አንደኛ ሳሙኤል 18:1-30

  • የዳዊትና የዮናታን ወዳጅነት (1-4)

  • ሳኦል፣ ዳዊት ባገኘው ድል ቀና (5-9)

  • ሳኦል ዳዊትን ሊገድለው ሞከረ (10-19)

  • ዳዊት የሳኦልን ልጅ ሜልኮልን አገባ (20-30)

18  ዳዊት ከሳኦል ጋር ተነጋግሮ እንደጨረሰ ዮናታንና+ ዳዊት የጠበቀ ወዳጅነት መሠረቱ፤* ዮናታንም እንደ ራሱ* ወደደው።+  ከዚያን ቀን ጀምሮ ሳኦል ዳዊት ከእሱ ጋር እንዲኖር አደረገ፤ ወደ አባቱም ቤት እንዲመለስ አልፈቀደለትም።+  ዮናታንም ዳዊትን እንደ ራሱ* ስለወደደው+ ከዳዊት ጋር ቃል ኪዳን ተጋቡ።+  ከዚያም ዮናታን ለብሶት የነበረውን መደረቢያ አውልቆ ለዳዊት ሰጠው፤ እንዲሁም ልብሶቹን ሌላው ቀርቶ ሰይፉን፣ ቀስቱንና ቀበቶውን ሰጠው።  ዳዊትም ለውጊያ ይወጣ ጀመር፤ ሳኦል በሚልከው በማንኛውም ቦታ ተልእኮውን በተሳካ ሁኔታ* ይፈጽም ነበር።+ በመሆኑም ሳኦል በሠራዊቱ ላይ ሾመው፤+ ይህም ሕዝቡንና የሳኦልን አገልጋዮች በሙሉ አስደሰታቸው።  ዳዊትና አብረውት ያሉት ሰዎች ፍልስጤማውያንን መትተው በተመለሱ ጊዜ በመላው የእስራኤል ከተሞች የሚገኙ ሴቶች አታሞና+ ባለ ሦስት አውታር መሣሪያ ይዘው በደስታ እየዘፈኑና+ እየጨፈሩ ንጉሥ ሳኦልን ለመቀበል ወጡ።  እየጨፈሩ የነበሩት ሴቶችም እንዲህ እያሉ ዘፈኑ፦ “ሳኦል ሺዎችን ገደለ፤ዳዊት ደግሞ አሥር ሺዎችን ገደለ።”+  ሳኦልም እጅግ ተቆጣ፤+ ዘፈኑም አላስደሰተውም፤ በመሆኑም “ለዳዊት አሥር ሺህ አሉለት፤ ለእኔ ግን ሺህ ብቻ፤ ያልተሰጠው ነገር እኮ መንግሥት ብቻ ነው!” አለ።+  ከዚያች ዕለት አንስቶ ሳኦል ዳዊትን በጥርጣሬ ዓይን ይመለከተው ጀመር። 10  በማግስቱም ከአምላክ የመጣ መጥፎ መንፈስ ሳኦልን ያዘው፤+ ዳዊት በፊት እንደሚያደርገው ሁሉ በገና እየደረደረ+ ሳለ ሳኦል ቤቱ ውስጥ እንግዳ ባሕርይ ያሳይ* ጀመር። ሳኦልም በእጁ ጦር ይዞ ነበር፤+ 11  እሱም ‘ዳዊትን ከግድግዳው ጋር አጣብቀዋለሁ!’ ብሎ በማሰብ ጦሩን በኃይል ወረወረው።+ ዳዊት ግን ሁለት ጊዜ ከእሱ አመለጠ። 12  ይሖዋ ከሳኦል ተለይቶ+ ከዳዊት ጋር ስለነበር+ ሳኦል ዳዊትን ፈራው። 13  በመሆኑም ሳኦል ከፊቱ እንዲርቅ አደረገው፤ የሺህ አለቃ አድርጎም ሾመው፤ ዳዊትም ሠራዊቱን እየመራ ወደ ጦርነት ይሄድ ነበር።*+ 14  ዳዊት የሚያከናውነው ነገር ሁሉ ይሳካለት ነበር፤*+ ይሖዋም ከእሱ ጋር ነበር።+ 15  ሳኦልም ዳዊት ስኬታማ እንደሆነ ሲያይ ፈራው። 16  መላው እስራኤልና ይሁዳ ግን ዳዊትን ወደዱት፤ ምክንያቱም ወደ ጦርነት ሲወጡ የሚመራቸው እሱ ነበር። 17  በኋላም ሳኦል ዳዊትን እንዲህ አለው፦ “እንግዲህ ትልቋ ልጄ ሜሮብ+ አለች። እሷን እድርልሃለሁ።+ ሆኖም ጀግንነትህን ለእኔ ከማሳየት ወደኋላ ማለት የለብህም፤ የይሖዋንም ጦርነቶች መዋጋት ይኖርብሃል።”+ ሳኦል ይህን ያለው ‘እጄን በዚህ ሰው ላይ አላሳርፍም። ከዚህ ይልቅ በፍልስጤማውያን እጅ ይሙት’ ብሎ ስላሰበ ነው።