አንደኛ ሳሙኤል 21:1-15

  • ዳዊት ከገጸ ኅብስቱ በላ (1-9)

  • ዳዊት አእምሮው እንደተነካ ሰው ሆነ (10-15)

21  በኋላም ዳዊት ካህኑ አሂሜሌክ ወደሚገኝበት ወደ ኖብ+ መጣ። አሂሜሌክም ዳዊትን ሲያገኘው ተንቀጠቀጠ፤ እሱም “ምነው ብቻህን? ሰው አብሮህ የለም?” አለው።+  ዳዊትም ለካህኑ ለአሂሜሌክ እንዲህ ሲል መለሰለት፦ “ንጉሡ አንድ ጉዳይ እንዳስፈጽም አዞኝ ነበር፤ ሆኖም ‘ስለሰጠሁህ ተልእኮና ስላዘዝኩህ ነገር ማንም ሰው ምንም ነገር እንዳያውቅ’ ብሎኛል። ከሰዎቼም ጋር የሆነ ቦታ ላይ ለመገናኘት ተቀጣጥረናል።  ስለዚህ አሁን እጅህ ላይ አምስት ዳቦ ካለ ወይም የተገኘውን ማንኛውንም ነገር ስጠኝ።”  ካህኑ ግን ዳዊትን እንዲህ አለው፦ “ማንኛውም ሰው የሚበላው ዓይነት ዳቦ የለኝም፤ ሰሞኑን ሰዎቹ ራሳቸውን ከሴት ጠብቀው*+ ከሆነ ግን የተቀደሰው ኅብስት አለ።”+  ስለዚህ ዳዊት ካህኑን እንዲህ አለው፦ “ከዚህ በፊት ለውጊያ እንደወጣሁባቸው ጊዜያት ሁሉ አሁንም ፈጽሞ ሴቶች ወደ እኛ አልቀረቡም።+ ተራ በሆነ ተልእኮም እንኳ የሰዎቹ አካል ቅዱስ ከነበረ ታዲያ ዛሬማ እንዴት ይበልጥ ቅዱስ አይሆን!”  በመሆኑም ካህኑ የተቀደሰውን ኅብስት ሰጠው፤+ ምክንያቱም ትኩስ ኅብስት በሚተካበት ቀን ከይሖዋ ፊት ከተነሳው ገጸ ኅብስት በስተቀር ሌላ ዳቦ አልነበረም።  ከሳኦል አገልጋዮች አንዱ በይሖዋ ፊት እንዲቆይ በመገደዱ ያን ቀን እዚያ ነበር። ዶይቅ+ የተባለው ይህ ኤዶማዊ+ የሳኦል እረኞች አለቃ ነበር።  ከዚያም ዳዊት አሂሜሌክን “ንጉሡ የሰጠኝ ተልእኮ አስቸኳይ ስለነበር ሰይፌንም ሆነ የጦር መሣሪያዎቼን አልያዝኩም፤ እዚህ አንተ ጋ ጦር ወይም ሰይፍ ይኖራል?” አለው።  ካህኑም “በኤላህ ሸለቆ*+ አንተ የገደልከው የፍልስጤማዊው የጎልያድ ሰይፍ+ አለ፤ ያውልህ ከኤፉዱ+ ኋላ በጨርቅ ተጠቅልሎ ተቀምጧል። ከእሱ ሌላ እዚህ ምንም ስለሌለ ከፈለግክ እሱን ውሰደው” አለው። ዳዊትም “ከእሱ የተሻለማ የትም አይገኝም። እሱኑ ስጠኝ” አለው። 10  በዚያም ቀን ዳዊት ተነስቶ ከሳኦል ሸሸ፤+ ከጊዜ በኋላም ወደ ጌት+ ንጉሥ ወደ አንኩስ መጣ። 11  የአንኩስ አገልጋዮችም እንዲህ አሉት፦ “ይህ የምድሪቱ ንጉሥ፣ ዳዊት አይደለም?‘ሳኦል ሺዎችን ገደለ፤ዳዊት ደግሞ አሥር ሺዎችን ገደለ’+ በማለት እየዘፈኑ የጨፈሩለትስ ለዚህ ሰው አይደለም?” 12  ዳዊትም ይህን ቃል በቁም ነገር ተመለከተው፤ የጌትን ንጉሥ አንኩስንም እጅግ ፈራው።+ 13  በመሆኑም በፊታቸው አእምሮውን እንደሳተ ሰው ሆነ፤+ በመካከላቸውም* እንደአበደ ሰው አደረገው። የከተማዋን በሮች ይቦጫጭር እንዲሁም ለሃጩን በጢሙ ላይ ያዝረበርብ ጀመር። 14  አንኩስም አገልጋዮቹን እንዲህ አላቸው፦ “እስቲ ተመልከቱ፣ ሰውየው እኮ እብድ ነው! ታዲያ ወደ እኔ ያመጣችሁት ለምንድን ነው? 15  ይህን ሰው ፊቴ እንዲህ እንዲያብድ ያመጣችሁት እኔ እብድ አጥቼ ነው? ይህስ ሰው ቤቴ መግባት ይገባዋል?”

የግርጌ ማስታወሻ

ወይም “የፆታ ግንኙነት ከመፈጸም ተቆጥበው።”
ወይም “ረባዳማ ሜዳ።”
ቃል በቃል “እጃቸውም ላይ።”