ለፊልጵስዩስ ሰዎች የተጻፈ ደብዳቤ 1:1-30

  • ሰላምታ (1, 2)

  • ለአምላክ የቀረበ ምስጋና፤ የጳውሎስ ጸሎት (3-11)

  • አስቸጋሪ ሁኔታ ቢኖርም ምሥራቹ ተስፋፋ (12-20)

  • ‘የምኖረው ለክርስቶስ ነው፤ ብሞት ደግሞ እጠቀማለሁ’ (21-26)

  • ‘አኗኗራችሁ ከምሥራቹ ጋር የሚስማማ ይሁን’ (27-30)

1  የክርስቶስ ኢየሱስ ባሪያዎች ከሆኑት ከጳውሎስና ከጢሞቴዎስ፣ ሽማግሌዎችንና የጉባኤ አገልጋዮችን+ ጨምሮ በፊልጵስዩስ+ ለሚገኙ ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር አንድነት ላላቸው ቅዱሳን ሁሉ፦  አባታችን ከሆነው አምላክና ከጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን።  እናንተን ባስታወስኩ ቁጥር ሁልጊዜ አምላኬን አመሰግናለሁ፤  ይህን የማደርገው ስለ እያንዳንዳችሁ ምልጃ ባቀረብኩ ጊዜ ሁሉ ነው። ደግሞም ምንጊዜም ምልጃ የማቀርበው በደስታ ነው፤+  ምክንያቱም ምሥራቹን ከሰማችሁበት ከመጀመሪያው ቀን አንስቶ እስከዚህ ጊዜ ድረስ ለምሥራቹ አስተዋጽኦ* ስታደርጉ ቆይታችኋል።  በእናንተ መካከል መልካም ሥራ የጀመረው አምላክ፣ ሥራውን እስከ ክርስቶስ ኢየሱስ ቀን+ ድረስ ወደ ፍጻሜ እንደሚያመጣው እርግጠኛ ነኝ።+  ስለ እናንተ ስለ ሁላችሁ እንዲህ ብዬ ማሰቤ ትክክል ነው፤ ምክንያቱም በእስራቴም+ ሆነ ለምሥራቹ ስሟገትና በሕግ የጸና እንዲሆን ለማድረግ ስጥር+ ከእኔ ጋር የጸጋው ተካፋዮች የሆናችሁት እናንተ በልቤ ውስጥ ናችሁ።  ክርስቶስ ኢየሱስ ባለው ዓይነት ጥልቅ ፍቅር እናንተ ሁላችሁም በጣም እንደምትናፍቁኝ አምላክ ምሥክሬ ነው።  ፍቅራችሁ ከአምላክ ፈቃድ ትክክለኛ እውቀትና+ ጥልቅ ግንዛቤ+ ጋር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ እንዲሄድ መጸለዬን እቀጥላለሁ፤+ 10  ደግሞም ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች ለይታችሁ በማወቅ+ እስከ ክርስቶስ ቀን ድረስ እንከን የማይገኝባችሁ እንድትሆኑና ሌሎችን እንዳታሰናክሉ+ 11  እንዲሁም ለአምላክ ክብርና ምስጋና በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል የተትረፈረፈ የጽድቅ ፍሬ እንድታፈሩ እጸልያለሁ።+ 12  እንግዲህ ወንድሞች፣ እኔ ያጋጠመኝ ሁኔታ ምሥራቹ ይበልጥ እንዲስፋፋ አስተዋጽኦ እንዳደረገ እንድታውቁ እወዳለሁ፤ 13  የታሰርኩት+ የክርስቶስ አገልጋይ በመሆኔ የተነሳ እንደሆነ በንጉሠ ነገሥቱ የክብር ዘብ ሁሉና በሌሎች ሰዎች ሁሉ ዘንድ በይፋ ታውቋል።+ 14  ጌታን የሚያገለግሉ አብዛኞቹ ወንድሞች በእኔ መታሰር ምክንያት የልበ ሙሉነት ስሜት አድሮባቸው የአምላክን ቃል ያለፍርሃት ለመናገር ከቀድሞው የበለጠ ድፍረት እያሳዩ ነው። 