አንደኛ ሳሙኤል 26:1-25
26 ከጊዜ በኋላ የዚፍ+ ሰዎች በጊብዓ+ ወደሚገኘው ወደ ሳኦል መጥተው “ዳዊት በየሺሞን*+ ፊት ለፊት በሚገኘው በሃኪላ ኮረብታ ተደብቆ የለም?” አሉት።
2 ስለሆነም ሳኦል ከእስራኤል የተመረጡ 3,000 ሰዎችን በማስከተል ዳዊትን በዚፍ ምድረ በዳ ለመፈለግ ወደዚያ ወረደ።+
3 ሳኦልም ከየሺሞን ፊት ለፊት በሚገኘው በሃኪላ ኮረብታ ላይ መንገድ ዳር ሰፈረ። በዚህ ጊዜ ዳዊት በምድረ በዳ ይኖር ነበር፤ ዳዊትም ሳኦል እሱን ለመፈለግ ወደ ምድረ በዳ እንደመጣ ሰማ።
4 በመሆኑም ሳኦል በእርግጥ መጥቶ እንደሆነ ለማወቅ ሰላዮችን ላከ።
5 በኋላም ዳዊት ሳኦል ወደሰፈረበት ቦታ ሄደ፤ ሳኦልና የሠራዊቱ አዛዥ የሆነው የኔር ልጅ አበኔር+ የተኙበትንም ቦታ አየ፤ ሳኦል በሰፈሩ መሃል ተኝቶ ነበር፤ ሠራዊቱም ዙሪያውን ሰፍሮ ነበር።
6 ከዚያም ዳዊት ሂታዊውን+ አሂሜሌክንና የኢዮዓብ ወንድም የሆነውን የጽሩያን+ ልጅ አቢሳን+ “ሳኦል ወደሰፈረበት ቦታ አብሮኝ የሚወርድ ማን ነው?” አላቸው። አቢሳም “እኔ አብሬህ እወርዳለሁ” አለ።
7 ስለዚህ ዳዊትና አቢሳ በሌሊት ሠራዊቱ ወዳለበት ሄዱ፤ ሳኦልም ጦሩን ራስጌው አጠገብ መሬት ላይ ሰክቶ በሰፈሩ መሃል ተኝቶ አገኙት፤ አበኔርና ሠራዊቱም በዙሪያው ተኝተው ነበር።
8 አቢሳም ዳዊትን “አምላክ ዛሬ ጠላትህን እጅህ ላይ ጥሎታል።+ እባክህ አሁን አንድ ጊዜ ብቻ በጦር ወግቼ ከመሬት ጋር ላጣብቀው፤ መድገም አያስፈልገኝም” አለው።
9 ሆኖም ዳዊት አቢሳን “ጉዳት እንዳታደርስበት፤ ለመሆኑ ይሖዋ በቀባው+ ላይ እጁን አንስቶ ከበደል ነፃ የሚሆን ማን ነው?”+ አለው።
10 ከዚያም ዳዊት እንዲህ አለው፦ “ሕያው በሆነው በይሖዋ እምላለሁ፣ ይሖዋ ራሱ ይቀስፈዋል፤+ ወይም ደግሞ እንደ ማንኛውም ሰው አንድ ቀን ይሞታል፤+ አሊያም ወደ ጦርነት ወርዶ እዚያ ይገደላል።+
11 በእኔ በኩል ይሖዋ በቀባው ላይ እጄን ማንሳት በይሖዋ ዓይን ፈጽሞ የማይታሰብ ነገር ነው!+ በል አሁን ራስጌው አጠገብ ያለውን ጦርና የውኃ መያዣውን አንሳና እንሂድ።”
12 በመሆኑም ዳዊት ጦሩንና የውኃ መያዣውን ከሳኦል ራስጌ ወሰደ፤ ከዚያም ሄዱ። ሁሉም ተኝተው ስለነበር ያያቸውም ሆነ ልብ ያላቸው ወይም ከእንቅልፉ የነቃ አንድም ሰው አልነበረም፤+ ምክንያቱም ይሖዋ ከባድ እንቅልፍ ጥሎባቸው ነበር።
13 ከዚያም ዳዊት ወደ ማዶ ተሻግሮ በተራራው ጫፍ ላይ ራቅ ብሎ ቆመ፤ በመካከላቸውም ያለው ርቀት ሰፊ ነበር።
14 ዳዊትም ወደ ሠራዊቱና ወደ ኔር ልጅ ወደ አበኔር+ ተጣርቶ “አበኔር፣ የማትመልስልኝ ለምንድን ነው?” አለ። አበኔርም “ንጉሡን የምትጣራው አንተ ማን ነህ?” ሲል መለሰለት።
15 ዳዊትም አበኔርን እንዲህ አለው፦ “አንተ ወንድ አይደለህም? ደግሞስ በእስራኤል ውስጥ እንደ አንተ ያለ ማን አለ? ታዲያ ጌታህን ንጉሡን በንቃት ያልጠበቅከው ለምንድን ነው? ምክንያቱም ከወታደሮቹ አንዱ ንጉሡን ጌታህን ለመግደል መጥቶ ነበር።+
16 ይህ ያደረግከው ነገር ጥሩ አይደለም። ሕያው በሆነው በይሖዋ እምላለሁ፣ ይሖዋ የቀባውን+ ጌታችሁን በንቃት ስላልጠበቃችሁ ሞት ይገባችኋል። እስቲ ዙሪያህን ተመልከት! በንጉሡ ራስጌ አጠገብ የነበረው የንጉሡ ጦርና የውኃ መያዣ+ የት አለ?”
