አንደኛ ሳሙኤል 11:1-15

  • ሳኦል አሞናውያንን ድል መታ (1-11)

  • የሳኦል ንግሥና በድጋሚ ጸና (12-15)

11  ከዚያም አሞናዊው+ ናሃሽ ወጥቶ በጊልያድ የምትገኘውን ኢያቢስን ከበባት። የኢያቢስ+ ሰዎች በሙሉ ናሃሽን “ከእኛ ጋር ቃል ኪዳን ግባ፤* እኛም እናገለግልሃለን” አሉት።  አሞናዊው ናሃሽም “ከእናንተ ጋር ቃል ኪዳን የምገባው የእያንዳንዳችሁ ቀኝ ዓይን ከወጣ ነው። ይህን የማደርገውም መላውን እስራኤል ለማዋረድ ስል ነው” አላቸው።  የኢያቢስ ሽማግሌዎችም “ወደ መላው የእስራኤል ግዛት መልእክተኞችን እንድንልክ የሰባት ቀን ጊዜ ስጠን። ከዚያም የሚያድነን ሰው ከሌለ ለአንተ እጃችንን እንሰጣለን” ሲሉ መለሱለት።  መልእክተኞቹም ሳኦል ወደሚገኝበት ወደ ጊብዓ+ መጥተው ይህን መልእክት ለሕዝቡ ተናገሩ፤ ሕዝቡም ሁሉ ድምፁን ከፍ አድርጎ አለቀሰ።  ሳኦል ግን መንጋውን እየነዳ ከመስክ በመምጣት ላይ ነበር፤ ሳኦልም “ሕዝቡ የሚያለቅሰው ምን ሆኖ ነው?” አለ። እነሱም የኢያቢስ ሰዎች ያሏቸውን ነገሩት።  ሳኦልም ይህን ሲሰማ የአምላክ መንፈስ ኃይል ሰጠው፤+ ቁጣውም ነደደ።  እሱም ጥንድ በሬዎችን ወስዶ ቆራረጣቸው፤ እነዚህንም በመልእክተኞቹ እጅ አስይዞ “ሳኦልንና ሳሙኤልን የማይከተል ማንኛውም ሰው ከብቱ እንዲህ ይቆራረጣል!” በማለት እንዲናገሩ ወደ መላው የእስራኤል ግዛት ላካቸው። በሕዝቡም ላይ የይሖዋ ፍርሃት ስለወደቀ ሕዝቡ እንደ አንድ ሰው ሆኖ ወጣ።  ከዚያም ሳኦል ሰዎቹን ቤዜቅ ላይ ቆጠራቸው፤ እነሱም 300,000 እስራኤላውያንና 30,000 የይሁዳ ሰዎች ነበሩ።  የመጡትንም መልእክተኞች እንዲህ አሏቸው፦ “በጊልያድ ባለችው በኢያቢስ የሚኖሩትን ሰዎች ‘በነገው ዕለት ፀሐይዋ በምትከርበት ጊዜ መዳን ታገኛላችሁ’ በሏቸው።” ከዚያም መልእክተኞቹ መጥተው ለኢያቢስ ሰዎች ነገሯቸው፤ እነሱም በደስታ ፈነደቁ። 10  ስለሆነም የኢያቢስ ሰዎች “ነገ እጃችንን ለእናንተ እንሰጣለን፤ እናንተም መልካም መስሎ የታያችሁን ሁሉ ልታደርጉብን ትችላላችሁ” አሏቸው።+ 11  በማግስቱ ሳኦል ሕዝቡን በሦስት ቡድን ከፈለው፤ እነሱም በማለዳው ክፍለ ሌሊት* ወደ አሞናውያን+ ሰፈር ገብተው ፀሐይዋ እስክትከር ድረስ መቷቸው። የተረፉትም ቢሆኑ ሁለቱ እንኳ አንድ ላይ መሆን እስከማይችሉ ድረስ ተበታተኑ። 12  ከዚያም ሕዝቡ ሳሙኤልን “‘አሁን ሳኦል በእኛ ላይ ንጉሥ ሊሆን ነው?’ ሲሉ የነበሩት እነማን ናቸው?+ እነዚህን ሰዎች ስጡንና እንግደላቸው” አለው። 13  ሳኦል ግን “ይህ ዕለት ይሖዋ እስራኤልን ያዳነበት ስለሆነ በዚህ ቀን ማንም ሰው መገደል የለበትም” አለ።+ 14  በኋላም ሳሙኤል ሕዝቡን “ኑ፣ ወደ ጊልጋል+ እንውጣና ንግሥናውን እንደገና እናጽና” አለ።+ 15  በመሆኑም ሕዝቡ ሁሉ ወደ ጊልጋል ሄደ፤ በጊልጋልም ሳኦልን በይሖዋ ፊት አነገሡት። በዚያም በይሖዋ ፊት የኅብረት መሥዋዕቶችን አቀረቡ፤+ ሳኦልና የእስራኤል ሰዎች ሁሉ እጅግ ተደሰቱ።+

የግርጌ ማስታወሻ

ወይም “ስምምነት አድርግ።”
ከሌሊቱ 8 ሰዓት እስከ ጠዋት 12 ሰዓት ገደማ ያለውን ጊዜ ያመለክታል።