ለገላትያ ሰዎች የተጻፈ ደብዳቤ 1:1-24

  • ሰላምታ (1-5)

  • “ሌላ ምሥራች የለም” (6-9)

  • ጳውሎስ የሰበከው ምሥራች ከአምላክ የመጣ ነው (10-12)

  • የጳውሎስ መለወጥና መጀመሪያ ላይ ያደረጋቸው ነገሮች (13-24)

1  ከሰዎች ወይም በሰው ሳይሆን በኢየሱስ ክርስቶስ+ እንዲሁም እሱን ከሞት ባስነሳውና አባታችን በሆነው አምላክ+ አማካኝነት ሐዋርያ ከሆነው ከጳውሎስ፣  እንዲሁም አብረውኝ ካሉት ወንድሞች ሁሉ፣ በገላትያ ላሉት ጉባኤዎች፦  አባታችን ከሆነው አምላክና ከጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን።  ኢየሱስ እንደ አምላካችንና እንደ አባታችን ፈቃድ+ አሁን ካለው ክፉ ሥርዓት*+ እኛን ለመታደግ ስለ ኃጢአታችን ራሱን ሰጠ፤+  ለዘላለም ለአምላክ ክብር ይሁን። አሜን።  አምላክ በክርስቶስ ጸጋ ከጠራችሁ በኋላ እንዲህ በፍጥነት ከእሱ ዞር ማለታችሁና* ለሌላ ዓይነት ምሥራች ጆሯችሁን መስጠታችሁ ደንቆኛል።+  እንደ እውነቱ ከሆነ ሌላ ምሥራች የለም፤ ሆኖም እናንተን የሚረብሹና+ ስለ ክርስቶስ የሚናገረውን ምሥራች ለማጣመም የሚፈልጉ አንዳንድ ሰዎች አሉ።  ይሁን እንጂ ከመካከላችን አንዱ ወይም ከሰማይ የወረደ መልአክ፣ እኛ ከሰበክንላችሁ ምሥራች የተለየ ምሥራች ቢሰብክላችሁ የተረገመ ይሁን።  ቀደም ሲል እንደተናገርነው፣ አሁንም ደግሜ እላለሁ፣ ማንም ይሁን ማን ከተቀበላችሁት የተለየ ምሥራች ቢሰብክላችሁ የተረገመ ይሁን። 10  አሁን እኔ ጥረት የማደርገው የሰውን ሞገስ ለማግኘት ነው ወይስ የአምላክን? ደግሞስ ሰዎችን ለማስደሰት እየሞከርኩ ነው? አሁንም ሰዎችን እያስደሰትኩ ከሆነ የክርስቶስ ባሪያ አይደለሁም ማለት ነው። 11  ወንድሞች፣ እኔ የሰበክሁላችሁ ምሥራች ከሰው የመነጨ ምሥራች እንዳልሆነ ላሳውቃችሁ እወዳለሁ፤+ 12  ኢየሱስ ክርስቶስ በራእይ ገለጠልኝ እንጂ የተቀበልኩትም ሆነ የተማርኩት ከሰው አይደለምና። 13  በእርግጥ፣ በአይሁዳውያን ሃይማኖት+ ሳለሁ ምን ዓይነት ሰው እንደነበርኩ ሰምታችኋል፤ የአምላክን ጉባኤ ክፉኛ* አሳድድና ለማጥፋት ጥረት አደርግ ነበር፤+ 14  ለአባቶቼ ወግ ከፍተኛ ቅንዓት ስለነበረኝ ከወገኖቼ መካከል በእኔ ዕድሜ ካሉት ከብዙዎቹ የበለጠ በአይሁዳውያን ሃይማኖት የላቀ እድገት እያደረግኩ ነበር።+ 15  ሆኖም ከእናቴ ማህፀን እንድለይ* ያደረገኝና በጸጋው አማካኝነት የጠራኝ አምላክ+ 16  ስለ ክርስቶስ የሚገልጸውን ምሥራች ለአሕዛብ እንዳውጅ+ ልጁን በእኔ አማካኝነት ለመግለጥ በወደደ ጊዜ ከማንም ሰው* ጋር ወዲያው አልተማከርኩም፤ 17  በኢየሩሳሌም ወደሚገኙት ከእኔ በፊት ሐዋርያት ወደሆኑትም አልሄድኩም፤ ከዚህ ይልቅ ወደ ዓረብ አገር ሄድኩ፤ ከዚያም ወደ ደማስቆ+ ተመለስኩ። 18  ከዚያም ከሦስት ዓመት በኋላ ኬፋን*+ ለመጠየቅ ወደ ኢየሩሳሌም ወጣሁ፤+ ከእሱም ጋር 15 ቀን ተቀመጥኩ። 19  ሆኖም ከጌታ ወንድም ከያዕቆብ+ በስተቀር ከሌሎቹ ሐዋርያት መካከል ማንንም አላየሁም። 20  እንግዲህ እየጻፍኩላችሁ ያለሁት ነገር ውሸት እንዳልሆነ በአምላክ ፊት ላረጋግጥላችሁ እወዳለሁ። 21  ከዚያ በኋላ በሶርያና በኪልቅያ ወዳሉ ክልሎች ሄድኩ።+ 22  ሆኖም በይሁዳ ያሉ የክርስቲያን ጉባኤዎች በአካል አይተውኝ አያውቁም ነበር። 23  ይሁንና “ከዚህ ቀደም ያሳድደን የነበረው ሰው፣+ ሊያጠፋው ይፈልግ ስለነበረው እምነት+ የሚገልጸውን ምሥራች አሁን እየሰበከ ነው” የሚል ወሬ ብቻ ይሰሙ ነበር። 24  ስለዚህ በእኔ ምክንያት አምላክን ከፍ ከፍ ያደርጉ ጀመር።

የግርጌ ማስታወሻ

ወይም “ክፉ ዘመን።” የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ወይም “እንዲህ በፍጥነት ከእሱ እየራቃችሁ መሄዳችሁና።”
ቃል በቃል “ያለልክ።”
ወይም “እንድወለድ።”
ቃል በቃል “ከሥጋና ከደም።”
ጴጥሮስ ተብሎም ይጠራል።