አንደኛ ሳሙኤል 19:1-24

  • ሳኦል ዳዊትን ይበልጥ ጠላው (1-13)

  • ዳዊት ከሳኦል አመለጠ (14-24)

19  በኋላም ሳኦል፣ ዳዊት እንዲገደል ማሰቡን ለልጁ ለዮናታንና ለአገልጋዮቹ በሙሉ ነገራቸው።+  የሳኦል ልጅ ዮናታን ዳዊትን በጣም ይወደው+ ስለነበር ዳዊትን እንዲህ አለው፦ “አባቴ ሳኦል ሊገድልህ ይፈልጋል። ስለዚህ እባክህ ጠዋት ላይ ተጠንቀቅ፤ ወደ አንድ ሰዋራ ቦታም ሄደህ ተሸሽገህ ቆይ።  እኔም እወጣና አንተ ባለህበት ሜዳ ከአባቴ አጠገብ እቆማለሁ። ከእሱም ጋር ስለ አንተ እነጋገራለሁ፤ የሆነ ነገር እንዳለ ከተረዳሁ እነግርሃለሁ።”+  በመሆኑም ዮናታን ለአባቱ ለሳኦል ስለ ዳዊት መልካም ነገር ነገረው።+ እንዲህም አለው፦ “ንጉሡ በአገልጋዩ በዳዊት ላይ ኃጢአት አይሥራ፤ ምክንያቱም እሱ በአንተ ላይ የሠራው ኃጢአት የለም፤ ያደረገልህም ነገር ቢሆን ለአንተ የሚበጅ ነው።  ሕይወቱን አደጋ ላይ ጥሎ* ፍልስጤማዊውን መታ፤+ ይሖዋም ለመላው እስራኤል ታላቅ ድል አጎናጸፈ።* አንተም ይህን አይተህ በጣም ተደስተህ ነበር። ታዲያ ያለምንም ምክንያት ዳዊትን በመግደል በንጹሕ ሰው ደም ላይ ለምን ኃጢአት ትሠራለህ?”+  ሳኦልም የዮናታንን ቃል ሰማ፤ እሱም “ሕያው በሆነው በይሖዋ እምላለሁ፣ ዳዊት አይገደልም” ሲል ማለ።  ከዚያም ዮናታን ዳዊትን ጠርቶ ሁሉንም ነገር ነገረው። ስለዚህ ዮናታን ዳዊትን ወደ ሳኦል አመጣው፤ እሱም እንደቀድሞው ሳኦልን ማገልገሉን ቀጠለ።+  ከጊዜ በኋላ ሌላ ጦርነት ተነሳ፤ ዳዊትም ወጥቶ ከፍልስጤማውያን ጋር ተዋጋ፤ ክፉኛም ጨፈጨፋቸው፤ እነሱም ከፊቱ ሸሹ።  ሳኦል ጦሩን ይዞ ቤቱ ውስጥ ተቀምጦ ሳለ ከይሖዋ የመጣ መጥፎ መንፈስ ወረደበት፤+ በዚህ ጊዜ ዳዊት በገና እየደረደረ ነበር።+ 10  ሳኦልም ዳዊትን በጦሩ ከግድግዳው ጋር ሊያጣብቀው ሞከረ፤ ዳዊት ግን ከሳኦል ፊት ዞር በማለቱ ጦሩ ግድግዳው ላይ ተሰካ። ዳዊትም በዚያ ሌሊት ሸሽቶ አመለጠ። 11  በኋላም ሳኦል የዳዊትን ቤት ከበው በንቃት በመጠባበቅ ጠዋት ላይ እንዲገድሉት መልእክተኞችን ላከ፤+ ሆኖም የዳዊት ሚስት ሜልኮል “ዛሬ ሌሊት ካላመለጥክ* ነገ ትገደላለህ” አለችው። 12  ሜልኮልም ዳዊት ሸሽቶ እንዲያመልጥ ወዲያውኑ በመስኮት አሾልካ አወረደችው። 13  ከዚያም የተራፊም ቅርጹን* ወስዳ አልጋው ላይ አጋደመች፤ በራስጌውም ከፍየል ፀጉር የተሠራ እንደ መረብ ያለ ጨርቅ አደረገች፤ በልብስም ሸፈነችው። 