አንደኛ ሳሙኤል 14:1-52

  • ዮናታን በሚክማሽ ጀብዱ ፈጸመ (1-14)

  • አምላክ በእስራኤላውያን ጠላቶች ላይ ሽብር ለቀቀባቸው (15-23)

  • ሳኦል ሕዝቡ ምግብ እንዳይቀምስ አስማለ (24-46)

    • ሕዝቡ ሥጋውን ከነደሙ በላ (32-34)

  • ሳኦል ያካሄዳቸው ጦርነቶች፤ የሳኦል ቤተሰብ (47-52)

14  አንድ ቀን የሳኦል ልጅ ዮናታን+ ጋሻ ጃግሬውን “ና፣ በዚያ በኩል ወዳለው የፍልስጤማውያን የጦር ሰፈር እንሻገር” አለው። ይህን ግን ለአባቱ አልነገረውም።  ሳኦልም በጊብዓ+ ዳርቻ በሚግሮን በሚገኘው የሮማን ዛፍ ሥር ሰፍሮ ነበር፤ ከእሱም ጋር 600 ሰዎች ነበሩ።+  (በሴሎ+ የይሖዋ ካህን የሆነው የኤሊ+ ልጅ፣ የፊንሃስ+ ልጅ፣ የኢካቦድ+ ወንድም የአኪጡብ+ ልጅ አኪያህ ኤፉድ ለብሶ ነበር።)+ ሕዝቡም ዮናታን መሄዱን አላወቀም።  ዮናታን ወደ ፍልስጤማውያን የጦር ሰፈር ለመሻገር ባሰበባቸው መተላለፊያዎች መካከል በአንደኛው በኩል እንደ ጥርስ የሾለ ዓለት፣ በሌላኛውም በኩል እንደ ጥርስ የሾለ ዓለት ነበር፤ የአንደኛው ስም ቦጼጽ ሲሆን የሌላኛው ስም ደግሞ ሴኔ ነበር።  አንደኛው ዓለት በሚክማሽ ትይዩ በስተ ሰሜን እንደ ዓምድ ቆሞ ነበር፤ ሌላኛው ደግሞ በጊብዓ+ ትይዩ በስተ ደቡብ ቆሞ ነበር።  በመሆኑም ዮናታን ጋሻ ጃግሬውን “ና፣ ወደ እነዚህ ያልተገረዙ ሰዎች የጦር ሰፈር እንሻገር።+ ይሖዋ በብዙም ሆነ በጥቂት ሰዎች ተጠቅሞ ከማዳን የሚያግደው ነገር ስለሌለ ምናልባት ይሖዋ ስለ እኛ ሲል እርምጃ ይወስድ ይሆናል” አለው።+  በዚህ ጊዜ ጋሻ ጃግሬው “ልብህ ያነሳሳህን ማንኛውንም ነገር አድርግ። ወደፈለግክበት ሂድ፤ እኔም ልብህ ወዳነሳሳህ ወደየትኛውም ቦታ ተከትዬህ እሄዳለሁ” አለው።  ከዚያም ዮናታን እንዲህ አለው፦ “እንግዲያውስ ወደ እነዚያ ሰዎች እንሻገርና እንታያቸው።  እነሱም ‘ወደ እናንተ እስክንመጣ ድረስ ባላችሁበት ጠብቁን’ ካሉን ባለንበት ሆነን እንጠብቃቸዋለን፤ ወደ እነሱም አንወጣም። 10  ይሁንና ‘ውጡና ግጠሙን!’ ካሉን ወደዚያ እንወጣለን፤ ምክንያቱም ይሖዋ እነሱን በእጃችን አሳልፎ ይሰጠናል። እንግዲህ ይህ ምልክት ይሆነናል።”+ 11  ከዚያም ሁለቱ ወጥተው ለፍልስጤማውያን የጦር ሰፈር ታዩ። ፍልስጤማውያኑም “አያችሁ፣ ዕብራውያኑ ከተደበቁባቸው ጉድጓዶች እየወጡ ነው” አሉ።+ 12  በመሆኑም በጦር ሰፈሩ የነበሩት ሰዎች ዮናታንንና ጋሻ ጃግሬውን “ኑ፣ ወደ እኛ ውጡ፤ እናሳያችኋለን!” አሏቸው።+ ዮናታንም ወዲያውኑ ጋሻ ጃግሬውን “ይሖዋ እስራኤላውያን እጅ ላይ ስለሚጥላቸው ተከተለኝ” አለው።