አንደኛ ሳሙኤል 28:1-25

  • ሳኦል በኤንዶር የምትኖር አንዲት መናፍስት ጠሪ ጠየቀ  (1-25)

28  በዚያም ዘመን ፍልስጤማውያን ከእስራኤል ጋር ለመዋጋት ሠራዊታቸውን አሰባሰቡ።+ በመሆኑም አንኩስ ዳዊትን “መቼም አንተና ሰዎችህ አብራችሁኝ ወደ ጦርነት እንደምትወጡ ታውቃለህ” አለው።+  ዳዊትም አንኩስን “አገልጋይህ ምን እንደሚያደርግ አንተ በእርግጥ ታውቃለህ” አለው። ከዚያም አንኩስ ዳዊትን “እኔም በቋሚነት የግል ጠባቂዬ* እንድትሆን የምሾምህ ለዚህ ነው” አለው።+  በዚህ ጊዜ ሳሙኤል ሞቶ ነበር፤ እስራኤላውያንም ሁሉ አልቅሰውለት በገዛ ከተማው በራማ+ ቀብረውት ነበር። ሳኦልም መናፍስት ጠሪዎችንና ጠንቋዮችን ከምድሪቱ አስወግዶ ነበር።+  ፍልስጤማውያንም ተሰብስበው በመምጣት በሹነም+ ሰፈሩ። ሳኦል ደግሞ እስራኤላውያንን በሙሉ አሰባሰበ፤ እነሱም በጊልቦአ+ ሰፈሩ።  ሳኦል የፍልስጤማውያንን ሠራዊት ባየ ጊዜ ፈራ፤ ልቡም እጅግ ተሸበረ።+  ሳኦል ይሖዋን ቢጠይቅም+ ይሖዋ በሕልምም ሆነ በኡሪም+ አሊያም በነቢያት በኩል መልስ አልሰጠውም።  በመጨረሻም ሳኦል አገልጋዮቹን “መናፍስት ጠሪ+ ፈልጉልኝ፤ እኔም ሄጄ ምክር እጠይቃታለሁ” አላቸው። አገልጋዮቹም “በኤንዶር+ አንዲት መናፍስት ጠሪ አለች” በማለት መለሱለት።  በመሆኑም ሳኦል ማንነቱን ሰውሮና ሌላ ልብስ ለብሶ ከሁለት ሰዎች ጋር በመሆን በሌሊት ወደ ሴትየዋ ሄደ። እሱም “እባክሽ፣ መናፍስትን ጠርተሽ+ ጠንቁይልኝ፤ የምነግርሽንም ሰው አስነሺልኝ” አላት።  ሆኖም ሴትየዋ እንዲህ አለችው፦ “ሳኦል መናፍስት ጠሪዎችንና ጠንቋዮችን ከምድሪቱ በማስወገድ ምን እንዳደረገ አንተ ራስህ በሚገባ ታውቃለህ።+ ታዲያ እኔ እንድገደል ልታጠምደኝ* የምትሞክረው ለምንድን ነው?”+ 10  ከዚያም ሳኦል “ሕያው በሆነው በይሖዋ እምላለሁ፣ በዚህ ጉዳይ በጥፋተኝነት አትጠየቂም!” በማለት በይሖዋ ማለላት። 11  በዚህ ጊዜ ሴትየዋ “እሺ ማንን ላስነሳልህ?” አለችው። እሱም “ሳሙኤልን አስነሺልኝ” አላት። 12  ሴትየዋም “ሳሙኤልን”*+ ስታየው በኃይል ጮኸች፤ ከዚያም ሳኦልን “ያታለልከኝ ለምንድን ነው? አንተ ሳኦል አይደለህ!” አለችው። 13  ንጉሡም “አትፍሪ፤ ለመሆኑ ምን እያየሽ ነው?” አላት። ሴትየዋም ለሳኦል “አማልክትን የሚመስል ከምድር ሲወጣ አያለሁ” ስትል መለሰችለት። 