አንደኛ ሳሙኤል 24:1-22

  • ዳዊት ሳኦልን ሳይገድለው ቀረ (1-22)

    • ዳዊት፣ ይሖዋ ለቀባው ንጉሥ አክብሮት እንዳለው አሳየ (6)

24  ሳኦል ፍልስጤማውያንን አሳዶ እንደተመለሰ “ዳዊት በኤንገዲ+ ምድረ በዳ ይገኛል” ብለው ነገሩት።  ስለዚህ ሳኦል ከመላው እስራኤል የተመረጡ 3,000 ሰዎችን ይዞ ዳዊትንና ሰዎቹን ለመፈለግ የተራራ ፍየሎች ወደሚገኙበት ዓለታማ ገደላ ገደል ሄደ።  ሳኦልም በመንገዱ ዳር ወዳለ ከድንጋይ የተሠራ የበጎች ጉረኖ ደረሰ፤ በዚያም አንድ ዋሻ ነበር፤ በመሆኑም ሳኦል ለመጸዳዳት* ወደ ዋሻው ገባ፤ በዚህ ጊዜ ዳዊትና ሰዎቹ በዋሻው+ ውስጠኛ ክፍል ተቀምጠው ነበር።  ከዚያም የዳዊት ሰዎች “ይሖዋ ‘ጠላትህን በእጅህ አሳልፌ እሰጥሃለሁ፤+ አንተም ደስ ያለህን ታደርግበታለህ’ ያለህ ቀን ይህ ነው” አሉት። ስለሆነም ዳዊት ተነሳ፤ የሳኦልንም ልብስ ጫፍ በቀስታ ቆርጦ ወሰደ።  በኋላ ላይ ግን ዳዊት የሳኦልን ልብስ ጫፍ በመቁረጡ ልቡ* ወቀሰው።+  አብረውት የነበሩትንም ሰዎች “ይሖዋ በቀባው በጌታዬ ላይ እጄን በማንሳት እንዲህ ያለውን ድርጊት መፈጸም በይሖዋ ዓይን ፈጽሞ የማይታሰብ ነገር ነው፤ ምክንያቱም እሱ ይሖዋ የቀባው ነው”+ አላቸው።  ስለዚህ ዳዊት ይህን በማለት ሰዎቹን ከለከላቸው፤* በሳኦል ላይ ጉዳት እንዲያደርሱበትም አልፈቀደላቸውም። ሳኦልም ተነስቶ ከዋሻው ወጥቶ ሄደ።  ከዚያም ዳዊት ከዋሻው በመውጣት “ጌታዬ ንጉሥ ሆይ!”+ በማለት ሳኦልን ጠራው። ሳኦልም ወደኋላው ዞር ብሎ ሲመለከት ዳዊት በግንባሩ መሬት ላይ ተደፍቶ ሰገደ።  ዳዊትም ሳኦልን እንዲህ አለው፦ “‘ዳዊት የአንተን ክፉ ማየት ይፈልጋል’ የሚሉትን ሰዎች ወሬ ለምን ትሰማለህ?+ 10  በዛሬዋ ዕለት በዋሻው ውስጥ ይሖዋ አንተን እንዴት አድርጎ በእጄ ሰጥቶኝ እንደነበር በገዛ ዓይንህ አይተሃል። አንድ ሰው እንድገድልህ ገፋፍቶኝ+ የነበረ ቢሆንም እኔ ግን ለአንተ በማዘን ‘ይሖዋ የቀባው+ ስለሆነ በጌታዬ ላይ እጄን አላነሳም’ አልኩ። 11  አሁንም አባቴ ሆይ፣ ተመልከት፣ በእጄ የያዝኩትን የልብስህን ቁራጭ እይ፤ የልብስህን ጫፍ በቆረጥኩ ጊዜ ልገድልህ እችል ነበር፤ ግን አልገደልኩህም። እንግዲህ አንተን ለመጉዳትም ሆነ በአንተ ላይ ለማመፅ ፈጽሞ እንዳላሰብኩ ከዚህ ማየትና መረዳት ትችላለህ፤ ምንም እንኳ ሕይወቴን* ለማጥፋት እያሳደድከኝ+ ቢሆንም እኔ በአንተ ላይ ምንም የፈጸምኩት በደል የለም።+ 12  ይሖዋ በእኔና በአንተ መካከል ይፍረድ፤+ ይሖዋ አንተን ይበቀልልኝ+ እንጂ እኔ በምንም ዓይነት እጄን በአንተ ላይ አላነሳም።+ 13  ‘ከክፉ ሰው ክፉ ነገር ይወጣል’ የሚል የጥንት አባባል አለ፤ እኔ ግን በምንም ዓይነት እጄን በአንተ ላይ አላነሳም። 14  ለመሆኑ የእስራኤል ንጉሥ የወጣው ማንን ፍለጋ ነው? የምታሳድደውስ ማንን ነው? አንድን የሞተ ውሻ? ወይስ አንዲትን ቁንጫ?+ 15  አሁንም ይሖዋ ዳኛ ሆኖ በእኔና በአንተ መካከል ይፍረድ፤ ጉዳዩንም ተመልክቶ ስለ እኔ ይሟገትልኝ፤+ እሱ ይፍረድልኝ፣ ከእጅህም ያድነኝ።” 16  ዳዊት ይህን ተናግሮ ሲጨርስ ሳኦል “ልጄ ዳዊት፣ ይህ የአንተ ድምፅ ነው?”+ አለው። ከዚያም ሳኦል ድምፁን ከፍ አድርጎ አለቀሰ። 17  ዳዊትንም እንዲህ አለው፦ “አንተ መልካም ስታደርግልኝ እኔ ግን ክፉ መለስኩልህ፤ ስለሆነም አንተ ከእኔ ይልቅ ጻድቅ ነህ።+ 18  አዎ፣ ይሖዋ እኔን በእጅህ አሳልፎ ቢሰጥህም ሳትገድለኝ በመቅረት ለእኔ ያደረግከውን መልካም ነገር ይኸው ዛሬ ነገርከኝ።+ 19  ለመሆኑ ጠላቱን አግኝቶ ጉዳት ሳያደርስበት የሚለቀው ሰው ይኖራል? ዛሬ አንተ ለእኔ መልካም ስላደረግክልኝ ይሖዋም ለአንተ መልካም በማድረግ ወሮታህን ይመልስልህ።+ 20  ደግሞም አንተ በእርግጥ ንጉሥ ሆነህ እንደምትገዛ አውቃለሁ፤+ የእስራኤልም መንግሥት በእጅህ ይጸናል። 21  በመሆኑም አሁን ከእኔ በኋላ የሚመጡትን ዘሮቼን እንደማታጠፋና ስሜንም ከአባቴ ቤት+ እንደማትደመስስ በይሖዋ ማልልኝ።”+ 22  ስለዚህ ዳዊት ለሳኦል ማለለት፤ ከዚያም ሳኦል ወደ ቤቱ ሄደ።+ ዳዊትና ሰዎቹ ግን ወደ ምሽጉ ወጡ።+

የግርጌ ማስታወሻ

ቃል በቃል “እግሩን ለመሸፈን።”
ወይም “ሕሊናው።”
“በተናቸው” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ወይም “ነፍሴን።”