ዳንኤል 5:1-31

  • ንጉሥ ቤልሻዛር ያዘጋጀው ግብዣ (1-4)

  • በግድግዳ ላይ የተጻፈው የእጅ ጽሑፍ (5-12)

  • ዳንኤል የጽሑፉን ፍቺ እንዲያሳውቅ ተጠየቀ (13-25)

  • የጽሑፉ ፍቺ፦ የባቢሎን ውድቀት (26-31)

5  ንጉሥ ቤልሻዛር+ ለሺህ መኳንንቱ ታላቅ ግብዣ አደረገ፤ በእነሱም ፊት የወይን ጠጅ እየጠጣ ነበር።+  ቤልሻዛር የወይን ጠጅ ጠጥቶ ሞቅ ሲለው አባቱ ናቡከደነጾር በኢየሩሳሌም ከነበረው ቤተ መቅደስ የወሰዳቸውን የወርቅና የብር ዕቃዎች፣+ ንጉሡና መኳንንቱ እንዲሁም ቁባቶቹና ቅምጦቹ ይጠጡባቸው ዘንድ እንዲያመጧቸው አዘዘ።  በዚህ ጊዜ በኢየሩሳሌም፣ በአምላክ ቤት ከነበረው ቤተ መቅደስ የወሰዷቸውን የወርቅ ዕቃዎች አመጡ፤ ንጉሡና መኳንንቱ እንዲሁም ቁባቶቹና ቅምጦቹ ጠጡባቸው።  እነሱም የወይን ጠጅ እየጠጡ ከወርቅ፣ ከብር፣ ከመዳብ፣ ከብረት፣ ከእንጨትና ከድንጋይ የተሠሩ አማልክትን አወደሱ።  ወዲያውኑም የሰው እጅ ጣቶች ብቅ ብለው በንጉሡ ቤተ መንግሥት፣ በመቅረዙ ትይዩ ባለው ግድግዳ ልስን ላይ መጻፍ ጀመሩ፤ ንጉሡም የሚጽፈውን እጅ አየ።  በዚህ ጊዜ ንጉሡ ፊቱ ገረጣ፤* ወደ አእምሮው የመጣው ሐሳብ አሸበረው፤ ወገቡም ተንቀጠቀጠ፤+ ጉልበቶቹም ይብረከረኩ ጀመር።  ንጉሡ ድምፁን ከፍ አድርጎ ጠንቋዮቹን፣ ከለዳውያኑንና* ኮከብ ቆጣሪዎቹን እንዲያመጧቸው አዘዘ።+ ንጉሡም የባቢሎንን ጠቢባን እንዲህ አላቸው፦ “ይህን ጽሑፍ የሚያነብና ትርጉሙን የሚነግረኝ ማንኛውም ሰው ሐምራዊ ልብስ ይለብሳል፤ አንገቱ ላይ የወርቅ ሐብል ይደረግለታል፤+ በመንግሥትም ላይ ሦስተኛ ገዢ ይሆናል።”+  በዚህ ጊዜ የንጉሡ ጠቢባን ሁሉ ገቡ፤ ሆኖም ጽሑፉን ማንበብም ሆነ ትርጉሙን ለንጉሡ ማሳወቅ አልቻሉም።+  በመሆኑም ንጉሥ ቤልሻዛር እጅግ ፈራ፤ ፊቱም ገረጣ፤ መኳንንቱም ግራ ተጋቡ።+ 10  ንግሥቲቱም ንጉሡና መኳንንቱ የተናገሩትን በሰማች ጊዜ ወደ ግብዣው አዳራሽ ገባች። እንዲህም አለች፦ “ንጉሥ ሆይ፣ ለዘላለም ኑር። በፍርሃት አትዋጥ፤ ፊትህም አይለዋወጥ። 11  በመንግሥትህ ውስጥ የቅዱሳን አማልክት መንፈስ ያለበት ሰው* አለ። በአባትህ ዘመን እንደ አማልክት ጥበብ ያለ ጥበብ፣ የእውቀት ብርሃንና ጥልቅ ማስተዋል ተገኝቶበት ነበር።+ አባትህ ንጉሥ ናቡከደነጾር የአስማተኛ ካህናቱ፣ የጠንቋዮቹ፣ የከለዳውያኑና* የኮከብ ቆጣሪዎቹ አለቃ አድርጎ ሾመው፤+ ንጉሥ ሆይ፣ ይህን ያደረገው አባትህ ነው። 12  ንጉሡ፣ ብልጣሶር ብሎ የሰየመው ዳንኤል+ ሕልምን በመተርጎም ረገድ በዓይነቱ ልዩ የሆነ ችሎታ፣ እውቀትና ጥልቅ ማስተዋል እንዲሁም እንቆቅልሽንና የተወሳሰቡ ችግሮችን የመፍታት* ችሎታ ነበረው።+ እንግዲህ ዳንኤል ይጠራ፤ እሱም ትርጉሙን ይነግርሃል።” 13  በመሆኑም ዳንኤልን በንጉሡ ፊት አቀረቡት። ንጉሡም ዳንኤልን እንዲህ ሲል ጠየቀው፦ “ንጉሡ አባቴ ከይሁዳ ምድር ካመጣቸው+ የይሁዳ ግዞተኞች አንዱ የሆንከው ዳንኤል አንተ ነህ?+ 14  የአማልክት መንፈስ በውስጥህ እንዳለ+ እንዲሁም የእውቀት ብርሃን፣ ጥልቅ ማስተዋልና በዓይነቱ ልዩ የሆነ ጥበብ እንደተገኘብህ ስለ አንተ ሰምቻለሁ።