+ 13  ዮናታንም በእጁና በእግሩ እየቧጠጠ ወጣ፤ ጋሻ ጃግሬውም ይከተለው ነበር፤ ዮናታንም በፍልስጤማውያን ላይ ጥቃት ሰነዘረ፤ ጋሻ ጃግሬውም ከኋላው እየተከተለ ገደላቸው። 14  ዮናታንና ጋሻ ጃግሬው መጀመሪያ ላይ በሰነዘሩት ጥቃት አንድ ጥማድ በሚያውል የእርሻ መሬት ላይ ግማሽ ትልም በሚያህል ቦታ 20 ሰው ገደሉ። 15  ከዚያም በእርሻው ውስጥ በሰፈረው ሠራዊትና በጦር ሰፈሩ ውስጥ በነበረው ሕዝብ ሁሉ መካከል ሽብር ተነዛ፤ ሌላው ቀርቶ ወራሪ ቡድኖቹ+ እንኳ ተሸበሩ። ምድሪቱም መንቀጥቀጥ ጀመረች፤ ከአምላክ የመጣ ሽብርም ወረደባቸው። 16  በቢንያም ግዛት በምትገኘው በጊብዓ+ የነበሩት የሳኦል ጠባቂዎችም በየአቅጣጫው ሁከት መሰራጨቱን አዩ።+ 17  ሳኦልም አብረውት የነበሩትን ሰዎች “እስቲ ሕዝቡን ቁጠሩና ትቶን የሄደው ማን እንደሆነ እወቁ” አላቸው። እነሱም ሲቆጥሩ ዮናታንና ጋሻ ጃግሬው እዚያ እንዳልነበሩ ተረዱ። 18  ሳኦልም አኪያህን+ “የእውነተኛውን አምላክ ታቦት ወደዚህ አምጣ!” አለው። (በዚያ ጊዜ* የእውነተኛው አምላክ ታቦት በእስራኤላውያን ዘንድ ነበር።) 19  ሳኦል ካህኑን እያነጋገረ ሳለ በፍልስጤማውያን ሰፈር የነበረው ትርምስ ይበልጥ እየጨመረ ሄደ። ከዚያም ሳኦል ካህኑን “እያደረግክ ያለኸውን ነገር ተው”* አለው። 20  በመሆኑም ሳኦልና አብረውት የነበሩት ሰዎች በሙሉ ተሰባስበው ውጊያው ወደሚደረግበት ቦታ ሄዱ፤ እዚያ ሲደርሱም ፍልስጤማውያኑ እርስ በርሳቸው በሰይፍ ሲጨፋጨፉ አገኟቸው፤ ከፍተኛ ትርምስ ተፈጥሮ ነበር። 21  ቀደም ሲል ከፍልስጤማውያን ጋር ወግነው የነበሩትና አብረዋቸው ወደ ሰፈሩ የመጡት ዕብራውያንም በሳኦልና በዮናታን ሥር ከነበሩት እስራኤላውያን ጋር ተቀላቀሉ። 22  በተጨማሪም በኤፍሬም ተራራማ አካባቢ ተደብቀው+ የነበሩት የእስራኤል ሰዎች በሙሉ ፍልስጤማውያን እየሸሹ መሆኑን ሰሙ፤ እነሱም ከሌሎቹ ጋር በመተባበር ፍልስጤማውያንን ማሳደዱን ተያያዙት። 23  በዚህ መንገድ ይሖዋ በዚያ ቀን እስራኤልን አዳነ፤+ ውጊያውም እስከ ቤትአዌን+ ድረስ ዘለቀ። 24  ሆኖም ሳኦል “ጠላቶቼን ከመበቀሌ በፊት እስከ ማታ ድረስ እህል የሚቀምስ ሰው የተረገመ ይሁን!” በማለት ሕዝቡን አስምሎ ስለነበር በዚያ ዕለት የእስራኤል ሰዎች ተጨንቀው ዋሉ። በመሆኑም ከሕዝቡ መካከል አንድም ሰው እህል አልቀመሰም።+ 25  ሕዝቡም* ሁሉ ወደ ጫካው ገባ፤ መሬቱም ላይ ማር ነበር። 26  ሕዝቡም ወደ ጫካው ሲገባ ማሩ ሲንጠባጠብ አየ፤ ሆኖም ሁሉም መሐላውን ስለፈሩ እጁን ወደ አፉ ያነሳ አንድም ሰው አልነበረም። 