ለገላትያ ሰዎች የተጻፈ ደብዳቤ 4:1-31
4 እንግዲህ ይህን እላለሁ፦ ወራሹ የሁሉም ነገር ጌታ ቢሆንም እንኳ ሕፃን እስከሆነ ድረስ ከባሪያ በምንም አይለይም፤
2 ይልቁንም አባቱ አስቀድሞ የወሰነው ቀን እስኪደርስ ድረስ በሞግዚቶችና በመጋቢዎች ሥር ሆኖ ይቆያል።
3 በተመሳሳይ እኛም ልጆች በነበርንበት ጊዜ በዓለም ውስጥ ላሉ ተራ ነገሮች ባሪያ ሆነን ቆይተናል።+
4 ሆኖም ዘመኑ ሙሉ በሙሉ የሚጠናቀቅበት ጊዜ ሲደርስ አምላክ ከሴት የተወለደውንና+ በሕግ ሥር የነበረውን ልጁን ላከ፤+
5 ይህን ያደረገው እኛን ልጆቹ አድርጎ መውሰድ ይችል ዘንድ+ በሕግ ሥር ያሉትን ዋጅቶ ነፃ ለማውጣት ነው።+
6 አሁን እናንተ ልጆች ስለሆናችሁ አምላክ የልጁን መንፈስ ወደ ልባችን+ ልኳል፤+ ይህም መንፈስ “አባ፣* አባት!” እያለ ይጣራል።+
7 በመሆኑም ከእንግዲህ ወዲህ ልጅ ነህ እንጂ ባሪያ አይደለህም፤ ልጅ ከሆንክ ደግሞ አምላክ ወራሽም አድርጎሃል።+
8 ይሁንና አምላክን ከማወቃችሁ በፊት በእርግጥ አማልክት ላልሆኑ ባሪያዎች ሆናችሁ ትገዙ ነበር።
9 አሁን ግን አምላክን አውቃችኋል፤ እንዲያውም አምላክ እናንተን አውቋችኋል፤ ታዲያ ደካማና ከንቱ ወደሆኑ ተራ ነገሮች መመለስና+ እንደገና ለእነዚህ ነገሮች ባሪያ መሆን ትፈልጋላችሁ?+
10 ቀናትን፣ ወራትን፣+ ወቅቶችንና ዓመታትን በጥንቃቄ እየጠበቃችሁ ታከብራላችሁ።
11 የእናንተ ሁኔታ ያሳስበኛል፤ ምክንያቱም ለእናንተ የደከምኩት በከንቱ እንዳይሆን እሰጋለሁ።
12 ወንድሞች፣ እንደ እኔ ሁኑ ብዬ እለምናችኋለሁ፤ ምክንያቱም እኔም በአንድ ወቅት እንደ እናንተ ነበርኩ።+ እናንተ ምንም የበደላችሁኝ ነገር የለም።
13 በተጨማሪም ለመጀመሪያ ጊዜ ለእናንተ ምሥራቹን ለመስበክ አጋጣሚ ያገኘሁት በመታመሜ የተነሳ እንደነበር ታውቃላችሁ።
14 ሕመሜ ፈተና ሆኖባችሁ የነበረ ቢሆንም እንኳ አልናቃችሁኝም ወይም አልተጸየፋችሁኝም፤* ከዚህ ይልቅ እንደ አምላክ መልአክ ወይም እንደ ክርስቶስ ኢየሱስ ተቀበላችሁኝ።
15 ታዲያ ያ ሁሉ ደስታችሁ የት ጠፋ? የሚቻል ቢሆን ኖሮ ዓይናችሁን እንኳ አውጥታችሁ ትሰጡኝ እንደነበር እርግጠኛ ነኝ።+
16 ታዲያ እውነቱን ስለምነግራችሁ ጠላት ሆንኩባችሁ ማለት ነው?