14  ሳኦልም ዳዊትን እንዲይዙት መልእክተኞችን ላከ፤ እሷ ግን “አሞታል” አለቻቸው። 15  በመሆኑም ሳኦል ዳዊትን እንዲያዩት መልእክተኞቹን ላከ፤ እነሱንም “ዳዊትን እንድገድለው በአልጋው ላይ እንዳለ አምጡልኝ” አላቸው።+ 16  መልእክተኞቹም ሲገቡ አልጋው ላይ ያገኙት የተራፊም ቅርጹን* ነበር፤ በራስጌውም ከፍየል ፀጉር የተሠራ እንደ መረብ ያለ ጨርቅ ነበር። 17  ሳኦልም ሜልኮልን “እንዲህ ያታለልሽኝና ጠላቴ+ ሸሽቶ እንዲያመልጥ ያደረግሽው ለምንድን ነው?” አላት። ሜልኮልም “‘እንዳመልጥ እርጂኝ፣ አለዚያ እገድልሻለሁ!’ አለኝ” አለችው። 18  ዳዊትም ሸሽቶ አመለጠ፤ በራማ+ ወደሚገኘው ወደ ሳሙኤልም መጣ። ሳኦል ያደረገበትንም ነገር ሁሉ ነገረው። ከዚያም እሱና ሳሙኤል ሄደው በናዮት+ መኖር ጀመሩ። 19  ከጊዜ በኋላም ሳኦል “ዳዊት እኮ ያለው በራማ በምትገኘው በናዮት ነው!” የሚል ወሬ ደረሰው። 20  ሳኦልም ዳዊትን እንዲይዙት ወዲያውኑ መልእክተኞችን ላከ። የሳኦል መልእክተኞችም አረጋውያን የሆኑት ነቢያት ትንቢት ሲናገሩ፣ ሳሙኤል ደግሞ እንደ መሪያቸው ሆኖ ቆሞ ሲያዩ የአምላክ መንፈስ ወረደባቸው፤ እነሱም እንደ ነቢያት ያደርጋቸው ጀመር። 21  ይህን ለሳኦል በነገሩት ጊዜ ወዲያውኑ ሌሎች መልእክተኞችን ላከ፤ እነሱም እንደ ነቢያት ያደርጋቸው ጀመር። በመሆኑም ሳኦል ለሦስተኛ ጊዜ መልእክተኞችን ላከ፤ እነሱም እንደ ነቢያት ያደርጋቸው ጀመር። 22  በመጨረሻም እሱ ራሱ ወደ ራማ ሄደ። በሰኩ ወደሚገኘው ትልቅ የውኃ ማጠራቀሚያ ጉድጓድ እንደደረሰም “ለመሆኑ ሳሙኤልና ዳዊት የት ናቸው?” ሲል ጠየቀ። እነሱም “በራማ ባለችው በናዮት+ ይገኛሉ” ብለው መለሱለት። 23  ሳኦልም በራማ ወደምትገኘው ወደ ናዮት እየሄደ ሳለ የአምላክ መንፈስ በእሱም ላይ ወረደበት፤ እሱም በራማ ወደምትገኘው ወደ ናዮት እስኪደርስ ድረስ እንደ ነቢይ አደረገው። 24  ልብሱንም አወለቀ፤ በሳሙኤልም ፊት እንደ ነቢይ አደረገው፤ ቀኑንና ሌሊቱን ሙሉ ራቁቱን* ሆኖ በዚያ ተጋደመ። እነሱም “ሳኦልም ከነቢያቱ አንዱ ነው እንዴ?”+ ያሉት በዚህ የተነሳ ነው።

የግርጌ ማስታወሻ

ወይም “ነፍሱን በእጁ ይዞ።”
ወይም “መዳን አስገኘ።”
ወይም “ነፍስህ እንድታመልጥ ካላደረግክ።”
ወይም “የቤት ውስጥ አምላኩን፤ ጣዖቱን።”
ወይም “የቤት ውስጥ አምላኩን፤ ጣዖቱን።”
ወይም “ከውስጥ በለበሰው ልብስ ብቻ።”