+ 15  ይህን ጽሑፍ አንብበው ትርጉሙን እንዲያሳውቁኝ ጥበበኞችንና ጠንቋዮችን በፊቴ አቅርበዋቸው ነበር፤ እነሱ ግን የመልእክቱን ትርጉም መናገር አልቻሉም።+ 16  አንተ ግን የመተርጎምና የተወሳሰቡ ችግሮችን የመፍታት* ችሎታ እንዳለህ ሰምቻለሁ።+ አሁንም ይህን ጽሑፍ አንብበህ ትርጉሙን ልታሳውቀኝ ከቻልክ ሐምራዊ ልብስ ትለብሳለህ፤ አንገትህ ላይ የወርቅ ሐብል ይደረግልሃል፤ በመንግሥትም ላይ ሦስተኛ ገዢ ትሆናለህ።”+ 17  በዚህ ጊዜ ዳንኤል ለንጉሡ እንዲህ ሲል መለሰ፦ “ስጦታህ ለራስህ ይሁን፤ ገጸ በረከቶችህንም ለሌሎች ስጥ። ይሁንና ጽሑፉን ለንጉሡ አነባለሁ፤ ትርጉሙንም አሳውቀዋለሁ። 18  ንጉሥ ሆይ፣ ልዑሉ አምላክ ለአባትህ ለናቡከደነጾር መንግሥት፣ ታላቅነት፣ ክብርና ግርማ ሰጠው።+ 19  ታላቅነትን ስላጎናጸፈው ከተለያዩ ብሔራትና ቋንቋዎች የተውጣጡ ሕዝቦች ሁሉ በፊቱ በፍርሃት ይንቀጠቀጡ ነበር።+ የፈለገውን ይገድል ወይም በሕይወት እንዲኖር ይፈቅድ፣ የፈለገውን ከፍ ከፍ ያደርግ ወይም ያዋርድ ነበር።+ 20  ሆኖም ልቡ ታብዮና አንገተ ደንዳና ሆኖ የእብሪተኝነት መንፈስ ባሳየ ጊዜ+ ከመንግሥቱ ዙፋን እንዲወርድ ተደረገ፤ ክብሩንም ተገፈፈ። 21  ከሰው ልጆች መካከል ተሰደደ፤ ልቡም ወደ አውሬ ልብ ተለወጠ፤ መኖሪያውም ከዱር አህዮች ጋር ሆነ። ልዑሉ አምላክ በሰው ልጆች መንግሥት ላይ እንደሚገዛና የፈለገውን በመንግሥቱ ላይ እንደሚያስቀምጥ እስኪያውቅ ድረስ እንደ በሬ ሣር በላ፤ ሰውነቱም በሰማያት ጠል ረሰረሰ።+ 22  “ቤልሻዛር ሆይ፣ አንተ ግን ልጁ እንደመሆንህ መጠን ይህን ሁሉ ብታውቅም ትሕትና አላሳየህም። 23  ይልቁንም በሰማያት ጌታ ላይ ታበይክ፤+ የቤተ መቅደሱንም ዕቃ አስመጣህ።+ ከዚያም አንተና መኳንንትህ እንዲሁም ቁባቶችህና ቅምጦችህ በእነዚህ ዕቃዎች የወይን ጠጅ ጠጣችሁ፤ አንዳች ነገር ማየትም ሆነ መስማት ወይም ማወቅ የማይችሉትን ከብር፣ ከወርቅ፣ ከመዳብ፣ ከብረት፣ ከእንጨትና ከድንጋይ የተሠሩ አማልክት አወደሳችሁ።+ እስትንፋስህንና መንገድህን ሁሉ በእጁ የያዘውን አምላክ ግን አላከበርክም።+ 24  ስለዚህ ይህን እጅ የላከው እሱ ነው፤ ይህም ጽሑፍ ተጻፈ።+ 25  የተጻፈውም ጽሑፍ፣ ‘ሚኒ፣ ሚኒ፣ ቲቄል እና ፋርሲን’ ይላል። 26  “የቃላቱ ትርጉም ይህ ነው፦ ሚኒ ማለት አምላክ የመንግሥትህን ዘመን ቆጠረው፤ ወደ ፍጻሜም አመጣው ማለት ነው።+ 27  “ቲቄል ማለት በሚዛን ተመዘንክ፤ ጉድለትም ተገኘብህ ማለት ነው። 28  “ፊሬስ ማለት ደግሞ መንግሥትህ ተከፈለ፤ ለሜዶናውያንና ለፋርሳውያን ተሰጠ ማለት ነው።”+ 29  በዚህ ጊዜ ቤልሻዛር ትእዛዝ አስተላለፈ፤ ዳንኤልንም ሐምራዊ ልብስ አለበሱት፤ በአንገቱም ላይ የወርቅ ሐብል አጠለቁለት፤ በመንግሥትም ላይ ሦስተኛ ገዢ ሆኖ መሾሙን አወጁ።+ 30  በዚያኑ ሌሊት ከለዳዊው ንጉሥ ቤልሻዛር ተገደለ።+ 31  ሜዶናዊው ዳርዮስም+ መንግሥቱን ተረከበ፤ ዕድሜውም 62 ዓመት ገደማ ነበር።

የግርጌ ማስታወሻ

ወይም “የንጉሡ ፊት ተለወጠ።”
በሟርትና በኮከብ ቆጠራ የተካኑ ሰዎችን ያቀፈ ቡድንን ያመለክታል።
በሟርትና በኮከብ ቆጠራ የተካኑ ሰዎችን ያቀፈ ቡድንን ያመለክታል።
ወይም “ጥሩ ችሎታ ያለው ሰው።”
ቃል በቃል “የተቋጠረውን የመፍታት።”
ቃል በቃል “የተቋጠረውን የመፍታት።”