ለፊልጵስዩስ ሰዎች የተጻፈ ደብዳቤ 2:1-30

  • ክርስቲያናዊ ትሕትና (1-4)

  • ክርስቶስ ያሳየው ትሕትናና ያገኘው ክብር (5-11)

  • የራሳችሁን መዳን ከፍጻሜ አድርሱ (12-18)

    • “እንደ ብርሃን አብሪዎች ታበራላችሁ” (15)

  • ጳውሎስ ጢሞቴዎስንና አፍሮዲጡን ለመላክ አሰበ (19-30)

2  እንግዲህ ከክርስቶስ ጋር ባላችሁ አንድነት በመካከላችሁ ማንኛውም ዓይነት ማበረታቻ፣ ማንኛውም ዓይነት ፍቅራዊ ማጽናኛ፣ ማንኛውም ዓይነት መንፈሳዊ ኅብረት፣ ማንኛውም ዓይነት ጥልቅ ፍቅርና ርኅራኄ ካለ፣  ፍጹም አንድነት ኖሯችሁና* አንድ ዓይነት አስተሳሰብ ይዛችሁ በአንድ ሐሳብና በአንድ ፍቅር በመኖር ደስታዬን የተሟላ አድርጉልኝ።+  ሌሎች ከእናንተ እንደሚበልጡ በትሕትና አስቡ+ እንጂ በጠበኝነት መንፈስ+ ወይም በትምክህተኝነት+ ምንም ነገር አታድርጉ፤  ስለ ራሳችሁ ፍላጎት ብቻ ከማሰብ ይልቅ+ እያንዳንዳችሁ ለሌሎች ሰዎች ፍላጎትም ትኩረት ስጡ።+  ክርስቶስ ኢየሱስ የነበረው ይህ አስተሳሰብ በእናንተም ዘንድ ይኑር፤+  እሱ በአምላክ መልክ ይኖር የነበረ ቢሆንም+ ከአምላክ ጋር እኩል ለመሆን የመሞከር ሐሳብም እንኳ ወደ አእምሮው አልመጣም።+  ከዚህ ይልቅ ራሱን ባዶ በማድረግ የባሪያን መልክ ያዘ፤+ ደግሞም ሰው ሆነ።*+  ከዚህም በላይ ሰው ሆኖ በመጣ ጊዜ* ራሱን ዝቅ በማድረግ እስከ ሞት ድረስ ያውም በመከራ እንጨት*+ ላይ እስከ መሞት ድረስ ታዛዥ ሆኗል።+  በዚህም ምክንያት አምላክ የላቀ ቦታ በመስጠት ከፍ ከፍ አደረገው፤+ እንዲሁም ከሌላ ከማንኛውም ስም በላይ የሆነ ስም በደግነት ሰጠው፤+ 10  ይህም በሰማይና በምድር እንዲሁም ከምድር በታች ያሉ ሁሉ በኢየሱስ ስም ይንበረከኩ ዘንድ ነው፤+ 11  ምላስም ሁሉ ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታ እንደሆነ በመመሥከር+ አባት ለሆነው አምላክ ክብር ያመጣ ዘንድ ነው። 12  ስለዚህ የተወደዳችሁ ወንድሞቼ፣ እኔ አብሬያችሁ ስሆን ብቻ ሳይሆን ይልቁንም አሁን አብሬያችሁ በሌለሁበት ወቅት ሁልጊዜ ታዛዥ እንደሆናችሁ ሁሉ በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ የራሳችሁን መዳን ከፍጻሜ ለማድረስ ተግታችሁ ሥሩ። 13  ለተግባር የሚያነሳሳ ፍላጎት እንዲያድርባችሁም ሆነ ኃይል እንድታገኙ በማድረግ እሱ ደስ ለሚሰኝበት ነገር ብርታት የሚሰጣችሁ አምላክ ነውና። 14  ምንጊዜም ማንኛውንም ነገር ሳታጉረመርሙና+ ሳትከራከሩ አድርጉ፤+ 15  ይህም በጠማማና በወልጋዳ ትውልድ+ መካከል እንከንና እድፍ የሌለባችሁ ንጹሐን የአምላክ ልጆች እንድትሆኑ ነው።+ በዚህ ዓለም ውስጥ እንደ ብርሃን አብሪዎች ታበራላችሁ፤+ 16  ይህን የምታደርጉትም የሕይወትን ቃል አጥብቃችሁ በመያዝ ነው።