አንደኛ ሳሙኤል 16:1-23

  • ሳሙኤል ዳዊትን ንጉሥ እንዲሆን ቀባው (1-13)

    • ‘ይሖዋ የሚያየው ልብን ነው’ (7)

  • የአምላክ መንፈስ ከሳኦል ተወሰደ (14-17)

  • ዳዊት ለሳኦል በገና ይጫወትለት ጀመር (18-23)

16  ከጊዜ በኋላ ይሖዋ ሳሙኤልን እንዲህ አለው፦ “ሳኦል በእስራኤል ላይ ንጉሥ እንዲሆን አልፈለግኩም፤+ ታዲያ አንተ ለእሱ የምታዝነው እስከ መቼ ነው?+ በል ቀንድህን ዘይት ሙላና+ ሂድ። የቤተልሔም ሰው ወደሆነው ወደ እሴይ+ እልክሃለሁ፤ ምክንያቱም ከወንዶች ልጆቹ መካከል ንጉሥ የሚሆንልኝ ሰው መርጫለሁ።”+  ሳሙኤል ግን “እንዴት መሄድ እችላለሁ? ሳኦል ይህን ከሰማ ይገድለኛል”+ አለ። ይሖዋም እንዲህ አለው፦ “አንዲት ጊደር ይዘህ ሂድ፤ ከዚያም ‘የመጣሁት ለይሖዋ መሥዋዕት ለማቅረብ ነው’ በል።  እሴይንም ወደ መሥዋዕቱ ጥራው፤ እኔም ምን ማድረግ እንዳለብህ አሳውቅሃለሁ። አንተም እኔ የምመርጥልህን ሰው ትቀባልኛለህ።”+  ሳሙኤልም ይሖዋ የነገረውን አደረገ። ቤተልሔም+ እንደደረሰም የከተማዋ ሽማግሌዎች ባገኙት ጊዜ እየተንቀጠቀጡ “የመጣኸው በሰላም ነው?” አሉት።  እሱም “አዎ በሰላም ነው። የመጣሁት ለይሖዋ መሥዋዕት ለማቅረብ ነው። ራሳችሁን ቀድሱ፤ ወደ መሥዋዕቱም አብራችሁኝ ሂዱ” አላቸው። ከዚያም እሴይንና ልጆቹን ቀደሳቸው፤ ወደ መሥዋዕቱ እንዲመጡም ጠራቸው።  እነሱም እዚያ በደረሱ ጊዜ ሳሙኤል ኤልያብን+ ሲያየው “መቼም ይሖዋ የሚቀባው ሰው ይህ መሆን አለበት” አለ።  ሆኖም ይሖዋ ሳሙኤልን እንዲህ አለው፦ “እኔ ስላልተቀበልኩት መልኩንና የቁመቱን ርዝማኔ አትይ።+ አምላክ የሚያየው ሰው በሚያይበት መንገድ አይደለም፤ ምክንያቱም ሰው የሚያየው ውጫዊ ገጽታን ነው፤ ይሖዋ ግን የሚያየው ልብን ነው።”+  ከዚያም እሴይ አቢናዳብን+ ጠርቶ በሳሙኤል ፊት እንዲያልፍ አደረገ፤ እሱ ግን “ይሄኛውንም ይሖዋ አልመረጠውም” አለ።  ቀጥሎም እሴይ ሻማህ+ እንዲቀርብ አደረገ፤ እሱ ግን “ይሄኛውንም ይሖዋ አልመረጠውም” አለ። 10  በመሆኑም እሴይ ሰባቱም ወንዶች ልጆቹ በሳሙኤል ፊት እንዲያልፉ አደረገ፤ ሳሙኤል ግን እሴይን “ይሖዋ ከእነዚህ መካከል ማናቸውንም አልመረጠም” አለው። 