አንደኛ ሳሙኤል 29:1-11

  • ፍልስጤማውያን በዳዊት ላይ ጥርጣሬ አደረባቸው (1-11)

29  ፍልስጤማውያን+ ሠራዊታቸውን በሙሉ በአፌቅ አሰባሰቡ፤ እስራኤላውያን ደግሞ በኢይዝራኤል+ በሚገኘው ምንጭ አጠገብ ሰፍረው ነበር።  የፍልስጤም ገዢዎችም በመቶዎችና በሺዎች እየሆኑ አለፉ፤ ዳዊትና ሰዎቹም ከአንኩስ+ ጋር ሆነው ከኋላ ተሰልፈው ይሄዱ ነበር።  የፍልስጤም መኳንንት ግን “እነዚህ ዕብራውያን እዚህ ምን ያደርጋሉ?” አሉ። በዚህ ጊዜ አንኩስ የፍልስጤምን መኳንንት “ይህ ሰው ከእኔ ጋር ለአንድ ዓመት ወይም ከዚያ በላይ አብሮኝ የኖረው የእስራኤል ንጉሥ የሳኦል አገልጋይ የሆነው ዳዊት ነው።+ ወደ እኔ ከተጠጋበት ቀን አንስቶ እስከዚህች ዕለት ድረስ ምንም ስህተት አላገኘሁበትም” አላቸው።  የፍልስጤም መኳንንት ግን በእሱ ላይ ተቆጥተው እንዲህ አሉት፦ “ይህ ሰው እንዲመለስ አድርግ።+ ወደሰጠኸውም ስፍራ ይመለስ። በውጊያው ወቅት እኛኑ ዞሮ እንዳይወጋን+ አብሮን ወደ ጦርነቱ እንዲሄድ ማድረግ የለብህም። ደግሞስ ከጌታው ጋር ለመታረቅ የእኛን ሰዎች ራስ ቆርጦ ከመውሰድ በስተቀር ምን የተሻለ ነገር ሊያደርግ ይችላል?  ይህ ሰው ‘ሳኦል ሺዎችን ገደለ፤ዳዊት ደግሞ አሥር ሺዎችን ገደለ’ በማለት እየዘፈኑ የጨፈሩለት ዳዊት አይደለም?”+  በመሆኑም አንኩስ+ ዳዊትን ጠርቶ እንዲህ አለው፦ “ሕያው በሆነው በይሖዋ እምላለሁ፣ አንተ ቅን ሰው ነህ፤ በእኔ በኩል ከሠራዊቴ ጋር አብረህ ብትዘምት ደስ ባለኝ፤+ ምክንያቱም ወደ እኔ ከመጣህበት ቀን አንስቶ እስከዚህች ዕለት ድረስ ምንም ስህተት አላገኘሁብህም።+ ሆኖም ገዢዎቹ አላመኑህም።+  ስለዚህ በሰላም ተመለስ፤ የፍልስጤም ገዢዎችን ቅር የሚያሰኝ ምንም ነገር አታድርግ።”  ዳዊት ግን አንኩስን “ምን አደረግኩ? ወደ አንተ ከመጣሁበት ጊዜ አንስቶ እስከዚህች ዕለት ድረስ በአገልጋይህ ላይ ምን ጥፋት አግኝተህበታል? ከአንተ ጋር የማልሄደውና ከንጉሡ ከጌታዬ ጠላቶች ጋር የማልዋጋው ለምንድን ነው?” አለው።  አንኩስም ዳዊትን እንዲህ አለው፦ “በእኔ በኩል አንተ እንደ አምላክ መልአክ ጥሩ ሰው ነህ።+ የፍልስጤም መኳንንት ግን ‘ከእኛ ጋር ለጦርነት እንዲወጣ አታድርግ’ አሉኝ። 10  አሁንም አብረውህ ከመጡት የጌታህ አገልጋዮች ጋር በማለዳ ተነሱ፤ ልክ ጎህ ሲቀድ ጉዞ ጀምሩ።” 11  በመሆኑም ዳዊትና ሰዎቹ ወደ ፍልስጤማውያን ምድር ለመመለስ በጠዋት ተነሱ፤ ፍልስጤማውያንም ወደ ኢይዝራኤል+ ወጡ።

የግርጌ ማስታወሻ