሡም ‘ብልጣሶር ሆይ፣ ሕልሙና ትርጉሙ አያስፈራህ’ አለው።
“ብልጣሶርም መልሶ እንዲህ አለው፦ ‘ጌታዬ ሆይ፣ ሕልሙ ለሚጠሉህ፣ ትርጉሙም ለጠላቶችህ ይሁን።
20 “‘አንተ ያየኸው ዛፍ ይኸውም በጣም ያደገውና የጠነከረው፣ ጫፉ እስከ ሰማያት የደረሰውና ከየትኛውም የምድር ክፍል የሚታየው፣+
21 ቅጠሉ ያማረውና ፍሬው የበዛው፣ ለሁሉም የሚሆን መብል ያለበት፣ የዱር እንስሳት መጠለያ የሆነውና በቅርንጫፎቹ ላይ የሰማይ ወፎች የሚኖሩበት ዛፍ፣+
22 ንጉሥ ሆይ፣ አንተ ነህ፤ ምክንያቱም አንተ ታላቅና ብርቱ ሆነሃል፤ ታላቅነትህ ገንኖ እስከ ሰማያት ደርሷል፤+ ግዛትህም እስከ ምድር ዳርቻ ተንሰራፍቷል።+
23 “‘ንጉሡም አንድ ቅዱስ ጠባቂ+ “ዛፉን ቆርጣችሁ አጥፉት፤ ጉቶው ግን በብረትና በመዳብ ታስሮ በሜዳ ሣር መካከል ከነሥሩ መሬት ውስጥ ይቆይ። በሰማያትም ጠል ይረስርስ፤ ሰባት ዘመናትም እስኪያልፉበት ድረስ ዕጣ ፋንታው ከዱር አራዊት ጋር ይሁን” እያለ ከሰማያት ሲወርድ አይቷል።+
24 ንጉሥ ሆይ፣ ትርጉሙ ይህ ነው፤ ልዑሉ አምላክ በጌታዬ በንጉሡ ላይ ይደርሳል ብሎ ያወጀው ነገር ይህ ነው።
25 ከሰዎች መካከል ትሰደዳለህ፤ ከዱር አራዊትም ጋር ትኖራለህ፤ እንደ በሬም ሣር ትበላለህ፤ በሰማያትም ጠል ትረሰርሳለህ፤+ ልዑሉ አምላክ በሰው ልጆች መንግሥት ላይ እንደሚገዛና መንግሥቱንም ለወደደው እንደሚሰጥ እስክታውቅ ድረስ+ ሰባት ዘመናት+ ያልፉብሃል።+
26 “‘ይሁንና የዛፉን ጉቶ ከነሥሩ እንዲተዉት+ ስለተነገራቸው፣ አምላክ በሰማያት እንደሚገዛ ካወቅክ በኋላ መንግሥትህ ይመለስልሃል።
27 ስለዚህ ንጉሥ ሆይ፣ ምክሬ በአንተ ዘንድ ተቀባይነት ያግኝ። ኃጢአት መሥራትህን ትተህ ትክክል የሆነውን አድርግ፤ ግፍ መፈጸምህን ትተህ ለድሆች ምሕረት አሳይ። ምናልባት የተደላደለ ሕይወት የምትኖርበት ዘመን ይራዘምልህ ይሆናል።’”+
28 ይህ ሁሉ በንጉሥ ናቡከደነጾር ላይ ደረሰ።
29 ከ12 ወራት በኋላ በባቢሎን ቤተ መንግሥት ሰገነት ላይ እየተመላለሰ ነበር።
30 ንጉሡም “ይህች፣ ንጉሣዊ መኖሪያ እንድትሆን ለግርማዬ ክብር፣ በገዛ ብርታቴና ኃይሌ የገነባኋት ታላቂቱ ባቢሎን አይደለችም?” አለ።
31 ንጉሡ ንግግሩን ገና ከአፉ ሳይጨርስ እንዲህ የሚል ድምፅ ከሰማያት መጣ፦ “ንጉሥ ናቡከደነጾር ሆይ፣ የተላከልህ መልእክት ይህ ነው፦ ‘መንግሥትህ ከአንተ ተወስዷል፤+
32 ከሰዎች መካከል ትሰደዳለህ። ከዱር አራዊት ጋር ትኖራለህ፤ እንደ በሬም ሣር ትበላለህ፤ ልዑሉ አምላክ በሰው ልጆች መንግሥት ላይ እንደሚገዛና መንግሥቱንም ለወደደው እንደሚሰጥ እስክታውቅ ድረስ ሰባት ዘመናት ያልፉብሃል።’”+
33 ወዲያውኑ ይህ ቃል በናቡከደነጾር ላይ ተፈጸመ። ከሰው ልጆች መካከል ተሰደደ፤ እንደ በሬም ሣር መብላት ጀመረ፤ ፀጉሩ እንደ ንስር ላባ እስኪረዝም፣ ጥፍሮቹም እንደ ወፍ ጥፍሮች እስኪያድጉ ድረስ ሰውነቱ በሰማያት ጠል ረሰረሰ።+
34 “ዘመኑ በተፈጸመ ጊዜ+ እኔ ናቡከደነጾር ወደ ሰማያት ተመለከትኩ፤ አእምሮዬም ተመለሰልኝ፤ ልዑሉንም አምላክ አመሰገንኩ፤ ለዘላለም የሚኖረውንም አወደስኩ፤ አከበርኩትም፤ ምክንያቱም የመግዛት ሥልጣኑ ዘላለማዊ ነው፤ መንግሥቱም ከትውልድ እስከ ትውልድ ይኖራል።+
35 የምድር ነዋሪዎች ሁሉ እንደ ኢምንት ይቆጠራሉ፤ በሰማያት ሠራዊትና በምድር ነዋሪዎች ላይ እንደ ፈቃዱ ያደርጋል። ሊያግደው* ወይም ‘ምን ማድረግህ ነው?’ ብሎ ሊጠይቀው የሚችል ማንም የለም።+
36 “በዚህ ጊዜ አእምሮዬ ተመለሰልኝ፤ ደግሞም የመንግሥቴ ክብር፣ ግርማዊነቴና ሞገሴ ተመለሰልኝ።+ ከፍተኛ ባለሥልጣናቴና መኳንንቴ አጥብቀው ፈለጉኝ፤ እኔም ወደ መንግሥቴ ተመለስኩ፤ ከቀድሞውም የበለጠ ታላቅ ሆንኩ።
37 “አሁንም እኔ ናቡከደነጾር የሰማያትን ንጉሥ አወድሰዋለሁ፣ ከፍ ከፍ አደርገዋለሁ እንዲሁም አከብረዋለሁ፤+ ምክንያቱም ሥራው ሁሉ እውነት፣ መንገዶቹም ትክክል ናቸው፤+ በኩራት የሚመላለሱትንም ማዋረድ ይችላል።”+