27  ዮናታን ግን አባቱ ሕዝቡን ሲያስምል አልሰማም ነበር፤+ በመሆኑም በእጁ የነበረውን በትር ዘርግቶ ጫፉን የማር እንጀራው ውስጥ አጠቀሰ። ከዚያም እጁን ወደ አፉ ሲመልስ ዓይኑ በራ። 28  በዚህ ጊዜ ከሕዝቡ መካከል አንዱ “አባትህ እኮ ‘በዛሬው ዕለት እህል የሚቀምስ ሰው የተረገመ ይሁን!’+ በማለት ሕዝቡን በጥብቅ አስምሏል። ሕዝቡ በጣም የተዳከመው ለዚህ ነው” አለው። 29  ዮናታን ግን እንዲህ አለ፦ “አባቴ በምድሪቱ ላይ ከባድ ችግር አምጥቷል። እኔ ይህችን ማር በመቅመሴ ዓይኖቼ እንዴት እንደበሩ እስቲ ተመልከቱ። 30  ሕዝቡ ከጠላቶቻቸው ከወሰዱት ምርኮ ዛሬ በነፃነት በልተው ቢሆን ኖሮ ምንኛ የተሻለ ይሆን ነበር!+ የተገደሉት ፍልስጤማውያንም ቁጥር ከዚህ እጅግ በበለጠ ነበር።” 31  በዚያም ዕለት ፍልስጤማውያንን ከሚክማሽ አንስተው እስከ አይሎን+ ድረስ መቷቸው፤ ሕዝቡም በጣም ተዳከመ። 32  ስለሆነም ሕዝቡ ምርኮውን በመስገብገብ ተሻምቶ ወሰደ፤ በጎችን፣ ከብቶችንና ጥጆችን ወስደው መሬት ላይ አረዷቸው፤ ሥጋውንም ከነደሙ በሉት።+ 33  በመሆኑም ሳኦል “ይኸው ሕዝቡ ሥጋውን ከነደሙ በመብላት+ በይሖዋ ላይ ኃጢአት እየሠራ ነው” ተብሎ ተነገረው። እሱም በዚህ ጊዜ “እምነት እንደሌላችሁ የሚያሳይ ድርጊት ፈጽማችኋል። በሉ አሁኑኑ አንድ ትልቅ ድንጋይ አንከባላችሁ አምጡልኝ” አለ። 34  አክሎም እንዲህ አለ፦ “በሕዝቡ መሃል ተበታትናችሁ እንዲህ በሏቸው፦ ‘እያንዳንዳችሁ በሬያችሁንና በጋችሁን አምጡ፤ በዚህም ስፍራ አርዳችሁ ብሉ። ሥጋውን ከነደሙ በመብላት በይሖዋ ላይ ኃጢአት አትሥሩ።’”+ በመሆኑም በዚያ ምሽት እያንዳንዱ ሰው በሬውን አምጥቶ በዚያ ስፍራ አረደው። 35  ሳኦልም ለይሖዋ መሠዊያ ሠራ።+ ይህ መሠዊያ ሳኦል ለይሖዋ የሠራው የመጀመሪያ መሠዊያ ነው። 36  በኋላም ሳኦል “በሌሊት ፍልስጤማውያንን ተከታትለን በመውረድ እስኪነጋ ድረስ እንበዝብዛቸው። አንድም ሰው በሕይወት አናስተርፍም” አለ። በዚህ ጊዜ ሕዝቡ “መልካም መስሎ የታየህን ማንኛውንም ነገር አድርግ” አሉት። ከዚያም ካህኑ “እዚሁ ወደ እውነተኛው አምላክ እንቅረብ” አለ።+ 37  ሳኦልም “ፍልስጤማውያንን ተከትዬ ልውረድ?+ በእስራኤላውያን እጅ እንዲወድቁ ታደርጋለህ?” በማለት አምላክን ጠየቀ። አምላክ ግን በዚያ ዕለት አልመለሰለትም። 38  በመሆኑም ሳኦል እንዲህ አለ፦ “እናንተ የሕዝቡ አለቆች ሁሉ ወደዚህ ቅረቡ፤ በዛሬው ዕለት ምን ኃጢአት እንደተፈጸመ አጣሩ። 39  እስራኤልን ባዳነው ሕያው በሆነው በይሖዋ እምላለሁ ይህን ኃጢአት የሠራው ልጄ ዮናታን ሆኖ ቢገኝ እንኳ መሞት አለበት።” ሆኖም ከሕዝቡ መካከል መልስ የሰጠው አንድም ሰው አልነበረም። 