አንደኛ ሳሙኤል 27:1-12

  • ፍልስጤማውያን ጺቅላግን ለዳዊት ሰጡት (1-12)

27  ሆኖም ዳዊት በልቡ እንዲህ አለ፦ “አንድ ቀን በሳኦል እጅ መጥፋቴ አይቀርም። የሚያዋጣኝ ወደ ፍልስጤማውያን ምድር መሸሽ ነው፤+ ሳኦልም ተስፋ ቆርጦ በእስራኤል ግዛት ሁሉ እኔን መፈለጉን ያቆማል፤+ እኔም ከእጁ አመልጣለሁ።”  በመሆኑም ዳዊት አብረውት ከነበሩት 600 ሰዎች+ ጋር ተነስቶ የጌት ንጉሥ ወደሆነው ወደ ማኦክ ልጅ ወደ አንኩስ+ ተሻገረ።  ዳዊትና ሰዎቹም እያንዳንዳቸው ከነቤተሰባቸው ጌት ውስጥ አንኩስ ዘንድ ተቀመጡ። ዳዊትም ከሁለቱ ሚስቶቹ ማለትም ከኢይዝራኤላዊቷ ከአኪኖዓም+ እና የናባል ሚስት ከነበረችው ከቀርሜሎሳዊቷ ከአቢጋኤል+ ጋር ነበር።  ሳኦልም ዳዊት ወደ ጌት መሸሹ ሲነገረው እሱን መፈለጉን ተወ።+  ከዚያም ዳዊት አንኩስን “በፊትህ ሞገስ አግኝቼ ከሆነ በገጠር ካሉ ከተሞች በአንዱ እንድኖር ቦታ እንዲሰጡኝ አድርግ። አገልጋይህ ለምን በንጉሥ ከተማ ከአንተ ጋር ይኖራል?” አለው።  በመሆኑም አንኩስ በዚያ ቀን ጺቅላግን+ ሰጠው። ጺቅላግ እስካሁንም ድረስ የይሁዳ ነገሥታት ይዞታ የሆነችው በዚህ ምክንያት ነው።  ዳዊት በፍልስጤማውያን ገጠራማ አካባቢ የኖረበት ጊዜ* አንድ ዓመት ከአራት ወር ነበር።+  ዳዊትም ከሰዎቹ ጋር በመሆን ገሹራውያንን፣+ ጊዝራውያንን እና አማሌቃውያንን+ ለመውረር ይወጣ ነበር፤ ምክንያቱም እነዚህ ሕዝቦች ከቴላም አንስቶ እስከ ሹር+ እና እስከ ግብፅ ምድር ድረስ ባለው አካባቢ ይኖሩ ነበር።  ዳዊት በምድሪቱ ላይ ጥቃት በሚሰነዝርበት ጊዜ ወንድም ሆነ ሴት በሕይወት አያስቀርም ነበር፤+ ሆኖም መንጎችን፣ ከብቶችን፣ አህዮችን፣ ግመሎችንና ልብሶችን ወስዶ ወደ አንኩስ ይመለስ ነበር። 10  አንኩስም “ዛሬ በማን ላይ ዘመታችሁ?” ይለው ነበር። ዳዊትም “በይሁዳ ደቡባዊ ክፍል*+ ላይ ዘምተን ነበር” ወይም “በየራህምኤላውያን+ ምድር ደቡባዊ ክፍል ላይ ዘምተን ነበር” አሊያም “በቄናውያን+ ምድር ደቡባዊ ክፍል ላይ ዘምተን ነበር” በማለት ይመልስለት ነበር። 11  ዳዊት “‘እሱ እንዲህ አደረገ’ በማለት ስለ እኛ ሊነግሯቸው ይችላሉ” ብሎ ስላሰበ ወንድም ሆነ ሴት በሕይወት አስተርፎ ወደ ጌት አያመጣም ነበር። (ዳዊት በፍልስጤም ገጠራማ አካባቢ በኖረበት ዘመን ሁሉ እንዲህ የማድረግ ልማድ ነበረው።) 12  ስለዚህ አንኩስ ‘በእርግጥም ይህ ሰው በገዛ ሕዝቦቹ በእስራኤላውያን ዘንድ እንደ ጥንብ ተቆጥሯል፤ ስለሆነም ዕድሜ ልኩን አገልጋዬ ይሆናል’ ብሎ ስላሰበ ዳዊትን አመነው።

የግርጌ ማስታወሻ

ቃል በቃል “የቀናት ቁጥር።”
ወይም “ኔጌብ።”