15  እርግጥ፣ አንዳንዶች ክርስቶስን እየሰበኩ ያሉት በቅናትና በፉክክር መንፈስ ነው፤ ይሁንና ሌሎች ይህን እያደረጉ ያሉት በጥሩ ዓላማ ነው። 16  እነዚህ፣ እኔ ለምሥራቹ ለመሟገት+ እንደተሾምኩ ስለሚያውቁ ስለ ክርስቶስ የሚያውጁት ከፍቅር ተነሳስተው ነው፤ 17  እነዚያ ግን በእስራቴ ላይ ችግር ሊፈጥሩብኝ ስላሰቡ ይህን የሚያደርጉት በቅን ልቦና ሳይሆን በጥላቻ ተነሳስተው ነው። 18  ታዲያ ይህ ምን አስከተለ? በማስመሰልም ሆነ በእውነት፣ በሁሉም መንገድ ክርስቶስ እንዲሰበክ አስችሏል፤ በዚህ ደግሞ ደስተኛ ነኝ። ወደፊትም ቢሆን መደሰቴን እቀጥላለሁ፤ 19  ይህ በእናንተ ምልጃ+ እንዲሁም የኢየሱስ ክርስቶስ መንፈስ በሚሰጠኝ ድጋፍ+ መዳን እንደሚያስገኝልኝ አውቃለሁና። 20  ይህም በጉጉት ከምጠባበቀው ነገርና ከተስፋዬ ጋር በሚስማማ ሁኔታ በማንኛውም መንገድ እንዳላፍር ነው፤ ከዚህ ይልቅ በነፃነት በመናገር በሕይወትም ሆነ በሞት እንደ ወትሮው ሁሉ አሁንም ክርስቶስን በሰውነቴ አማካኝነት ከፍ ከፍ አደርገው ዘንድ ነው።+ 21  እኔ ብኖር የምኖረው ለክርስቶስ ነውና፤+ ብሞት ደግሞ እጠቀማለሁ።+ 22  በሥጋ መኖሬን የምቀጥል ከሆነ በማከናውነው ሥራ አማካኝነት ብዙ ፍሬ ማፍራት እችላለሁ፤ ይሁንና የትኛውን እንደምመርጥ አላሳውቅም። 23  በእነዚህ ሁለት ነገሮች አጣብቂኝ ውስጥ ገብቻለሁ፤ ምኞቴ ነፃ መለቀቅና ከክርስቶስ ጋር መሆን ነውና፤+ እርግጡን ለመናገር ይህ እጅግ የተሻለ ነው።+ 24  ይሁን እንጂ ለእናንተ ሲባል በሥጋ መኖሬ ይበልጥ አስፈላጊ ነው። 25  በመሆኑም በዚህ ጉዳይ እርግጠኛ ስለሆንኩ እድገት እንድታደርጉና በእምነት ደስታ እንድታገኙ ስል በሥጋ እንደምቆይና ከሁላችሁም ጋር መኖሬን እንደምቀጥል አውቃለሁ፤ 26  ይህም ዳግመኛ በእናንተ መካከል ስገኝ በእኔ ምክንያት ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር በተያያዘ ደስታችሁ ይትረፈረፍ ዘንድ ነው። 27  ብቻ አኗኗራችሁ ስለ ክርስቶስ ከሚገልጸው ምሥራች ጋር የሚስማማ ይሁን፤*+ ይህም መጥቼ ባያችሁም ሆነ ከእናንተ ብርቅ አንድ ላይ ሆናችሁ በምሥራቹ ላይ ያላችሁን እምነት ጠብቃችሁ ለመኖር በአንድ ነፍስ* በመጋደል በአንድ መንፈስ ጸንታችሁ መቆማችሁን+ 28  እንዲሁም በምንም መንገድ በጠላቶቻችሁ አለመሸበራችሁን እሰማና አውቅ ዘንድ ነው። ይህ ነገር እነሱ እንደሚጠፉ+ እናንተ ግን እንደምትድኑ የሚያሳይ+ ማስረጃ ነው፤ ይህም ከአምላክ የተሰጠ ነው። 29  እናንተ በክርስቶስ እንድታምኑ ብቻ ሳይሆን ለእሱ ስትሉ መከራ እንድትቀበሉም መብት ተሰጥቷችኋል።+ 30  እኔ ስጋፈጥ ያያችሁትንና+ አሁንም እየተጋፈጥኩት እንዳለሁ የሰማችሁትን ያንኑ ትግል እናንተም እየተጋፈጣችሁ ነውና።

የግርጌ ማስታወሻ

ወይም “ምሥራቹን በማስፋፋቱ ሥራ ተሳትፎ።”
ወይም “ዜጎች እንደመሆናችሁ መጠን ስለ ክርስቶስ ከሚገልጸው ምሥራች ጋር በሚስማማ መንገድ ኑሩ።”
ወይም “በአንድነት።”