ለፊልጵስዩስ ሰዎች የተጻፈ ደብዳቤ 4:1-23

  • አንድነት፣ ደስታ፣ ንጹሕ ሐሳብ (1-9)

    • “ስለ ምንም ነገር አትጨነቁ” (6, 7)

  • ለፊልጵስዩስ ወንድሞች ያለውን አድናቆት ገለጸ (10-20)

  • የስንብት ቃላት (21-23)

4  ስለዚህ የምወዳችሁና የምናፍቃችሁ እንዲሁም ደስታዬና አክሊሌ+ የሆናችሁ ወንድሞቼና ወዳጆቼ፣ አሁን በገለጽኩላችሁ መሠረት ከጌታ ጋር ባላችሁ አንድነት ጸንታችሁ ቁሙ።+  በጌታ አንድ ዓይነት አስተሳሰብ እንዲኖራቸው+ ኤዎድያንን እመክራለሁ፤ ሲንጤኪንም እመክራለሁ።  አዎ፣ እውነተኛ የሥራ አጋሬ የሆንከው አንተም፣ ከቀሌምንጦስና ስማቸው በሕይወት መጽሐፍ ውስጥ ከሰፈረው+ ከቀሩት የሥራ ባልደረቦቼ ጋር ለምሥራቹ ሲሉ ከጎኔ ተሰልፈው ብዙ የደከሙትን* እነዚህን ሴቶች መርዳትህን እንድትቀጥል አደራ እልሃለሁ።  ሁልጊዜ በጌታ ደስ ይበላችሁ። ደግሜ እላለሁ ደስ ይበላችሁ!+  ምክንያታዊነታችሁ*+ በሰው ሁሉ ዘንድ የታወቀ ይሁን። ጌታ ቅርብ ነው።  ስለ ምንም ነገር አትጨነቁ፤+ ከዚህ ይልቅ ስለ ሁሉም ነገር በጸሎትና በምልጃ ከምስጋና ጋር ልመናችሁን ለአምላክ አቅርቡ፤+  ከመረዳት ችሎታ ሁሉ በላይ የሆነው የአምላክ ሰላም+ በክርስቶስ ኢየሱስ አማካኝነት ልባችሁንና+ አእምሯችሁን* ይጠብቃል።  በመጨረሻም ወንድሞች፣ እውነት የሆነውን ነገር ሁሉ፣ ቁም ነገር ያለበትን ነገር ሁሉ፣ ጽድቅ የሆነውን ነገር ሁሉ፣ ንጹሕ የሆነውን ነገር ሁሉ፣ ተወዳጅ የሆነውን ነገር ሁሉ፣ በመልካም የሚነሳውን ነገር ሁሉ፣ በጎ የሆነውን ሁሉና ምስጋና የሚገባውን ነገር ሁሉ ማሰባችሁን* አታቋርጡ።+  ከእኔ የተማራችሁትንም ሆነ የተቀበላችሁትን እንዲሁም የሰማችሁትንና ያያችሁትን ነገር ሁሉ ሥራ ላይ አውሉ፤+ የሰላምም አምላክ ከእናንተ ጋር ይሆናል። 10  አሁን ለእኔ እንደገና ማሰብ በመጀመራችሁ በጌታ እጅግ ደስ ይለኛል።+ ስለ እኔ ደህንነት ታስቡ የነበረ ቢሆንም ይህን በተግባር ለማሳየት የሚያስችል አጋጣሚ አላገኛችሁም። 11  ይህን ስል እንደተቸገርኩ መናገሬ አይደለም፤ ምክንያቱም በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ ብሆን ባለኝ ረክቼ መኖርን ተምሬአለሁ።+ 12  በትንሽ ነገር እንዴት መኖር እንደሚቻልም+ ሆነ ብዙ አግኝቶ እንዴት መኖር እንደሚቻል አውቃለሁ። በማንኛውም ነገርና በሁሉም ሁኔታ ጠግቦም ሆነ ተርቦ፣ ብዙ አግኝቶም ሆነ አጥቶ መኖር የሚቻልበትን ሚስጥር ተምሬአለሁ። 13  ኃይልን በሚሰጠኝ በእሱ አማካኝነት ለሁሉም ነገር የሚሆን ብርታት አለኝ።+ 14  የሆነ ሆኖ የመከራዬ ተካፋዮች በመሆናችሁ መልካም አድርጋችኋል። 15  እንዲያውም እናንተ የፊልጵስዩስ ወንድሞች፣ ምሥራቹን መጀመሪያ ከሰማችሁ በኋላ ከመቄዶንያ ስወጣ በመስጠትም ሆነ በመቀበል ረገድ ከእናንተ በስተቀር ከእኔ ጋር የተባበረ አንድም ጉባኤ እንዳልነበረ ታውቃላችሁ፤+ 16  በተሰሎንቄ በነበርኩበት ጊዜ የሚያስፈልገኝን ነገር ከአንዴም ሁለቴ ልካችሁልኛልና። 17  ይህን ስል ስጦታ ለማግኘት በመፈለግ ሳይሆን እናንተ የምታገኙት ጥቅም እንዲጨምር የሚያደርገውን ፍሬ ለማየት በመፈለግ ነው። 18  ይሁን እንጂ የሚያስፈልገኝ ነገር ሁሉ፣ እንዲያውም ከሚያስፈልገኝ በላይ አለኝ። የላካችሁልኝን ከአፍሮዲጡ+ ስለተቀበልኩ ሞልቶ ተትረፍርፎልኛል፤ ይህም ጥሩ መዓዛ ያለው ሽታ፣+ ተቀባይነት ያለው መሥዋዕትና አምላክ ደስ የሚሰኝበት ነገር ነው። 19  በአጸፋው ደግሞ አምላኬ እንደ ታላቅ ብልጽግናው መጠን በክርስቶስ ኢየሱስ አማካኝነት የሚያስፈልጋችሁን ሁሉ አሟልቶ ይሰጣችኋል።+ 20  እንግዲህ ለአምላካችንና ለአባታችን ለዘላለም ክብር ይሁን። አሜን። 21  ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር አንድነት ላላቸው ቅዱሳን ሁሉ ሰላምታዬን አድርሱልኝ። ከእኔ ጋር ያሉ ወንድሞች ሰላምታ ልከውላችኋል። 22  ቅዱሳን ሁሉ በተለይ ደግሞ ከቄሳር ቤተሰብ+ የሆኑት ሰላምታ ያቀርቡላችኋል። 23  የጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከምታሳዩት መንፈስ ጋር ይሁን።

የግርጌ ማስታወሻ

ወይም “የተጋደሉትን።”
ቃል በቃል “ገርነታችሁ፤ እሺ ባይነታችሁ።”
ወይም “ሐሳባችሁን።”
ወይም “ማውጠንጠናችሁን፤ ማሰላሰላችሁን።”