+ 18  በዚህ ጊዜ ዳዊት ሳኦልን “ለንጉሡ አማች እሆን ዘንድ እኔም ሆንኩ የአባቴ ቤተሰቦች የሆኑት ዘመዶቼ በእስራኤል ውስጥ ከቶ ማን ሆነን ነው?” አለው።+ 19  ሆኖም የሳኦል ልጅ ሜሮብ ለዳዊት ልትሰጥ የነበረበት ጊዜ ሲደርስ እሷ ቀድሞውኑ ለመሆላታዊው ለአድሪዔል+ ተድራ ነበር። 20  የሳኦል ልጅ ሜልኮል+ ዳዊትን ትወደው ነበር፤ ይህን ለሳኦል ነገሩት፤ እሱም ነገሩ ደስ አሰኘው። 21  በመሆኑም ሳኦል “ወጥመድ እንድትሆነውና የፍልስጤማውያን እጅ በእሱ ላይ እንዲሆን እሷን እሰጠዋለሁ” አለ።+ ከዚያም ሳኦል ለሁለተኛ ጊዜ ዳዊትን “በዛሬዋ ዕለት በዚህች በሁለተኛዋ ሴት አማካኝነት ከእኔ ጋር በጋብቻ ትዛመዳለህ”* አለው። 22  በተጨማሪም ሳኦል አገልጋዮቹን እንዲህ ሲል አዘዛቸው፦ “ለዳዊት እንዲህ ብላችሁ በሚስጥር ንገሩት፦ ‘ንጉሡ በአንተ ደስ ብሎታል፤ አገልጋዮቹም በሙሉ ይወዱሃል። ስለሆነም አሁን ከንጉሡ ጋር በጋብቻ ተዛመድ።’” 23  የሳኦልም አገልጋዮች ይህን በነገሩት ጊዜ ዳዊት “እዚህ ግባ ለማልባል ለእንደኔ ዓይነቱ ድሃ ከንጉሡ ጋር በጋብቻ መዛመድ እንዲህ ቀላል ነገር ይመስላችኋል?” አላቸው።+ 24  ከዚያም የሳኦል አገልጋዮች “ዳዊት እኮ እንዲህ እንዲህ አለ” ብለው ነገሩት። 25  በዚህ ጊዜ ሳኦል እንዲህ አለ፦ “ዳዊትን እንዲህ በሉት፦ ‘ንጉሡ ከአንተ የሚፈልገው ጥሎሽ+ ሳይሆን ጠላቶቹን መበቀል እንዲችል የ100 ፍልስጤማውያንን ሸለፈት+ ብቻ ነው።’” ሳኦል ይህን ያለው ዳዊት በፍልስጤማውያን እጅ እንዲወድቅ ተንኮል አስቦ ስለነበር ነው። 26  በመሆኑም አገልጋዮቹ ይህንኑ ለዳዊት ነገሩት፤ ዳዊትም ከንጉሡ ጋር በጋብቻ የመዛመዱ ጉዳይ አስደሰተው።+ ስለሆነም የተሰጠው ጊዜ ከማብቃቱ በፊት 27  ዳዊት አብረውት ከነበሩት ሰዎች ጋር በመሄድ 200 ፍልስጤማውያንን መታ፤ ዳዊት ከንጉሡ ጋር በጋብቻ ለመዛመድ የገደላቸውን ሰዎች ሸለፈት በሙሉ አምጥቶ ለንጉሡ ሰጠው። በመሆኑም ሳኦል ልጁን ሜልኮልን ዳረለት።+ 28  ሳኦል ይሖዋ ከዳዊት ጋር እንደነበርና+ ልጁ ሜልኮልም ዳዊትን እንደወደደችው+ ተረዳ። 29  በዚህም ምክንያት ሳኦል ዳዊትን ከበፊቱ ይልቅ ፈራው፤ በመሆኑም ዕድሜውን ሙሉ የዳዊት ጠላት ሆነ።+ 30  የፍልስጤም መኳንንትም ለውጊያ ይወጡ ነበር፤ ሆኖም ለውጊያ በወጡ ቁጥር ዳዊት ከሳኦል አገልጋዮች ሁሉ ይበልጥ ይሳካለት ነበር፤*+ ስሙም እየገነነ መጣ።+

የግርጌ ማስታወሻ

ወይም “እንደ ገዛ ነፍሱ።”
ወይም “የዮናታን ነፍስ ከዳዊት ነፍስ ጋር ተቆራኘች።”
ወይም “እንደ ገዛ ነፍሱ።”
ወይም “ተልእኮውን በጥበብ።”
ወይም “እንደ ነቢይ ያደርገው።”
ቃል በቃል “በሕዝቡ ፊት ይወጣና ይገባ ነበር።”
ወይም “የሚያከናውነውን ነገር ሁሉ በጥበብ ያደርግ ነበር።”
ወይም “አማቼ ትሆናለህ።”
ወይም “በጥበብ ይመላለስ ነበር።”