11  በመጨረሻም ሳሙኤል እሴይን “ወንዶች ልጆችህ እነዚሁ ብቻ ናቸው?” አለው። እሱም “ታናሽየው+ ገና ይቀራል፤ በጎች እየጠበቀ ነው” አለ።+ ከዚያም ሳሙኤል እሴይን “በል ልከህ አስመጣው፤ ምክንያቱም እሱ ሳይመጣ ምግብ ለመብላት መቀመጥ አንችልም” አለው። 12  በመሆኑም ልኮ አስመጣው። እሱም የቀይ ዳማ፣ ዓይኑ የሚያምርና መልከ መልካም ነበር።+ ከዚያም ይሖዋ “ተነስ፣ ቀባው፤ የመረጥኩት እሱን ነው!” አለው።+ 13  ስለዚህ ሳሙኤል የዘይቱን ቀንድ+ ወስዶ በወንድሞቹ ፊት ቀባው። ከዚያም ቀን አንስቶ የይሖዋ መንፈስ ለዳዊት ኃይል ሰጠው።+ በኋላም ሳሙኤል ተነስቶ ወደ ራማ+ ሄደ። 14  በዚህ ጊዜ የይሖዋ መንፈስ ከሳኦል ራቀ፤+ ከይሖዋ የመጣ መጥፎ መንፈስም ይረብሸው ጀመር።+ 15  የሳኦል አገልጋዮችም እንዲህ አሉት፦ “እንግዲህ ከአምላክ የመጣ መጥፎ መንፈስ እየረበሸህ ነው። 16  ጌታችን በፊቱ የቆሙትን አገልጋዮቹን በገና የሚደረድር ጥሩ ችሎታ ያለው ሰው እንዲፈልጉ ይዘዝ።+ ከአምላክ የመጣው መጥፎ መንፈስ በአንተ ላይ ሲወርድ ይህ ሰው በገና ይጫወትልሃል፤ አንተም ደህና ትሆናለህ።” 17  ስለዚህ ሳኦል አገልጋዮቹን “እንግዲያው እባካችሁ ጥሩ አድርጎ በገና የሚደረድር ሰው ፈልጋችሁ አምጡልኝ” አላቸው። 18  ከአገልጋዮቹም አንዱ እንዲህ አለ፦ “የቤተልሔሙ ሰው የእሴይ ልጅ በገና የመደርደር ጥሩ ችሎታ እንዳለው አይቻለሁ፤ እሱም ደፋርና ኃያል ተዋጊ ነው።+ ደግሞም አንደበተ ርቱዕና መልከ መልካም+ ሲሆን ይሖዋም ከእሱ ጋር ነው።”+ 19  ከዚያም ሳኦል ወደ እሴይ መልእክተኞችን ልኮ “በጎች የሚጠብቀውን ልጅህን ዳዊትን ላክልኝ” አለው።+ 20  በመሆኑም እሴይ ዳቦና በወይን ጠጅ የተሞላ አቁማዳ በአህያ አስጭኖ እንዲሁም የፍየል ግልገል አስይዞ ልጁን ዳዊትን ወደ ሳኦል ላከው። 21  በዚህ መንገድ ዳዊት ወደ ሳኦል መጣ፤ እሱንም ያገለግለው ጀመር።+ ሳኦልም እጅግ እየወደደው ሄደ፤ ጋሻ ጃግሬውም ሆነ። 22  ሳኦልም “ዳዊት በፊቴ ሞገስ ስላገኘ እባክህ እዚሁ እኔ ጋ ሆኖ እንዲያገለግለኝ ፍቀድልኝ” በማለት ወደ እሴይ መልእክት ላከ። 23  ከአምላክ የሚመጣ መጥፎ መንፈስ በሳኦል ላይ በሚወርድበት ጊዜ ሁሉ ዳዊት በገናውን አንስቶ ይደረድር ነበር፤ ሳኦልም ቀለል ይለውና ደህና ይሆን ነበር፤ መጥፎው መንፈስም ከእሱ ይርቅ ነበር።+

የግርጌ ማስታወሻ