17 ሳኦልም የዳዊት ድምፅ መሆኑን ስለለየ “ልጄ ዳዊት ሆይ፣ ይህ የአንተ ድምፅ ነው?” አለው።+ ዳዊትም መልሶ “ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፣ አዎ የእኔ ድምፅ ነው” አለ።
18 አክሎም እንዲህ አለ፦ “ጌታዬ አገልጋዩን የሚያሳድደው ለምንድን ነው?+ ምን አድርጌ ነው? የተገኘብኝስ በደል ምንድን ነው?+
19 ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፣ እባክህ የአገልጋይህን ቃል ስማ፦ በእኔ ላይ እንድትነሳ ያደረገህ ይሖዋ ከሆነ የማቀርበውን የእህል መባ ይቀበል።* ሆኖም እንዲህ እንድታደርግ ያነሳሱህ ሰዎች ከሆኑ+ በይሖዋ ፊት የተረገሙ ይሁኑ፤ ምክንያቱም ‘ሂድ፣ ሌሎች አማልክትን አገልግል!’ ብለው በይሖዋ ርስት+ ውስጥ ድርሻ እንዳይኖረኝ ዛሬ አባረውኛል።
20 አሁንም ደሜ ከይሖዋ ፊት ርቆ መሬት ላይ እንዲፈስ አታድርግ፤ ምክንያቱም የእስራኤል ንጉሥ በተራራ ላይ ቆቅ የሚያሳድድ ይመስል አንዲት ቁንጫ+ ለመፈለግ ወጥቷል።”
21 ሳኦልም መልሶ እንዲህ አለው፦ “በእርግጥ ኃጢአት ሠርቻለሁ።+ ልጄ ዳዊት ሆይ፣ ከእንግዲህ ምንም ጉዳት ስለማላደርስብህ ተመለስ፤ ምክንያቱም በዛሬው ዕለት ሕይወቴን* ውድ አድርገህ+ ተመልክተሃታል። በእርግጥም የሞኝነት ድርጊት ፈጽሜአለሁ፤ ትልቅ ስህተት ሠርቻለሁ።”
22 ዳዊትም እንዲህ ሲል መለሰለት፦ “የንጉሡ ጦር ይኸውና። ከወጣቶቹ መካከል አንዱ ይምጣና ይውሰደው።
23 ለእያንዳንዱ ሰው እንደ ጽድቁና+ እንደ ታማኝነቱ የሚከፍለው ይሖዋ ነው፤ ይኸው ዛሬ ይሖዋ እጄ ላይ ጥሎህ ነበር፤ እኔ ግን ይሖዋ በቀባው ላይ እጄን ለማንሳት ፈቃደኛ አልሆንኩም።+
24 እነሆ፣ ዛሬ የአንተ ሕይወት* በፊቴ ውድ እንደሆነች ሁሉ የእኔም ሕይወት* በይሖዋ ፊት ውድ ትሁን፤ ከመከራም ሁሉ ያድነኝ።”+
25 ሳኦልም ዳዊትን “ልጄ ዳዊት ሆይ፣ የተባረክ ሁን። አንተ ታላላቅ ሥራዎችን ታከናውናለህ፤ ድል አድራጊም ትሆናለህ” አለው።+ ከዚያም ዳዊት መንገዱን ቀጠለ፤ ሳኦልም ወደ ስፍራው ተመለሰ።+