14  እሱም ወዲያውኑ “ምን ይመስላል?” አላት፤ እሷም “የወጣው አንድ አረጋዊ ሰው ነው፤ እጅጌ የሌለው ቀሚስ ለብሷል”+ አለችው። በዚህ ጊዜ ሳኦል የወጣው “ሳሙኤል” እንደሆነ ተገነዘበ፤ በግንባሩም መሬት ላይ ተደፍቶ ሰገደ። 15  ከዚያም “ሳሙኤል” ሳኦልን “እንድነሳ በማድረግ ለምን ትረብሸኛለህ?” አለው። ሳኦልም እንዲህ አለው፦ “ከባድ ጭንቅ ውስጥ ገብቻለሁ። ፍልስጤማውያን እየወጉኝ ነው፤ አምላክም ከእኔ ርቋል፤ በነቢያትም ሆነ በሕልም አማካኝነት መልስ አይሰጠኝም፤+ ስለሆነም ምን ማድረግ እንዳለብኝ እንድትነግረኝ ጠራሁህ።”+ 16  “ሳሙኤልም” እንዲህ አለው፦ “ታዲያ ይሖዋ ከራቀህና+ ጠላት ከሆነብህ እኔን ለምን ትጠይቀኛለህ? 17  ይሖዋ በእኔ በኩል አስቀድሞ የተናገረውን ይፈጽማል፦ ይሖዋ መንግሥትን ከእጅህ ነጥቆ ከባልንጀሮችህ አንዱ ለሆነው ለዳዊት ይሰጠዋል።+ 18  የይሖዋን ቃል ስላልሰማህና በአማሌቃውያን ላይ የነደደውን ቁጣውን ስላላስፈጸምክ+ ይሖዋ በዚህ ቀን ይህን ያደርግብሃል። 19  ይሖዋ አንተንም ሆነ እስራኤላውያንን ለፍልስጤማውያን+ አሳልፎ ይሰጣችኋል፤ ነገ አንተና+ ልጆችህ+ ከእኔ ጋር ትሆናላችሁ። በተጨማሪም ይሖዋ የእስራኤልን ሠራዊት ለፍልስጤማውያን አሳልፎ ይሰጣል።”+ 20  በዚህ ጊዜ ሳኦል በቁመቱ መሬት ላይ ተዘረረ፤ “ሳሙኤል” በተናገረውም ቃል የተነሳ በከፍተኛ ፍርሃት ተዋጠ። ደግሞም ሙሉ ቀንና ሙሉ ሌሊት እህል ስላልቀመሰ አቅሙ ተሟጠጠ። 21  ሴትየዋም ወደ ሳኦል መጥታ በጣም እንደተረበሸ ስታይ እንዲህ አለችው፦ “እንግዲህ እኔ አገልጋይህ ቃልህን ሰምቻለሁ፤ ሕይወቴን አደጋ ላይ ጥዬም*+ እንዳደርገው የነገርከኝን ፈጽሜአለሁ። 22  አሁንም እባክህ፣ የአገልጋይህን ቃል ስማ። ትንሽ ምግብ ላቅርብልህና ብላ፤ ከዚያም ለመሄድ የሚያስችል ብርታት ታገኛለህ።” 23  እሱ ግን “አልበላም” በማለት እንቢ አለ። ሆኖም አገልጋዮቹና ሴትየዋ አጥብቀው ለመኑት። በመጨረሻም ቃላቸውን በመስማት ከመሬት ተነስቶ አልጋ ላይ ተቀመጠ። 24  ሴትየዋም ቤት ውስጥ አንድ የሰባ ጥጃ ነበራት፤ ስለዚህ ፈጠን ብላ ጥጃውን አረደችው፤* ከዚያም ዱቄት ወስዳ ካቦካች በኋላ ቂጣ ጋገረች። 25  ለሳኦልና ለአገልጋዮቹም አቀረበችላቸው፤ እነሱም በሉ። ከዚያም ተነስተው በሌሊት ሄዱ።+

የግርጌ ማስታወሻ

ቃል በቃል “በዘመኑ ሁሉ የራሴ ጠባቂ።”
ወይም “ነፍሴን ልታጠምድ።”
ወይም “ሳሙኤልን መስሎ የቀረበውን።”
ወይም “ነፍሴን በእጄ ይዤም።”
ወይም “ሠዋችው።”