+ ያን ጊዜ ሩጫዬም ሆነ ድካሜ ከንቱ ሆኖ እንዳልቀረ ስለምገነዘብ በክርስቶስ ቀን ሐሴት የማደርግበት ነገር ይኖረኛል። 17  ይሁንና በእምነት ተነሳስታችሁ በምታቀርቡት መሥዋዕትና+ ቅዱስ አገልግሎት* ላይ እንደ መጠጥ መባ ብፈስ+ እንኳ ደስ ይለኛል፤* እንዲሁም ከሁላችሁም ጋር ሐሴት አደርጋለሁ። 18  እናንተም ልክ እንደዚሁ ተደሰቱ፤ ከእኔም ጋር ሐሴት አድርጉ። 19  ስለ እናንተ በምሰማበት ጊዜ እንድበረታታ፣ ጌታ ኢየሱስ ቢፈቅድ ጢሞቴዎስን+ በቅርቡ ወደ እናንተ እንደምልከው ተስፋ አደርጋለሁ። 20  ስለ እናንተ ጉዳይ ከልብ የሚጨነቅ እንደ እሱ ያለ በጎ አመለካከት ያለው ሌላ ማንም የለኝምና። 21  ሌሎቹ ሁሉ የኢየሱስ ክርስቶስን ሳይሆን የራሳቸውን ፍላጎት ለማሟላት ይሯሯጣሉ። 22  እሱ ግን ከአባቱ ጋር እንደሚሠራ ልጅ+ ምሥራቹን በማስፋፋቱ ሥራ ከእኔ ጋር እንደ ባሪያ በማገልገል ማንነቱን እንዴት እንዳስመሠከረ ታውቃላችሁ። 23  በመሆኑም የእኔ ጉዳይ ምን ላይ እንደደረሰ ሳውቅ ወዲያውኑ ወደ እናንተ ልልከው ያሰብኩት እሱን ነው። 24  እንዲያውም የጌታ ፈቃድ ከሆነ እኔ ራሴም በቅርቡ እንደምመጣ እርግጠኛ ነኝ።+ 25  ለአሁኑ ግን በሚያስፈልገኝ ሁሉ በግል እንዲያገለግለኝ የላካችሁትን ወንድሜን፣ የሥራ ባልደረባዬንና አብሮኝ ወታደር የሆነውን አፍሮዲጡን ወደ እናንተ መላኩን አስፈላጊ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፤+ 26  ምክንያቱም ሁላችሁንም ለማየት ናፍቋል፤ በተጨማሪም እንደታመመ መስማታችሁን ስላወቀ ተጨንቋል። 27  በእርግጥም በጠና ታሞ ሞት አፋፍ ደርሶ ነበር፤ ሆኖም አምላክ ምሕረት አደረገለት፤ ደግሞም ምሕረት ያደረገው ለእሱ ብቻ ሳይሆን በሐዘን ላይ ሐዘን እንዳይደራረብብኝ ለእኔም ጭምር ነው። 28  ስለዚህ ስታዩት ዳግመኛ እንድትደሰቱና የእኔም ጭንቀት እንዲቀል እሱን በተቻለ ፍጥነት ወደ እናንተ እልከዋለሁ። 29  ስለዚህ የጌታን ተከታዮች ወትሮ በምትቀበሉበት መንገድ በታላቅ ደስታ ተቀበሉት፤ እንዲሁም እንደ እሱ ያሉትን ሰዎች በአክብሮት ያዟቸው፤+ 30  ምክንያቱም እሱ፣ እናንተ እዚህ ሆናችሁ በግል ልትሰጡኝ ያልቻላችሁትን አገልግሎት በሚገባ ለማሟላት ሲል ከክርስቶስ ሥራ* የተነሳ ሕይወቱን* ለአደጋ በማጋለጥ ለሞት ተቃርቦ ነበር።+

የግርጌ ማስታወሻ

ወይም “በአንድ ነፍስ ተሳስራችሁና።”
ቃል በቃል “በሰዎች አምሳል ተገኘ።”
ቃል በቃል “በሰው መልክ በተገኘ ጊዜ።”
ወይም “ሕዝባዊ አገልግሎት።”
እዚህ ላይ ጳውሎስ የመጠጥ መባን ምሳሌያዊ በሆነ መንገድ የተጠቀመ ሲሆን ክርስቲያን ባልንጀሮቹን ለመጥቀም ሲል ራሱን ሳይቆጥብ ለመስጠት ፈቃደኛ መሆኑን ያሳያል።
“ከጌታ ሥራ” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ወይም “ነፍሱን።”