17 እነሱ ወደ ራሳቸው ሊስቧችሁ ከፍተኛ ጥረት ያደርጋሉ፤ ይህን የሚያደርጉት ግን ለበጎ ሳይሆን እናንተን ከእኔ በማራቅ እነሱን አጥብቃችሁ እንድትከተሏቸው ለማድረግ ነው።
18 ይሁን እንጂ አንድ ሰው ምንጊዜም እናንተን አጥብቆ የሚፈልገው ለበጎ ዓላማ ከሆነ ጥሩ ነው፤ ይህም መሆን ያለበት እኔ ከእናንተ ጋር ስሆን ብቻ አይደለም፤
19 የምወዳችሁ ልጆቼ፣+ ክርስቶስ በውስጣችሁ እስኪቀረጽ ድረስ በእናንተ ምክንያት እንደገና ምጥ ይዞኛል።
20 በእናንተ ግራ ስለተጋባሁ አሁን በመካከላችሁ ተገኝቼ ለየት ባለ መንገድ ላነጋግራችሁ ብችል ደስ ባለኝ ነበር።
21 እናንተ በሕግ ሥር መኖር የምትፈልጉ እስቲ ንገሩኝ፤ ሕጉ የሚለውን አትሰሙም?
22 ለምሳሌ ያህል፣ አብርሃም አንዱ ከአገልጋዪቱ፣+ ሌላው ደግሞ ከነፃዪቱ ሴት+ የተወለዱ ሁለት ወንዶች ልጆች እንደነበሩት ተጽፏል፤
23 ሆኖም ከአገልጋዪቱ የተገኘው ልጅ የተወለደው በሥጋዊ መንገድ*+ ሲሆን ከነፃዪቱ ሴት የተገኘው ልጅ ደግሞ የተወለደው በተስፋ ቃል መሠረት ነው።+
24 እነዚህ ሴቶች ሁለት ቃል ኪዳኖችን ስለሚወክሉ እነዚህ ነገሮች ምሳሌያዊ ትርጉም አላቸው፤ አንደኛው ቃል ኪዳን የተገባው በሲና ተራራ+ ሲሆን በዚህ ቃል ኪዳን ሥር ያሉት ልጆች ሁሉ ባሪያዎች ናቸው፤ ይህ ቃል ኪዳን ደግሞ አጋርን ያመለክታል።
25 አጋር፣ በዓረብ አገር የሚገኘውን የሲና ተራራ+ የምትወክል ሲሆን ዛሬ ካለችው ኢየሩሳሌም ጋር ትመሳሰላለች፤ ኢየሩሳሌም ከልጆቿ ጋር በባርነት ሥር ናትና።
26 ላይኛይቱ ኢየሩሳሌም ግን ነፃ ናት፤ እሷም እናታችን ናት።
27 “አንቺ የማትወልጂ መሃን ሴት፣ ደስ ይበልሽ፤ አንቺ ምጥ የማታውቂ ሴት፣ እልል በይ፣ ጩኺም፤ ምክንያቱም ባል ካላት ሴት ይልቅ የተተወችው ሴት ልጆች እጅግ በዝተዋል” ተብሎ ተጽፏልና።+
28 እንግዲህ ወንድሞች፣ እንደ ይስሐቅ የተስፋው ቃል ልጆች ናችሁ።+
29 ሆኖም ያን ጊዜ በሥጋዊ መንገድ* የተወለደው በመንፈስ የተወለደውን ማሳደድ እንደጀመረ+ ሁሉ አሁንም እንደዚያው ነው።+
30 ይሁንና ቅዱስ መጽሐፉ ምን ይላል? “የአገልጋዪቱ ልጅ ከነፃዪቱ ልጅ ጋር በምንም ዓይነት አብሮ ስለማይወርስ አገልጋዪቱን ከነልጅዋ አባር።”+
31 ስለዚህ ወንድሞች፣ እኛ የነፃዪቱ ልጆች እንጂ የአገልጋዪቱ ልጆች አይደለንም።