40  ከዚያም እስራኤላውያንን በሙሉ “እናንተ በአንድ በኩል ትሆናላችሁ፤ እኔና ልጄ ዮናታን ደግሞ በሌላኛው በኩል እንሆናለን” አላቸው። በዚህ ጊዜ ሕዝቡ ሳኦልን “መልካም መስሎ የታየህን ማንኛውንም ነገር አድርግ” አለው። 41  ሳኦልም ይሖዋን “የእስራኤል አምላክ ሆይ፣ በቱሚም+ አማካኝነት መልስ ስጠን!” አለው። ከዚያም ዮናታንና ሳኦል ተመረጡ፤ ሕዝቡም ነፃ ሆነ። 42  በዚህ ጊዜ ሳኦል “ከእኔና ከልጄ ከዮናታን ማን እንደሆነ ለመለየት ዕጣ ጣሉ”+ አለ። ዕጣውም በዮናታን ላይ ወጣ። 43  ሳኦልም ዮናታንን “ንገረኝ፣ ያደረግከው ነገር ምንድን ነው?” አለው። በመሆኑም ዮናታን “በእጄ ይዤው በነበረው በትር ጫፍ ትንሽ ማር ቀምሻለሁ።+ እንግዲህ ይኸው ለመሞት ዝግጁ ነኝ!” በማለት መለሰለት። 44  በዚህ ጊዜ ሳኦል “ዮናታን፣ እንደው አንተ ካልሞትክ አምላክ ይፍረድብኝ፤ የከፋም ነገር ያድርግብኝ” አለ።+ 45  ሕዝቡ ግን ሳኦልን እንዲህ አለው፦ “ለእስራኤል ይህን ታላቅ ድል*+ ያስገኘው ዮናታን መሞት ይገባዋል? ይሄማ ፈጽሞ የማይሆን ነገር ነው! ሕያው በሆነው በይሖዋ እንምላለን፣ ከራስ ፀጉሩ አንዷ እንኳ መሬት ላይ አትወድቅም፤ ምክንያቱም በዚህ ዕለት ይህን ያደረገው ከአምላክ ጋር ሆኖ ነው።”+ በዚህ መንገድ ሕዝቡ ዮናታንን ታደገው፤* እሱም ከሞት ዳነ። 46  ሳኦልም ፍልስጤማውያንን ማሳደዱን ተወ፤ ፍልስጤማውያንም ወደ ክልላቸው ሄዱ። 47  ሳኦልም በእስራኤል ላይ ንግሥናውን አጸና፤ በዙሪያው ከነበሩት ጠላቶቹ ማለትም ከሞዓባውያን፣+ ከአሞናውያን፣+ ከኤዶማውያን፣+ ከጾባህ+ ነገሥታትና ከፍልስጤማውያን+ ጋር ተዋጋ፤ በሄደበትም ሁሉ ድል ያደርጋቸው ነበር። 48  እንዲሁም በጀግንነት በመዋጋት አማሌቃውያንን+ ድል አደረገ፤ እስራኤላውያንንም ከዘራፊዎቻቸው እጅ አዳነ። 49  የሳኦል ወንዶች ልጆች ዮናታን፣ ይሽዊ እና ሜልኪሳ+ ነበሩ። እሱም ሁለት ሴቶች ልጆች የነበሩት ሲሆን የትልቋ ስም ሜሮብ፣+ የትንሿ ደግሞ ሜልኮል+ ነበር። 50  የሳኦል ሚስት የአኪማዓስ ልጅ አኪኖዓም ነበረች። የሠራዊቱ አዛዥ ደግሞ አበኔር+ ሲሆን እሱም የሳኦል አጎት የኔር ልጅ ነበር። 51  የሳኦል አባት ቂስ+ ነበር፤ የአበኔር አባት ኔር+ ደግሞ የአቢዔል ልጅ ነበር። 52  በሳኦል ዘመን ሁሉ ከፍልስጤማውያን ጋር ከባድ ውጊያ ይደረግ ነበር።+ ሳኦልም ብርቱ ወይም ደፋር ሰው ሲያገኝ ወደ ሠራዊቱ እንዲቀላቀል ይመለምለው ነበር።+

የግርጌ ማስታወሻ

ቃል በቃል “በዚያን ቀን።”
ቃል በቃል “እጅህን ሰብስብ።”
ቃል በቃል “ምድሩም።”
ቃል በቃል “ተቤዠው።”
ወይም “መዳን።”